Tuesday, 3 January 2017

ዓለም ወዴት እያመራ ነው?


ዓለም ወዴት እያመራ ነው?


በዲ/ን ያሬድ መለሰ

የሮማው ካቶሊክ ‹‹ጳጳስ ›› ፋራንሲስ ከሰሞኑ በላቲን አሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት ጌታ ለሙሴ የሰጠውን አሥሩን ትእዛዛት እንዳሻሽለው አዞኛል በማለት ለካቶሊካዊያኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የሚጨመሩትም ትዕዛዛት ሁለት ሲሆኑ ግብረ ሰዶማዊያን በሕብረት መኖር እንዲችሉና ሰዶማዊያኑ የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እንዲቀበላቸው የሚያዝ ነው፡፡ ካቶሊካዊያኑ ባላቸው ቀኖና መሠረት የቤተ ክርስቲያኑ መሪ(ጳጳሱ) በማንኛውም ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የበላይና ወሳኝ ስለሆነ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ያስፈጽሙ ዘንድ ግድ አላቸው፡፡

ምንም እንኳን ጳጳሱ በይፋ ከግብረ ሰዶማዊያኑ ጋር ሕብረት መፍጠር እንደሚገባ ሲናገሩ የመጀመራቸው ቢሆንም ከዚህ በፊት ለግብረ ሰዶማዊያኑ ድጋፋ የሰጡ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናቸው እንዲጋቡ ጭምር የደገፉ የእምነት ተቋማት ነበሩ፡፡ ይህም ዓለም ወዴት እያመራ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ይህ የ‹‹ጳጳሱ›› ንግግር በሃገረ አሜሪካ ግብረ ሰዶማዊያኑ ‹‹መብት›› ድንጋጌ ጋር ተያይዞ የተነገረ መሆኑ ምናልባትም ካቶሊካዊያኑ ግብረ ሰዶማዊያኑን በቤተ ክርስቲያናቸው የማጋባት ‹‹መብት›› ጭምር ለመስጠት እንዳለመች የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ከ‹‹ጳጳሱ›› ንግግር ሁለት መሠረታዊ ስሕተቶችን ማንሳት ይቻላል አንደኛው መጽሐፍ ቅዱስን ድንጋጌ ማሻሻል ይቻላል ወይ የሚለውን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነት ጸያፍ ተግባር መሆኑን መዘንጋታቸው ነው፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ድግጋጌ ይሻሻላል ወይ?

መጽሐፍ ቅዱስ ስንል ከቃሉ አንደምንረዳው ቅዱስ(ልዩ ንዑድ ክቡር) የሆነ መጽሐፍ ማለት ነው፡፡ የሚያነቡትን የሚቀድስ ሰውን ሁሉ ወደ ቅድስና ስለሚመራ የጻፉት ቅዱሳን በመሆናቸው እራሱ ባለቤቱ የቃሉ ተናጋሪ ቅዱሱ እግዚአብሔር በመሆኑ ቅዱስ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ይህን መጽሐፍ ታዲያ ማንም በዘፈቀደ እንዲሁ የሚጨምርበት ወይም የሚቀንስበት አይደለም፡፡ (ራዕ 22፥19) ይህን መጽሐፍ የጻፉም ቅዱሳን ከራሳቸው አፍልቀው አውጥተው አውርደው በሥጋዊ ደማዊ እውቀት የደረሱት አይደለምና ይልቁንም በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የተጻፈ ነው እንጂ(2ኛ ጴጥ 1፥21) ስለሆነም በሙሴ ትዕዛዝ መኖር እንጂ ማሻሻል ከቶም አይቻልም፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ያጻፈው ቅዱሱ እግዚአብሔር ነው ሙሴ በጌታ ዘመናትን አሻግሮ ማየት ይቻለዋል በዚህ ዘመን ያለውን ሁሉ አስቀድሞ ማየት ይቻለዋል ትዕዛዛቱም ዘመን የማይሽራቸው ዘመን ተሸጋሪዎችናቸው፡፡ ራሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም ብሎ አስተምሮናልና፡፡(ማቴ 5፥18)

ግብረ ሰዶማዊነት ጸያፍ ተግባር መሆኑን

የመጀመርያዎቹ ግብረ ሰዶማዊያን ሕዝቦች ሰዶምና ጎመራ ናቸው፡፡ (ዘፍ 19፡24-25) ይህን ጸያፍ ተግባርም በመፈጸማቸው እግዚአብሔር ከሎጥና ቤተ ሰቡ ውጭ ያሉትን አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህ ተግባር ታዲያ ዳግመኛ ከጌታችን ልደት በኋላ አቆጠቆጠ፡፡ ይህንንም ድርጊት እስከዛሬ ድረስ አንዳንዶች ሲያወግዙት አንዳንዶች ግን ችላ ብለውት ከግብራቸው ሲተባበሩ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ በጣም አስነዋሪው ነገር ቀስ በቀስ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ የእምነት ተቋማት ድርጊቱን መደገፋቸው ነው፡፡ ይህን ግብር እንኳን የሚያስብበት ልቡና የተሰጠው ሰው ቀርቶ እንስሶች እንኳን የማይፈጽሙት ጸያፍ እኩይ ተግባር ነው፡፡

ዮሐንስ በራእዩ በምዕ 21፡27 “ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም” በማለት እንደተናገረ ይህነን ርኩሰት የሚያደርጉ ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት የሚለዩ ናቸውና በዚህ ግብር(በውሸትም ጭምር) ውስጥ ያሉ ከዚህ ሰይጣናዊ መንፈስ ተለይተው ወደ ንሥሐ ሕይወት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ግብር የሚፈጽሙ ጊዜው ሳያልፍባቸው በንሥሐ ከእግዚአብሔር ጋር በዕንባ ሊታረቁ እንዲገባቸው ከማስተማር ይልቅ ይህን መደገፍ ከኃያሉ እግዚአብሔር ከእውነተኛ አምላካችን መጣላት ነው፡፡ ጳጳሱም እንኳን ግብረ ሰዶማዊነት የእሳቸውም ከእግዚአብሔር ተነግሮኛል ያሉት ቅጥፈት ጭምር (እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አባባል) ጸያፍ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባቸው ነበር፡፡በዚህ ተመሳስለህ ኑር ግብራቸው እግዚአብሔርን በእጅጉ አሳዝነውታል፡፡ ከጌታም ጋር መታረቅ ይገባቸዋል፡፡

ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር በምንሰማ ሰዓትም አብዝተን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይገባናል፡፡
ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment