Thursday, 5 January 2017

ዓለም አቀፍ ጉባኤያትና አብያተ ክርስቲያናት


 ኦርቶዶክሳዊ ቅኝት

                                      
ጉባኤ ኒቅያ
የአርዮስ ኑፋቄ

 

ወልድ ባልነበረበት ጊዜ አብ ነበረ አብ ወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገው ይህም መለት እግዚአብሔር አብ ወልድን እንደማንኛውም ፍጥረት ፈጥሮታል በኋላም ሥልጣን ስለሰጠው ፈጥሮ ፈጥሮበታል ብሎ አስተማረ፡፡

ፈጥሮ ፈጠረበት?
ለዚህ ትምህርቱ መነሻ የሆነው ኃይለ ቃል ምሳ 826 ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ መቅድመ ኩሉ ተግባሩ ጥበብ ከፍጥረታት ሁሉ እስቀድሞ እኔን ፈጠረችኝ በማለት ጥበብ የተባለ ወልድ ነው ብሎ አስታማረ
የአርዩስ ትምህርት የተቀዳው ከማን ነው?
አርዩስ ትምህርቱን የቀዳው ከፈላስፎቹ አፍላጦንና አሪስጣጣስ ሲሆን እነዚህ ፈላስፎች ዓለም የተፈጠረው በራሱ በእግዚአብሔር በቀጥታ ሳይሆን እግዚአብሔር  በፈጠራቸው መናፍስት ወይም ኃይሎች አማካኝነት ነው ብለው አስተምረዋል፡፡ ይህን ትምህርት አርዮስ አዲስ ቅርጽ በማስያዝ መናፍስት ያሏቸውን ክብር ይግባውና ወልድ ነው በማለት የእነዚህን ‹‹ፈላስፎች›› ትምህርት መጽሐፋዊ በማድረግ ብዙዎችን አስቷል፡፡
የአባቶች መልስ
አባቶቻችን ጸሎተ ሃይማኖትን እስከ ሰባተኛው አንቀጽ ድረስ የነገጉት በዘህ ጉባኤ ላይ ነው ይህም ፍጹም መጽሐፋዊና ለመሠረተ እምነታችንን ማሳያ ነው፡፡
j0293236ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር እናመናለን
ሰማይና ምድርን የፈጠረ የማይታየውንና የሚታየውን ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር የነበረ
አንድ የአብ ልጅ በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን
ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ
የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በባሕርዩ ከአብ ጋር የሚስተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ
በሰማይም በምድርም ካለው ያለእርሱ ምንም ምን የሆነ የለም
ስለእኛ ስለሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ
በመንፈስ ቅደስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ
ደግሞ ስለእኛ ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ
በቅዱሳን መጻሕፍት እንደተጻፈ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ
ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን
ለመፍረድ በምስጋና ይመጣል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም፡፡j0293236


ይህን የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል ጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሲጠቀሙት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት(ከግሪካዊያን ውጪ) ካቶሊካዊያን እናምናለን በሚለው ፈንታ አምናለሁ ብለው ቅርጹን ቀይረው ይጠቀሙበታል፡፡ሌላው ልዩነት ከአብ የሰረጸ የሚለውን ካቶሊካዊያኑ ከአብና ከወልድ የሰረጸ ብለው ቀይረውታል፡፡

አባቶች ከአርዮስ ትምህርት በተጨማሪ ከዚህ በተጨማሪ 20 ቀኖናዎች ተንግገዋል፡፡


ጉባኤ ኒቅያ

ጉባኤ ቁስጠጥንጥንያ


በጉባኤው ላይ ትምህርታቸው የተወገዘባቸው መናፍቃን
አቡናርዮስ ዘላዞቅያ ክህደት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት የሥጋ በሆነች ነፍስ ብቻ ተተክቶ ሕማምን ስቅለትንና ሞትን ከሥጋ ጋር ተቀበለ ይላል፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም መንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው ወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው  አብ ከሁሉ ትልቅ ነው ብሎ አስተምሮል፡፡[1]
የአባቶች መልስ
ጌታ ነፍስ ያላተዋሐደው ነው ወይም በነፍስ ፈንታ መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሐደ ማለት የቤተ ክርስቲያንን የነገረ ድኅነት ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ነፍስ የሌለውን ሥጋ ተዋሕዶ እንዴት የሰው ነፍስን ሊያድን ይችላል ብለው ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡
በሥላሴ መካከል መበላለጥ አለ የሚለው ትምህርት በጉባኤ ኒቅያም ጭምር የተወገዘ ነው፡፡ የጉባኤ ኒቅያ ትምህርት የሆነው ጸሎተ ሃይማኖት ‹‹ከአብ ጋር የሚተካከል ›› የሚለውን አንቀጽ የሚያነብ ሰው በቅድስት ሥላሴ መካከል የሥልጣን ልዩነት እንደሌለ በጉልህ ይረዳል፡፡ ይህ የአባቶች ትምህርት መጽሐፋዊ ሲሆን የመናፍቁ የአቡሊናርዮስ ትምህርት ግን የመጽሐፍ ማስረጃ የሌለው ተራ ክህደት ነው፡፡
የአውሳብዩስ ትምህርት
 እንደሰባርዩስ ትምህርት ሦስቱ አካላት በተለያዩ ሁኔታዎች የተገለጡ ናቸው፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምንለው ሦስቱ አካላት በተለያዩ ሁኔታዎች መገለጥ ነው እንጂ የተለያዩ አካል ያላቸው ሆነው አይደለም፡፡ ይህን ትምህርት በመቅዳት በኦሪት እንደ አብ በሐዲስ እንደ ወልድ በዘመነ ሐዋርያት ደግሞ እንደ መንፈስ ቅዱሰ የተገለጠው አንድ ነው የአካል ሦስትነት የለውም ብሎ አስተማረ፡፡[2]
ይህም ተራ ፍልስፍና ነው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፍጽም መልክ ፍጹም ገጽ ፍጽም አካል ያላቸው መሆኑን በሚያመለክት ሁኔታ በማቴ 317 በተለያየ አምሳል በዩርዳኖስ ወንዝ ስለወልድ መመስከራቸው ምስክር ነው፡፡(1 ዮሐ 512)
የመቅዶንዩስ ትምህርት
ይህን ትምህርት ያሰራጨው መናፍቅ የአርዩስ ትምህርት ደጋፊ ነበር፡፡ ጌታችንን የካደውን አርዩስን የሚከተል ሰው መንፈስ ቅዱስን ቢክድ አይደንቅም፡፡ እንዲህም ብሎ ያስተምር ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታቱ ሁሉ የተሰራጨ የእግዚአብሔር ፍጡር ነው እንጂ በአብና በወልድ ደረጃ ያለ አይደለም በመላእክት መልክ ተፈጥሮ ከመላእክት  ከፍ ያለ ነው ብሎ አስተማረ፡፡[3]
አባቶቻችን የመቅዶንዩስን ትምህርት በማውገዝ የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል ላይ ተጨማሪ ስለመንፈስ ቅዱስ የሚያወሱ ክፍሎችን ጨምረዋል፡፡ ይህ ምንፍቅና ተራ ፍልስፍና እንጂ መጽሐፋዊ አይደለም፡፡(1 ዮሐ 512)
የኤፌሶን ጉባኤ
በጉባኤው ላይ ትምህርታቸው የተወገዘባቸው መናፍቃን
ቢላግዩስ
የዚህ ሰው ክህደት የአዳም ኃጢአት ለልጆቹ አልተላለፈም፡፡ አንድ ሰው በሚወልድ ጊዜ ኣዳም ከኃጢአት ከመውቁ በፊት እንዳለ ሆኖ ይወለዳል፡፡በዚህም አንድ ሰው ወደ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ የሚደርሰው የእግዚአብሔርን እርዳታ ሳይጠይቅ ነው ብሎ አስተማረ፡፡[4]
ይህ ትምህርት የምሥጢረ ድኅነትን ትምህርት ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ አምላክ ሰው ስለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ መልስ ለመመለስ ይቸግረናል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ከኃጢአት ነጻ ሆኖ ይወለዳል ብሎ ያስተምራልና
መጽሐፍትም ይህን ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ ይመሰክራሉ፡፡(መዝ 513 ሮሜ512 1 ቆሮ 1522)
ንስጥሮስ[5]
የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በፊት ነበረ መሆኑን አምናለሁ ማርያም የእምላክ እናት ነች የሚለውን አባባል ግን አላምንም፡፡ የክርስቶስ እናት መሆኗን አልክድም ነገር ግን እናትነቷ ለትስብእት ነው፡፡ ማርያም እግዚአብሔርን አልወለደችም ነገር ግን ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው፡፡ ፍጡር ሆና የወለደችው የእግዚአብሔር መሳርያ ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ጌታችን ሁለት ጠባይ ሁለት አካልና ሁለት ፍቃድ አለው፡፡ ሰብአ ሰገል ለጌታ መስገዳቸው አግባብ አይደለም ምክንያቱም ሕጻኑ ኢየሱስ ገና መለኮት ያልተዋሐደው ሥጋ ነውና፡፡(ማቴ 211)[6]
የአባቶች መልስ
j0293236j0293236ቅዱስ ቄርሎስ አባታችን እመቤታችን ወላዲተ አምላክ መባል እንደሚገባት አምላክንም እንደወለደች በጉባኤው ላይ አብራርቶል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ የከበረ ያለመለወጥ ያለመከፈል ያለኅድረት ሥጋና መለኮት መዋሐዳቸውን አንዱ የአንዱን ባሕርይ ገንዘብ ማድረጉን በስፋት አስተማረ፡፡ ሁለት ፍቃድ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል የሚለው የንስጥሮስ ትምህርትም በዚህ ጉባኤ ተወግዞል፡፡

