የቅዱሳን አማላጅነት በአጸደ ነፍስ
ቅዱሳን ሰዎች ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኃላ በነፍስ ዓለም ወይም በአካለ ነፍስ ሆነው ማመስገን መጸለይና ማማለድ ይችላሉ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከለክላቸዋል››› (ሮሜ8፡33) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተናገረ፡፡ ሞት ማለት መለየት ማለት ሲሆን ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡
1. ሞተ ሥጋ የሥጋና የነፍስ መለየት ሲሆን አዳም ሕግን በማፍረሱ በሰው ላይ የተፈረደ ነው፡፡ “አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና ” (ዘፍ3፡19)
2.ሞተ ነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ ለመንግስተ ሰማያት የተፈጠረች ነፍስ ለአጋንንት ወደ ተዘጋጀ ገሃነመ እሳት ከፈጣሪዋ አንድነት ተለይታ መባረር ማለት ነው፡፡ ‹‹እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመላዕክቱ ወደተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ሂዱ›› (ማቴ25፡41)
በብሉይ ኪዳን ዘመን ሞተ ሥጋ ይፈራ ነበር፡፡ ‹‹በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።››( ዕብ2፡14‐16) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ከክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ወዲህ ሞት እንደተሻረ ገለጸ፡፡ ቅዱሳን ሞታቸው እረፍታቸው ነው፡፡ቅዱሳን ሞትን አይፈሩትም፡፡ ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?››
ቅደሳን ሰዎች ከዚህ ዓለም መለየታቸውን ይናፍቁታል፡፡ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ ‹‹ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፡፡ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፡፡ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።››( ፊልጵ1፡23) በማለት በዚህ ዓለም ከመኖር የሰማዩ ኑሮአቸው ለቅዱሳን መልካም እንደሆነ ተናገረ፡፡ቅዱሳን በዚህ ዓለም የተሰጣቸው የማማለድ ጸጋና ሥልጣን ከእረፍታቸው በኃላ በአጸደ ነፍስ አይነሳቸውም፡፡ የሚከተሉትም ይህን የሚያስረዱ ናቸው፡፡
1.
“አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ
ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።
በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ
እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።”
ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።›› (ራዕ 6፡9‐11) ይህ የሚያሳየን ከሞት በኃላ መጸለይ እንደሚቻል አይደለምን›እዚህ ላይ ቅዱሳን የጸለዩት
መከራ ስቃይ
ያደረሱባቸውን አምላካቸው
እንዲበቀላቸው ነው፡፡
በክፉዎቹ ላይ ከጸለዩባቸው ለበጎዎች እንዴት አይጸልዩላቸው› መናገር አይችሉም የሚሆነውን አያውቁምና ከሞቱ በኃላ አያማልዱም ማለት ግን ‹‹እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ…..የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።›› (ማር12፡26‐27) ያለውን ቃል አለማስታወስ ነው፡፡ አብርሃም፣ ይስሐቅ ከሞቱ በኃላ ስለ አብርሃም ስለ ይስሃቅ ብለህ እያሉ እነ ሊቀነቢያት ሙሴ ይለምኑት የነበረው የሞቱትን ወዳጆቼን ቃልኪዳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ ብቻ ነው የምጠብቀው ስላላላቸው ነው፡፡ እንዲያውም በሰሩት የጽድቅ ስራ ሕያዋን እንጂ ሙታን አለመሆናቸውን ገለጸ እንጂ፡፡
2.
ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል ባስተማረው ታሪክ ላይ አንድ ባለጸጋ ነዌ የተባለና በሱ ደጅ ወድቆ ሳለ ያልጠየቀው ሲጸየፈው የኖረው አልዓዛር የተባለ ሰው ነበር፡፡ ሁለቱም ሞቱ አልዓዛር በአብርሃም እቅፍ ሆኖ ባለጸጋው ነዌ ግን በሲኦል ውሃ ጥም ጸንቶበት ይሰቃይ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አልዓዛርን በአብርሃም እቅፍ ሆኖ ተመለከተው፡፡ ነዌ አልዓዛርን በዚህ ምድር ሳለ አልረዳውምና እርሱን መጥራት ቢያፍር አብርሃምን እየጮኧ ‹‹አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ በዚህ ነበልባል እሰቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ›› አለው፡፡ አብርሃም ግን ‹‹ልጄ ሆይ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ›› በማለት ሁለቱም በዚህ በምድር በሰሩት ስራ አጸፌታቸውን እየተቀበሉ መሆኑን አስረዳው ፡፡ ባለጸጋው የሰራው ስራ በቅዱሳን ረድኤትና በእግዚአብሔር ቸርነት ለመጠቀም እንደማያበቃው ባወቀ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ለመነ፡፡ ‹‹ እንኪያስ አባት ሆይ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ:: አምስት ወንድሞች አሉኝና እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው›› አብርሃም ግን መለሰና ‹‹ሙሴና ነቢያት አሉአቸው እነርሱን ይስሙ›› አለው። የወንድሞቹን አመጸኝነት የሚያውቀው ይህ ባለጸጋ መልሶ ‹‹አይደለም አብርሃም አባት ሆይ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ›› አለው። አብርሃም ግን ‹‹ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆኑ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም›› አለው።
ይህ የአብርሃምና የባለጸጋው
ጥያቄና መልስ የሚያስረዳው፡-
1. አብርሃም ከሞተ በኃላ በዚህ ዓለም ስለተፈጸሙት ነገሮች ማወቁን
1.1
አብርሃም የነበረው በዘመነ ሕገ ልቦና ከሙሴና ከነቢያት በፊት ሆኖ ሳለ ‹‹ሙሴና ነቢያት አሉላቸው›› ማለቱ ሙሴ የተባለ ነቢይ መነሣቱን በእርሱም በኩል ህግ መሰጠቱን እንዲሁም ሌሎች ነቢያት መነሣታቸውንና መጽሐፍ መጻፋቸውን በማወቁ ነው፡፡
1.2 አብርሃም
ስለ አልዓዛር ደሃ መሆን ይህን ሰው ያልረዳ ክፉ ባለጸጋ መኖራቸውን አውቀዋል፡፡ አብርሃም በነዚህ ሰዎች ዘመን አልነበረም፡፡ የአልዓዛርና የዚህን ባለጸጋ ሕይወት ምንም እንክዋን አብርሃም በነሱ ዘመን በሥጋ ባይኖርም በተሰጠው ጸጋ እግዚአብሔር ምን ዓይነት እንደነበር አውቆ ‹‹ልጄ ሆይ አንተ በሕይወት ሳለህ መልካም እንደተቀበልክ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ›› በማለት የነበራቸውን ምድራዊ ሕይወት ነግሮዋቸዋል፡፡ አብርሃም ስላለፈው ብቻ ሳይሆን ስለወደፊቱም ‹‹ሙሴና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆነ ከሙታንም እንክዋ አንድ ቢነሳ አያምኑም›› በማለት የሰዎቹን ልበ ደንዳናነትና አለማመን ማወቁን ያስረዳል፡፡
2. የአብርሃምን ሕያውነት
አብርሃም ከዚህ ዓለም ከተለየ ብዙ ዘመን ቢሆነውም በእግዚአብሔር ዘንድ ሕያው በመሆኑ አልዓዛር ሲሞት መላዕክት ወደ እርሱ እቅፍ ወሰዱት፡፡ ባለጸጋው በሲኦል ሆኖ አብርሃምን አሻግሮ አየው፡፡ ከስቃዩ ያስታግስለት ዘንድ አልዓዛርን እንዲልክለት ለመነው፡፡ የእርሱ እንደማይሆን ሲረዳ ወንድሞቹን ከሙታን አንዱን ልኮ እንዲመሰክርለት ለመነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚያስረዳን የአብርሃምን ሕያውነት ነው፡፡ ምክንያቱም መታየት፣ መለመን፣ መናገር እና በአጠቃላይ አብርሃም ከባለጸጋው ጋር ያደረጋቸው ነገሮች የሕያውነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ ምውትን ሊያዩትና ሊያናግሩት ሊለምኑት አይቻልም ምውት ቢያናግሩትም ሊሰማና ሊናገር አይችልም፡፡
ይህ ቃል የራሱ የጌታችን ቃል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ብዙ ነገሮችን በምሳሌ አስተምርዋል ስም ግን አልጠቀሰም፡፡ ይህ እውነተኛ ታሪክ ስለሆነ ስም ጠቀሰ፡፡ (ሉቃ16፡19)

Ø ነቢዩ ኤልሳዕ ከሞተ በኃላ ነፍስ የተለየው አጥንቱ የሞተ ሰው አስነሥቶዋል፡፡ (2ነገ 13፡20)
