ልደት
ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በአምላክ ፈቃድ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ ታኅሣም 24 ቀን1212 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ወላጆቻቸው ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን
በማለት አወጡላቸው፡፡ በተወለዱ በሦስተኛውም ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው “አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፡- አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው፡፡” በማለት የሥላሴን ስም ጠርተው አመስግነዋል፡፡
በተወለዱ በ15 ዓመት ዕድሜያቸው ዲቊናን፣በ22 ዓመታቸው ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ /ቄርሎስ/ ተቀብለዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን አባታችን ወደ ጫካ ለአደን ሄደው ሳለ፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ግሩም ድንቅ የሆነ ልብስ ለብሶ ታያቸው፡፡ አባታችንም እንደዚህ ባለ ገናንነት የማይህ ጌታዬማነህ?” አሉት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም “ዘወትር የምጠብቅህ ካንተ የማልለይ እናትህንና አባትህንም ስላንተ ከውኃ ስጥመትና ከምርኮ ያዳንኳቸው እኔ ሚካኤል ነኝ፡፡ እንግዲህ አውሬ አዳኝ አትሁን፤ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ሰውን በትምህርት የምታድን ሁን እንጂ፡፡
እነሆ እግዚአብሔር ጽኑዕ ሥልጣን ሰጥቶሀልና፤ ሙት ታስነሣለህ፤ ድውያንን ትፈውሳለህ፤ አጋንንትም አንተን በመፍራት ይሸሻሉ፡፡ ስምህ ፍሥሐ ጽዮን አይሁን፤ ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንጂ፡፡ ትርጓሜውም ተክለ አብ፥ ተክለ ወልድ፥ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፡፡”አላቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ይህን ሲያነጋግራቸው ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በሥጋ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበር ሆኖ መልከ መልካም ጎልማሳ መስሎ ታያቸው፡፡ ጌታችንም “ወዳጄ እንዴት ሰነበትክ! ቸር አለህን፤” አላቸው፡፡ ብፁዕ ተክለ ሃይማኖትም“ጌታዬ ሆይ አንተ ማነህ? ብለው ጠየቁ፡፡ ጌታም “እኔ የዓለምመድኀኒት ኢየሱስ ነኝ፤ በናትህ ማኅፀን ፈጥሬህ ያከበርኩህ እኔ ነኝ፡፡ በተወለድክ በሦስተኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፥አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፥ብለህ ታመሰግነኝ ዘንድ የምስጋና ሀብት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ በረሃብ ዘመን በቤት የሚያሻው ምግብ ሁሉ ቅቤው፣ የስንዴው ዶቄት በእናት በአባትህ ቤት ይመላ ዘንድ በእጅህ ሀብተ በረከት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ ያንን ሰው አንተን በተጣላ ጊዜ በነፋስ አውታር የሰቀለኩት በመዓት ጨንገር የገረፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ውኃ ጠምቶህ
በለመንከኝ ጊዜ ከደረቅ መሬት የጣፈጠ ውኃ ያመነጨሁልህ
አኔ ነኝ፡፡ ከልጅነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ተአምራት እያደረግሁ በአንተ እጅ የታመሙትን ያዳንኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ወደ ፊትም አደርግልሃለሁ፡፡ ይህንን ብሎ ንጹሓት ክቡራት በሆኑ እጆቹ ባረካቸው “ንሣእ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ የሹመትን ሀብት አሳደረባቸው፡፡ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሁን፡፡ በምድርም የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሁን፤ አንተን የሰማ እኔን መስማቱ ነው፤ የላከኝ አባቴንም መስማቱ ነው፡፡ አንተን እንቢያለ እኔን እንቢ ማለቱ ነው፡፡ የላከኝ አባቴንም እንቢ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ቀድሞ ለሐዋርያት ሰጥቻቸው ነበር፡፡ ከሐዋርያትም ሹመትን የተቀበለ ጳጳሱ ትሾምና ትሽር ትተክልና ትነቅል ዘንድ ሥልጣንን ሰጠህ፡፡ ይህንንም ያደረኩልህ የጳጳሱን ቃ ል በመናቅ አይደለም፡፡ የፍቅሬን ጽናት ባንተ እገልጽ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ሐዋርያት ወደአልደረሱበት ሕዝብ በመምህርነትእልክህ ዘንድ በሚካኤል ቃል አዲስ ስም አወጣሁልህ፡፡ አንተም