የኬልቄዶን ጉባኤና የአባቶች ተጋድሎ
የአውጣኪ ክህደት
አውጣኪ የንስጥሮስን ትምህርት ከመጥላቱ የተነሳ ወደ ስሕተት የገባ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ትምህርቱ አንድ ባሕርይ አንድ አካል ነው ቢልም በመጠፋፋት አንድ ሆኑ ብሎ ያስተምር ነበር፡፡ በዚህ ትምህርቱ ምክንያት በፍላፕያኖስ መጀመርያ (በሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ) ቀጥሎም በቅዱስ አባታችን ዲዮስቆሮስ አማካኝነት ትምህርቱ የተወገዘ ነው፡፡
ሁለተኛው የኤፌሶን ጉባኤ 449 . የአውጣኬን ትምህርት ለማውገዝ የተደረገ ነው፡፡በፍላፕያኖስ ዘቁስጠንጥንያ እንደተለመደው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሳይጠራና ኤጵስ ቆጶሳትን ሰብስቦ 431 አወገዛው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ፍላፕያኖስ ሁለት ባሕርይና ሁለት ፍቃድ አለው ከሚሉ ሰዎች በመሆኑ በችኮላ በመሆኑ ዳግመኛ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ 449 ኤፌሶንን ጉባኤ አደረገ ነገር ግን አውጣኪ አንድ ባሕርይ በመጠፋፋት ካለው ትምህርት ለጊዜውም ገሸሽ ብሎ እምነቴ የሠለስቱ ምዕትና የቅዱስ ቄርሎስ ነው በማለቱ ከእስራቱ ፈትውታል፡፡ በኃላ ላይ ግን ይህን ትምህርት መልሶ በማስተማሩ ዳግመኛ ተወግዞል፡፡[7]