እግዚአብሔር ዳዊት በሕይወተ ሥጋ ሳለ ቃልኪዳን ገብቶለት ነበር፡፡ ‹‹ኪዳኔን አላረክስም ከከንፈሬ የወጣውንም አልለውጥም ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ›› (መዝ88፡34) በማለት፡፡ ዳዊት ከሞተ በኃላ የገባለትን ቃልኪዳን በማክበር ኢየሩሳሌም ላይ ሊያመጣ የነበረውን መዓት መለሰ፡፡ ‹‹ስለእኔም ስለ ባርያዬም ስለ ዳዊት ስል ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እታደጋታለሁ፡፡›› ( 2ነገ 19፡34)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሕያውነታቸውን ሲገልጽ ‹‹ ዛሬስ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን፡፡ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን ዛሬስ ከዕውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግም እንደታወቁሁ አውቃለሁ፡፡›› / 1ቆሮ 13፡12/ /ሉቃ9፡30 ፣ 2ጴጥ 1፡13‐15/
ማጠቃለያ፡-
ቅዱሳን የሚባሉት ያላቸውን ትተው የተከተሉት፤ እናት፣ አባቴ፣ እህት፣ ወንድሜ፣ ዘመድ፣ ሀብት፣ ንብረት ሳይሉ ግርማ ሌሊቱን፣ ጸብዓ አጋንንቱን ፣ እሳት ግርፋቱን ሳይፈሩ እስከመጨረሻው የጸኑትን ማማለድ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምድር ሁሉ እንዲፈርዱ ስልጣን ሰትዋቸዋል፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።›› ማቴ 19፤27‐28 ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የጌታን ቃል መሰረት በማድረግ ‹‹ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን›› አለ፡፡ ለቅዱሳን እንዲያማልዱና እን ዲፈርዱ ብቻ ሳይሆን አምላክ ዘበጸጋ አድርጎ ሾምዋቸዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፡ እይ እኔ በፈርኦን ላይ አምላክ አድርጌሃለው›› ዘፀ 7፡ 1 ፣ መዝ 81፡ 6 ፣ ዩሐ 10 ፡ 34
ማሳሰቢያ፡
የቅዱሳንን እረፍት ስገልጽ ሞት በማለት ተጠቅሜያለሁ ለእናንተ ለማስረዳትና እንዲገባእሁ ከማድረግ አንጻር ነው:: እንጂ ለቅዱሳን ሞቱ አይባልም አረፉ ወይም ከዚህ ዓለም ተለዩ ነው እንጂ፡፡ ሞቱ የሚባለው ለኃጥአን ነው፡፡
የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት፡
መልአክ በነጠላ ሲሆን መላእክት በብዙ ነው፡፡ መልአክ ማለት በግዕዝም በዕብራይስጥም ተላላኪ፣ መልዕክተኛ፣ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ የአምላክ መልዕክተኛ እግዚአብሔር በሚገኝበት ሁሉ የሚገኝ ማለትን ያመለክታል፡፡
መላዕክት በሥነፍጥረት መጀመሪያ በዕለተ እሁድ የተፈጠሩ ረቂቃን መንፈሳዊውያን ኃይሎች ናቸው፡፡ ቅዱሳን ዋና አገልግሎታቸው ያለ ዕረፍት ፈጣሪያቸውን ማመስገን ነው፡፡ ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፤ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው ነው፡፡ ቅዱሳን መላዕክት በባሕሪያቸው ማርጀት፣ ማፍጀት፣ ድካም፣ ሕልፈት፣ ውላጤ የለባቸውም፡፡
እግዚአብሔር መላዕክትን ፈጽሮ በአስር በአስር ረገድ በሰባት ሊቃነ መላዕክት ወይም አለቆች እንደመደባቸው መጽሐፈ አክሲማሮስ ይናገራል፡፡ ቅዱሳን መላዕክት የሰውን ጸሎት ልመና ወደ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔርን ቸርነት በረከት ወደ ሰዎች ያደርሳሉ፡፡ ‹‹……..እርሱም እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል›› (ዳን10፡11)፣ (ዘፍ28፡12)፣ (ዩሐ1፡52)፣ (ዕብ1፡14)፡፡ ቅዱሳን መላዕክት እንዲያማልዱ ስልጣን ሰጥቷዋቸዋል ይኸውም በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል ለአብነት ያህል የተወሰነውን እንመለከታለን፡፡
እስራኤላውያን እግዚአብሔርን አንሰማም በማለታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቶ ከነርሱ ርቆ ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ የእግዚአብሔር መልዐክ ‹‹አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ። እግዚአብሔርም መልሶ……. በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።›› እግዚአብሔር ‹‹አንተ አያገባህም›› አላለውም ይልቁንም በሚያጽናና ቃል ተናገረው እንጂ ስለ መልዐኩም ብሎ ከቁጣው ተመለሰ፡፡ ‹‹…….ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ ቤቴ ይሠራባታል…….ከተሞቼ ደግሞ በበጎ ነገር ይረካሉ……..›› (ዘካ 1፡12‐17) እንዲል።
No comments:
Post a Comment