Thursday, 15 June 2017

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለምን ያላመኑ ሕጻናትን ታጠምቃለች?

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አላዋቂ የሕጻናት ጥምቀት ማጥመቅ ተገቢ ነውን?

በዲያቆን ያሬድ መለሰ

የፕሮቴስታንቱ ዓለም ክፍሎች በማርቆስ ወንጌል የሚገኘውን ክፍለ ንባብ በቁሙ በመተርጎም ‹‹ ያመነ የተጠቀ ይድናል›› የሚለውን ቃል በመጥቀስ ከመጠመቅ በፊት ማመን መቅደም አለበት በማለት ሕጻናት መጠመቅ የለባቸውም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ትምህርታቸውን ብንጠቀልለው ይህንን ይመስላል፡፡
1.       የሕጻናት ጥምቀት በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አልተቀመጠም
2.       የእምነት ጥምቀት(ካመኑ በኋላ ማጥመቅ) ይገባል
3.       ከሌሎች እምነቶች የመጡና ዳግመኛ በ‹‹እውነተኛ››ው ጥምቀት የተጠመቁ የእምነቱ የተቀበሉ አዲስ ሰዎች ሆነዋል የሚል ነው



ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሕጻናትን የምታጥቅበት ምክንያት ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡

  1. መጀመርያው ነጥብ ማር.1616 ላይ የተገለጸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ምንን መሠረት አድርጎ የተነገረ ነው የሚለው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ከሕጻናት ጥምቀት ጋር ምንም አያገናኘውም፡፡ ጌታችን ይህንን የተናገረው ስያስተምር ለነበረው ሕዝብ ነው እነዚህ ደግሞ ጥምቀት ሳይፈጽሙ የሕጻንነት ዘመናቸው ያለፈባቸው ሰዎች እንደሆኑ ከመጽሐፉ ዓውደ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ይሀ ጥቅስ ከሕጻናት ጥምቀት ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡
  2.  ጌታችንም ‹‹ሕጻናትን ወደ እኔ እንዲመጡ ተዉ አትከልክሏቸው የእግዚአብሔር መንግስት እንደነዚህ ላሉት ናትና›› (ማር. 10፥14) የሕጻናት ጥምቀትን የሚደግፉ መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስረጂ ታደርጋለች፡፡
  3. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስን ‹‹ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከመንፈስና ከውሃ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም››(ዮሐ 3፥5) ይህ ማለት ማንኛውም ሰው በጥምቀት ዳግመኛ በመወለድ ወደ እግዚአብሔር ለመግባት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡
  4. በበዓለ ኃምሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲሰብክ ይሕንን ብሎ ነበር ‹‹የተስፋው ቃል ለእናንተና ልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ የሚጠራቸው በሩቅ ላሉሁሉ ነውና አላቸው›› ሐዋ 2፥39) በዚህም ምዕራፍ ላይ በተመሳሳይ ልጆቻቸውም ጭምር ወደ መዳን እንዲቀርቡ ማጥመቅ እንዲገባ ያስተምራቸዋል፡፡ ለዚህም ምስክራችን ‹‹ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ››የሚለው የመጽሐፍ ቃል ነው(ሐዋ. 2፥40)
  5. የጥምቀት ምሳሌ የሆነው ግዝረት በእስራኤላዊያን ልማድ በልጅነት ስለሚደረግ ‹‹በስምንተኛው ቀን ልጅ አስገርዝ›› (ዘፍ.17፥12) ይህም ሥርዓት ከሕጻናት ጥምቀት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የእስራኤላዊያን ሥርዓት ነው፡፡
  6. የመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው በሐዋርያት ዘመን ክርስትናን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ከነቤተ ሰቦቻቸው እንደተጠመቁ አስረጅ የመጻሕፍት ታሪኮች ስላሉ
  • ልድያና ቤተሰቧ (ሐዋ 16፥15)
  •  የወይኒ ቤት ጠባቂውና ቤተሰቡ(ሐዋ. 16፥33)
  •  ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ(ሐዋ 10፥48)
  •  የምኩራቡ አለቃ ቀርስጶስና ቤተሰቡ (ሐዋ 18፥8)
  •  የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች(1ኛ ቆሮ 1፥16)




ስብሐት ለእግዚአብሔር 

No comments:

Post a Comment