የልዩን ክህደት
የልዩን ጦማር ወደ ፍላፕያኖስ(ፍላብያኖስ)
የልዩን ጦማር ፍጽም ክህደትና የንስጥሮስን ትምህርት በመድገም ዳግመኛ የአባቶቹን ድንበር ያፈረሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ጦማሩን የተመለከተው ንስጥሮስም የክህደቱ ትምህርት ስለሰመረለት የሮምን ቤተ ክርስቲያን አወድሶል፡፡ ጦመሰሩ በአጭሩ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ ሁለት ሕላዌ አንድ አካል አለው የሚል ነው፡፡ በልዩን ፍልስፍና አካልና ባሕርይ የተለያዩ ናቸው የሚል ነው፡፡
አባቶቻችን ከአካል የተለየ ባሕርይ የለም ከባሕርይ የተለየ አካል የለም ብለው አስተምረውናል፡፡ ከአካል የተለየ ባሕርይ ከሌለ ደግሞ ሁለት ባሕርይ ካልን ሁለት አካል ወደሚል ትምህርት ይወስደናል፡፡ ይህ ትምህርት ደግሞ የንስጥሮስ ትምህርት ነው ይህ የንስጥሮስ ትምህርት ታዲያ ቀድሞ በአባቶቻችን በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘ ነው፡፡ወይም አካልን አንድ ካልን በባሕርይም አንድ ወደ ማለት ይመራናል ይህም እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ነው፡፡ ሁለቱ ባሕርያት በመተባበር የየራሳቸውን ድርሻ ይሰራሉ ‹‹መለኮት ይገብር ግብረ መለኮት ትስብእት ይገብር ግብረ ትስብአት›› የሚል ጦማር ነበር፡፡ይህም ጦማር ተአምራት ያደረገው መለኮት መከራን የተቀበለው ሥጋ ብሎ ያስተምራል፡፡
የኬልቄዶን ጉባኤ የተሳታፊዎች ቁጥር 636 ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት ከቀድሞ ጉባኤያት ሁሉ ታላቅ ጉባኤ ለማስመሰል ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ከዚህ በፊት የንስጥሮስን ትምህርት በመደገፋቸው ምክንያት የተወገዙ ሰዎች ጭምር የተሳተፉበት በመሆኑ በአባቶች ዘንድ ግርታን ፈጥሮል፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም የእስክንድርያን አብያተ ክርስቲያናትን ወክሎ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ የጉባኤያቱ አባላትም ተቃውሞ አጸኑበት ተከሳሽም አደረጉት የአውጣኪ ትምህርት ደጋፊ ነህ ውጣ አሉት፡፡ ቅዱሱም መንበሩን ለማስከበር ሲል ወጣ ይህንን የአርመን የሕንድና የሶርያ አብያተ ክርስቲያናት ተቃወሙ፡፡ ግሪኮቸቹና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ግን ከምሥራቃዊያኑ ጋር ተባበሩ፡፡
የልዮን ጦማር ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች
*      ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው በኃላም ሰው ሆኖ ተገለጠ
*      መለኮትና ሥጋ በእርሱ ውስጥ ተገናኙ ያለመቀላቀል በእርሱ ውስጥ ይኖራሉ
*      እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል ማለት መለኮት የመለኮትን ትስብእት ትስብእትን ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡
*      የሁለቱም ባሕርያት ሀብት ለአንዱ አካል በእኩልነት ይገኛሉ
*      ከመዋሐድ በፊት ሁለት ነበሩ ከተዋሐዱ በኃላ አንድ ናቸው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ተገናኙ   ተራከቡ አብረው ይኖራሉ?
ይህ ትምህርት ለተዋሐዶ ትምህርት ጸር ይሆን ዘንድ በንስጥሮስ የተቀመመ ክህደት ነው፡፡እነዚህ ቃላት የአማላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መሆን አመልካች አይደሉም፡፡ ጽምረት ነው እንጂ እንደዳዊትና ማኅደሩ ኅድረት ተዋሕዶ ግን እንደነፍስና ሥጋ ነው፡፡
የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል?
ተዋሕዶ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ሥጋም የመለኮትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ብላ ታስተምራለች፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም እንደሚል‹‹ እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሃ ለሥጋ ኮነ ለቃል›.
አንዳንድ ጊዜ እንደሥጋ አንዳንድ ጊዜ እንደመለኮት ይሰራል ብሎ የሚከፍለው ልዩን በአንድ ጊዜ የአምላክነትና የሰውነት ሥራ አይሰራም ብሎ በመልእክቱ አስቀምጦል፡፡ እኛ ግን ሥግው ቃል መከራን ተቀበለ ሞተ ተነሳ ተአምራት አደረገ ተራበ ተጠማ እንላለን ይህም የአባቶቻችን ትምህርት ነው፡፡
ተዋሕዶን ያስተማሩ አባቶች
ከኬልቄዶን ጉባኤ በኃላ ለሚቀጥሉት 150 ዓመታት ያህል የነገሡ የቁስጥንጥንያ ነገሥታት ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ለማዋሐድ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ በሮም ቤተ ክርስቲያን ጣልቃ ገብነት ሳይሳካ ቀረ፡፡አጋግዩስ ብርቱ ጥረት የአንጾክያና የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ለስምምነት የሚያበቃቸውን ስምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡
ሳዊሮስን የመሰሉ ፊልክስዮስን የመሰሉ በአንጾክያና በሶርያ ተዋሕዶን የሰበኩ አልታጡም፡፡ ይህም የአባቶችን ተጋድሎ አመርካች የታሪከ ገጽ ነው፡፡
ጉባኤ ቁስጥንጥዮስ ሁለተኛ
ይህ ጉባኤ በዋነኝነት በጉባኤ ኬልቄዶን የተወሰነውንና በቅዱሳኑ በጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ልዩነት የፈጠረውን ትምህርት ማለትም በእነሱ አጠራር ሞኖፈስትስ (ይህም በእነሱ አረዳድና ትርጉም የአውጣኪን ትምህርት ማለትም ተዋሕዶ በመጠፋፋት የሚለውን ትምህርት የሚወክል ነው) ለመቃወም ካቶሊካዊያኑና የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ነው፡፡[8]
ለመሆኑ ሞኖፈስርስ ዳዩፈስቲስ ምንድን ነው?
ሞኖፊሲትስ (Monophysitism)  
ሞኖፊሲትስ ማለት በውላጤ የተገኘ አንድ ባሕርይ ይህ ስም ተዋሕዶን የሚገልጥ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ተዋሕዶ ስንል ያለ መጠፋፋት ተዋሐዱ አንዱ የአንዱ ባሕርይን ያለመለወጥ ያለፍልጠት ያለኅድረት ያለሚጠት ተዋሐደ ብለን እናስተምራለንና ነው፡፡ ይህ ትምህርት ግን የአውጣኪን ክህደት በትክክል የሚገልጥ ቃል ነው፡፡
ዳዩፊሲስትስ ይህ በትክክል የንስጥሮስን ክህደትና የልዩንን የፍልስፍና ትምህርት የሚገልጥ ነው ፡፡ የንስጥሮስ ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል ሁለት ሕላዌ አለው ስለሚል ዳዩፊሲስትስ ነው የልዮንም ሁለት ባሕርይ ስለሚል ዳዩፊሲስትስ ብለን መጥራት እንችላለን፡፡
ይህን ጉባኤ ማድረግ የተፈለገበት ምክንያት የተዋሕዶ አርበኞች ተዋሕዶን በማስተማር ስለበረቱና በክርስትናው ዓለም ተዋሕዶ እየታወቀ እየተረዳ ስለመጣ በዚህ ምክንያት ካቶሊካዊያኑ የኬልቄዶን ጉባኤን አንደ ሕጋዊ ጉባኤ በመቁጠር የጉባኤውን ሐሳብ ለማጽናት ነው፡፡
ተዋሕዶ ከአውጣኪ ትምህርት ጋር ያለው ልዩነት
ጥንታዊያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አውጣኪን ቁጥሩ ከመናፍቃን እንጂ ከቅዱሳኑ ተርታ አላኖሩትም፡፡ ትምህርቱም በቅዱስ አባታችን ዲዮስቆሮስ አማካኝነት የተወገዘ ነው፡፡ [9]