በማናቸውም ሥራ ከነሱ አታንስም፡፡ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጌሃለሁና፡፡ ሰውን ሁሉ በእኔ ስም እያስተማርክ ታሳምን
ዘንድ፤ ሚካኤልም ባሰብከው ሥራ ሁሉ ረዳት ይሁንልህ፡፡ ሁልጊዜ ካንተ አይለይም፡፡ በምትሄድበትም ጎዳና ሁሉ እርሱ መሪ ይሁንህ፡፡ እኔም ባለ ዘመንህ ሁሉ አልለይህም” ብሎ ሰላምታ ሰጥቷቸው ዐረገ፡፡ ብፁዕ አባታችንም እጅ ነስተው “ለእኔ ለኀጥኡ የማይገባኝ ሲሆን ይህን ሁሉ ጸጋ የጠኸኝ ስምህ በሰማይ በምድር የተመሰገነ ይሁን” አሉ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሀብተ ኀይልን የተመሉ ሆኑ፡፡ ከዚያም ወደቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ጨረሱ፡፡ ከዚያም “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን
እንደተከፈተ ተውኩልህ” ብለው ቤታቸውን እንደተከፈተ ትተው
ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ /ገድለ ተክለሃይማኖት ዘሠሉስ ምዕ.28 ገጽ 116/
ሐዋርያዊ አገልግሎት
ከ1219-1222 ዓ.ም. በከተታ ሦስት ዓመት፣ ወንጌልን አስተማሩ፡፡ ቀጥለውም ዘጠኝ ወር በዊፋት አገልግሎታቸውን ፈጽመዋል፡፡ ከ1223-1234 ዓ.ም. ዳሞት በተባለው ስፍራ ወይም በወላይታ ሀገር ለ12 ዓመታት ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ትምህርት በመስጠት ተአምራት አድርገው፤ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንፀዋል፡፡ በዚህ ሀገር ዲያብሎስ በዛፍ ላይ አድሮ አምላክ ነኝ እያለ ለረጅም ዘመናት ሕዝቡን በማሳት የሚጠቀምበትን ዛፍ በተአምራት ከሦሩ ነቅለው አፍልሰዋል፡፡
እምነት
በዚህ ተግባራቸው ጌታችን በቅዱስ ወንጌል “የሰናፍጭ ቅንጣት
የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፤ ይሄንን ሾላ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችኋል፡፡” ሉቃ.17፥6 ያለውን አምላካዊ ቃል በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ወደ አማራ ሳይንት ወሎ በመሄድ ሥርዓተ ምንኲስናን ከአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ገብተው ከ1234-1244 ዓ.ም. ለዓሥር ዓመታት የእርድና ሥራበመሥራትና ገቢረ ታምራትን በማሳየት ጌታ በቅዱስ ወንጌል“ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ ለእናንተ አገልጋይይሁን፤ ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፡፡ እንዲሁም የሰው ልጅ /ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ/ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም፡፡ ማቴ.20፥26-28 ያለውን መለኮታዊ ትእዛዝ በተግባር አሳይቷል፡፡ ከ1244-1254 ዓ.ም. አባ ኢየሱስ ሞዓ ወደሚገኙበት ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ሐይቁን በእግራቸው እንደ ደረቅ መሬት በመርገጥ ወደ ደሴቲቱ በመግባት የምንኲስናን ተግባራቸውን በመቀጠል በግብረ ሐዋርያትና በወንጌል
የተነገረውን የእርድናን ተግባር ፤የአገልግሎትና ትሩፋት/ሥራ ከፍጻሜ አድርሰዋል፡፡ በአባ ኢየሱስ ሞዓ እጅም የንጽሕና ምልክት የሆነውን የምንኲስናን ቀሚስ ተቀብለዋል፡፡
ከ1254-1266 ዓ.ም. ለዐሥራ ሁለት ዓመታት አቡነ አረጋዊ ወዳቀኑት ገዳም በትግራይ ሀገረ ስብከት ወደሚገኘው ደብረ ዳሞ ገዳም በመግባት በጊዜው ከነበሩት አበምኔት ከአባ ዮሐኒ ቆብና አስኬማ ተቀብለው በገድል በትሩፋት መንፈሳዊተጋድሎአቸውን ቀጠሉ፡፡ ከደብረ ዳሞ ገዳም ወደሌላ ለመሄድ ሲነሡ፤ ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት አበምኔቱና መነኰሳቱ ሲሸኟቸው ሳለ፤ አርባ ክንድ ርዝመት ባለው ገመድ ገደሉን ለመውረድ እንደጀመሩ፤ ገመዱ ከካስማው ሥራ በመቆረጡ እንዳይወድቁ በተሰጣቸው ስድስት የብርሃን ክንፎች እየበረሩ፤ ክንፎቻቸውን እያማቱ ሦስት ምዕራፍ ሄደው ዐርፈዋል፡፡ ከዚያም ወደ ገዳመ ዋሊ ገብተዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት “ለደካማ ኀይልን ይሰጣል፤ ጉልበት ለሌለው ብርታትን ይጨምራል፡፡ ብላቴኖች ይደክማሉ፤ ይታክቱማል፡፡