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስትል
እንበለ ዉላጤ(ያለ መለወጥ)
ዉላጤ ስንል ሥጋ ወደ መለኮት መለኮት ወደ ሥጋነት መለወጥ ማለታችን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናገኛቸው ታሪኮች የመለወጥን ትርጉም ለመረዳት ምሳሌ እንጥቀስ የሎጥ ሚስት ወደ ጨው አምድነት(ዘፍ 1926) መለወጥ የቃና ዘገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅነት (ዮሐ 21-3) መለወጥም ፍጹም ባሕርውን ለቆ አዲስ ወደ ሆነ ባሕርይ መለወጡን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ለተዋሕዶ ግን እንዲህ አይደለም፡፡
መለኮት ወደ ሥጋነት ተለወጠ ካልን መለኮት ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህም ነገረ ድኅነቱን ከንቱ ያደርገዋል ምክንያቱም የሰው ልጅ በፍጡር ደም አይድንምና በፍጡር ደም ቢድን ኖሮ ቀድሞ በዳነ ነበር፡፡ ሥጋ ወደ መለኮትነትም ተለወጠ ብንል ዓለም አልዳነም ወደሚል ሐሳብ የሚመራ ነው፡፡ መለኮት በባሕሪው ሊዳሰስ ሕማም ሊቀበል ወደ መቃብር ሊወርድ አይችልምና፡፡በተዐቅቦ(በመጠባበቅ) አንድ ሆኑ እንጂ መለኮት የሥጋን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ ሥጋም የመለኮትን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ
እንበለ ሚጠት(ያለመመለስ)
ይህም ዉላጤ ባሕርይው ከነበረበት ሁኔታ ከተቀየረ በኃላ መልሶ ወደ ቀድመ ግብሩ(ባሕርይው) ሲመለስ ሚጠት ይባላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የሙሴን በትር እንደምሳሌ ብናነሳ ወደ እባብነት ተለወጠ በኃላ መልሶ በትር እንደሆነው ሁሉ ለመለኮትና ለሥጋ እንዲሁ ነው ብሎ ማስተማር ሚጠት ይባላል፡፡
እንበለ ኅድረት
ይህ ትምህርት የተወገዘው የንስጥሮስ ትምህርት  ነው፡፡ ዳዊት ከማኅደር ሰይፍ ከሰገባው እንደሚያድር በማርያም ልጅ በኢየሱስ ላይ አምላክ አደረበት በማለት የስህተት ትምህርት አስተምሮል ይህ ኅድረት ይባላል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተዋሕዶ ስትል ከዚህ የሚለይ ነው፡፡ ይህ ባሕርይን ለሁለትለመክፈል የተመቸ ነው ይኸውም ዳዊት ከማህደሩ ቢቀመጥ ማኅደር እነደማይባል ሁሉ ኢየሱስም የሰው ልጅ እንጂ አምላክ አይባልም እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህም አምላክ ወሰብእ (ፍጹም ሰው ፍጹም)ማለት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ይህን የስሕተት ትምህርት በጉባኤ ኤፌሶን የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡
እንበለ ቱሳሔ(ያለመቀላቀል)
ቱሳሔ የአውጣኪ ትምህርት ነው ይህ ሰው በአካልም በባሕርይም አንድ ነው ብሎ ቢያስተምርም ነገር ግን በመቀላቀል በመደባለቅ ነው የሚል ነው፡፡
መለኮት ግን ምንም ቱሳሔ ሳይኖርበት ከእመቤታችን የነሣው ሥጋ ባለው አጽንቶ የፍጡር ልቡና መርምሮበማይደርስበት ግብረ አምላካዊ ጥልቅ በኾነ ምሥጢር(በመሆን) ተዋሕደው እንጂ በመቀላቀል እንደወተትና ቡና ተቀላቅለው በመካከላቸው ሌላ ነገርን ያስገኙ ወይም የተጠፋፉ አይደሉም
   ወይም እንደ ትድምርት ያለ(በመደራረብ) እንደ ልብስ እንደእንጀራ ዓይነት ባለሆነ ወይም እንደቡዐዴ(ማዋሐድ ማያያዝ ተቃርቦ ተላስቆ) እንደእንጨትና ብረት ባልሆነ እንደነፍስናሥጋ በኃላ መለያየት ያለው ያለ ፍልጠት በተዋሕዶ ከበረ እንላለን፡፡[10] የጥንታዊያን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እምነታቸው ይህ ነው፡፡

ጉባኤ ቁስጥንጥዮስ ሦስተኛ

ይህም ጉባኤ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ዳግመኛ የተወያየ ጉባኤ ነው፡፡ በካቶሊካዊያኑ አነጋገርና አጠራር ሞኖፈስትስ (ይህም በእነሱ አረዳድና ትርጉም የአውጣኪን ትምህርት ማለትም ተዋሕዶ በመጠፋፋት የሚለውን ትምህርት የሚወክል ነው) አውጣኪያዊ ነው በማለት ውሳኔውን አጽንተዋል፡፡ ተዋሕዶን ፍጹም ያልተረዱት ካቶሊኮችና በወቅቱ የነበሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ድዩፈስትስን(ምንታዌነትን) አጸኑት፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ታሪካዊ ስሕተት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡[11]
ሁለተኛው የኒቂያ ጉባኤ
ይህ ጉባኤ ከሌሎች ጉባኤያት አንጻር መሠረተ እምነት ላይ ያጠነጠነ አልነበረም፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ የጌታችንንና የቅዱሳን አሳሳል ጥበብን በተመለከተ አብያተ ክርስቲያናቱ መከተል ያለባቸውን ዘይቤ በሚመለከት የተወያየና ውሳኔ ያሳለፈ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ ግን ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያደረገችው የመጨረሻ ጉባኤ ነው፡፡ ከዚህ በኃላ የተደረጉትን ጉባኤያት በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደጉባኤ አይቀበሉትም፡፡[12]    
ስለቅዱሳን አጽምና ሥዕሎች የተሰነሱ ክርክሮችና ውዝግቦች
ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንና ማኅበረ ምዕመናን የክርስቶስን ልደቱን ስቅለቱን ትንሣኤውን ዕርገቱን እንዲሁም የቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲሁም ለክርስትናው መስፋፋት አስተዋጽዖ ያበረከቱ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሐዋርያነ አበው ሰባክያን ሰማዕታት ጻድቃን መነኮሳት በተለየ ክብር ስማቸው ይጠራል፡፡ ሥዕላቸው በቤተ መቅደስ ይሳላል በተለይ ታቦት በሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት አጽማቸው በልዩ ክብር እንደሥዕላቱ ሁሉ ይከብራል፡፡ ክርስቲያኖች ይህንን ተግባር ሲያደርጉ ለሥዕላቱም ሲሰግዱና ሲያከብሮቸው ያዩ አይሁድ እስላሞች ይህንን ድርጊት ከአምልኮ ስግደት ጋር በማያያዝና በመተንተን እጅግ ይቃወሙት ያዙ፡፡
ይህንን በሚመለከት በወቅቱ የነበረው የባዛንታይን ንጉሥ ልዩን ሣልሳዊ ስዕሎቹ እንዲወገዱ ትዕዛዝ አወጣ፡፡ ይህም ስለሁለት ምክንያት ነው አንደኛው ለሥዕል በመስገድ ሰበብ የጣዖት አምልኮ በክርስቲያኑ ዘንድ እንዳይስፋፋ በመስጋት ሲሆን ሁለተኛው የአይሁድና የእስላሞችን ክስ በማስወገድ ከእስላሞችና ከአይሁድ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር በማሰብ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ግን ከፍተኛ ውዝግብ አስከተለ አዋጁን ከተቃወሙት መካከልም የወቅቱ የባዛንታይን ፓትርያርክ አባ ጀርመኑስ ይገኙበታል በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከደም መፋሰስ ደረሰች፡፡ ይህን ለመፍታት ንጉሡ አዋጁን በጉባኤ ማጽደቅ እንዳለበት በማሰብ 730 . ስኖዶዩስ እንዲሰበሰብ አደረገ በዚህ ጊዜ ነበር ፓትርያርክ ጀርመኑን ንጉሡን ሐሳብ የገሰጹት  በዚህጉባኤ ነበር፡፡ በአባ ጀርመኑን ፈንታ የሥዕላት ተቃዋሚ ሌላ ፓትርያሪክ አባ አናስታስዩስ ተሸመ፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም የሮሙ ፖፕ ጎርጎርዩስ ሣልሳዊ ይህንን ሐሳብ አወገዘው፡፡
ሥዕላቱን ለማውደም የተሰጠራው ጉባኤ
ከልዩን ፈንታ ልጁ ቁስጥንጥንዩስ ተተካ እርሱም አባቱ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ 754 . 338 ጳጳሳትን  በማሰባሰብ ጉባኤ አካሄደ፡፡ይህም ጉባኤ የልዩንን ውሳኔ በማጽናት አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን ውሳኔ የማያከብር ሁሉ መከራ ጸናበት፡፡ በተለይ ጽኑ ተጋድሎ ያደረኩት መነኮሳት እጅግ መከራ ጸናባቸው፡፡ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጸረ ሥዕላት አቋም ያላቸው ሥዕላቱን በሚያከብሩት ላይ ሰቃይ አጸኑባቸው፡፡
በዚህም ምክንያት ነበር እንደሌሎች ጉባኤያት በመሠረተ እምነት ላይ መሠረት ያላደረገው ሁለተኛው የኒቅያ ጉባኤ በምሥራቅና በምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተደረገው ጊዜው 787 .. ነው፡፡ በጉባኤውም ዳግመኛ ለሥዕል ስግደት እንደሚገባ ተወሰነ፡፡
ውሳኔውም