ጐበዛዝትም ፈጽመው ይወድቃሉ፡፡ እግዚአብሔርን በመተማመን
የሚጠብቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስርም በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፡፡ “ኢሳይያስ 40፥29-31 ያለው ቃል በጻድቁ በቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሕይወት ሊተረጐም ችሏል፡፡ ከ1266-1267 ዓ.ም. አንድ ዓመት ሙሉ ገዳማተ
ትግራይን በመጐብኘት ኢየሩሳሌምንና ግብፅ ያሉ ቅዱሳትመካናትን ሲጎበኙ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ወር ሙሉ “ዳዳ” በተባለ ስፍራ ይመለክ የነበረውን 75 ክንድ ዘንዶ በጸሎት ኀይል በተአምራት ገድለውታል፡፡ አርባዓቱ እንስሳ /በኪሩቤልና በሱራፌል/ ስም ቤተ ክርስቲያን አንፀው፤ ታቦተ ሕግ /ጽላተ ሕግ/ አስገብተዋል፡፡ ከሴቶችና ከልጆች ሌላ፤ ሦስት ሺህ በጣዖት የሚያመልኩ ወንዶችን መልሰው፤
አጥምቀው አቊርበዋል፡፡ በዚህም ተግባራቸው መድኀኒታችን
“እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጎዳችሁም ምንም የለም” ሉቃስ 10፥19 ያለው ቃል ተፈጽሞላቸዋል፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙር 90፥13-14 “በተኲላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውና ዘንዶውን ትረግጣለህ፡፡ በእኔ ተማምኗልናአስጥለዋለሁ፤ ስሜንም ዐውቋልና እጋርደዋለሁ፡፡” የተባለው ትንቢት ተፈጽሞላቸዋል፡፡ ከ1267-1289 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት፤ ስምንት ጦሮችን /ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ አስተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት
የክርስቶስን ሕማምና ሞት፣ ነገረ መስቀልን በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን ያለማቋረጥ በጾምና በጸሎት በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ ጥር 4 ቀን 1289 ዓ.ም. አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም አክብረው በሥርዓት አኑረውታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታት በቊጥር ሃያ ሁለት ናቸው፡፡ በመዓልትና በሌሊት በትጋትና በቊመት በተጋድሎ ብዛት፤ አንዲት የአገዳ እግራቸው ስትሰበር፤ ዕድሜያቸው 92 ዓመት ሆኗቸው ነበር፡፡
መንፈሳዊ ተጋድሎና እረፍት
ከ1289-1296 ዓ.ም. ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው በመቆም ያለምግብና ያለውኃ በትኅርምት ሌትና ቀን እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር እንደ ምሰሶ ጸንተው፤ በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት
ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ ነበር፡፡ ማቴ.4፥4 የሐ.14፥22፣ 2ቆሮ.11፥26፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጌታችን ተገልጾ፤ “በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት
አዳራሽ ውሰድ” በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያላቸው የመንግሥት ልብስ አልብሷቸዋል፡፡ በመስቀል
ምልክት የተጌጡት ሰባት የሕይወት አክሊላት “ስለ ቀናች ሃይማኖትህ፤ ሃይማኖትን ለማስተማር መላዋን ኢትዮጵያን ስለመዞርህ፤ ከአረማውያን ሕዝብ ጋር በሃይማኖት ስትታገል ደምህን ስለማፍሰስህ፤ ወደ ኢየሩሳሌም ወርደህ ልዩ ልዩ የቅዱሳን ቦታዎች ስለመሳለምህ፤ በሰባት ዓመታት ቊመት የአንዱ አገዳ እግርህ ስለመሰበሩ፤ ስለብዙ ጾም ጸሎትህ ስግደትህ፤ ስለልብህ ንጽሕናና ቅድስና” ብሎ አቀዳጅቷቸዋል፡፡ ዝክራቸውን በማዘከር መታሰቢያቸውን የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ፍጹም ዋጋና ፍጹም ክብር እንደሚሰጣቸው ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ያዕ.1፥12፣
ራእ.14፥1213፣ 2ጢሞ.4፥6-8 በመጨረሻም ለዐሥር ቀናት በሕመም ቆይተው፤ ፈጣሪያቸው የገባላቸውን ቃል ኪዳን ለመነኰሳት መንፈሳውያን ልጆቻቸውና ለደቀ መዛሙርቶቻቸው ከነገሩ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን በክብር ዐርፈዋል፡፡
በረከታችው ይድርብን
No comments:
Post a Comment