1.   754 . የተካሄደውን የሥዕለ ተቃዋሚዎች ጉባኤ አወገዘ

2.   ለሥዕል ስግደት እንደሚገባ አረጋግጠው ወሰኑ

3.   ሥዕላቱ ጣዖታት ናቸው የሚለውን አወገዘ

4.   ለወንጌል ለመስቀል የሚሰጠው ክብር ለሥዕላቱም እንዲሰጥ ወሰነ

5.   በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን አጽም በክብር እንዲቀመጥ ተወሰነ

6.   በሥርዓቱ ወደ ዓለማዊ ተቋማት የተለወጡ ገዳምት ወደ ቀድሞ አገልግሎታቸው እንዲመለሱ ወሰነ[13]

ጉባኤ ቁስጥንጥንዩስ አራተኛ
የምሥራቅና የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል
ይህ ጉባኤ ለሁለቱ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል መፈጠር እንደመነሻ የሚታይ ነው ይህም በዚህ ጉባኤ ላይ የተነሳው የመንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሰረጸ ነው የሚለው ትምህርት ነው ይህ ትምህርት ከዚህ በፊት ያልነበረ ስርዋጽ ነውና ይህን በመቃወም የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሮም ቤተ ክርስቲያን ፖፕን ወቀሱ መናፍቅ ነህም አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጉባኤው ተደረገ የሮም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነችና የእኛ ሐሳብ ያደመጥ አለች ይህንን ምሥራቃውያን ተቃወሙት ፓፕ ኒኮላስም በዚህ ጉባኤ ላይ የስሕተት ትምህርቱን አጸደቀው፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እስካሁን ድረስ ዘሰረጸ እምአብ ወእም ወልድ ብለው ያስተምራሉ፡፡[14]
መለካዊያኑ በቅድመ ስማቸው የቀጠሉ ሲሆን 1054 .. ከምዕራባዊያኑ ካቶሊካዊያን ተገንጥለዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በዋነኝነት ካቶሊካዊያኑ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሰረጸ ነው የሚለውን ትምህርት በማስተማራቸው ይህንንም የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን በመቃወሟ ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሁሉት ባሕርይ የሚለውን ትምህርት የሚቀበሉ በመሆናቸው ከጥንት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በመሠረተ እምነት ደረጃ ልዩ ብያደርገንም በነገረ መለኮት አረዳድ ባሕል ግን በብዙ የምንቀራረብ ነን፡፡
በምሥራቅ ኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያሉ ስምምነቶች
*      ሁለቱም አብያተ ክርስቲያንት ስለመንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሰርጻል ከሚለው የካቶሊካዊያንና የምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊያን ልዩነት 21 የካቶሊክ ጉባኤያት 7 መቀበላቸው
*      ትልቁ ለውጥ(ፕሮቴስታንቶች) የሚቀበሏቸውን የመካከለኛው ዘመን ዶግማዎች ሁሉሁለቱም ይቀበሏቸዋል
*      የቤተ ክርስቲያን ባሕልና ትውፊት ከመጻሕፍት ጋር የመሠረተ እምነተ ምንጮች ናቸው
*      ለእመቤታችንንና ለጻድቃንና ለሰማዕታት መስገድ እንደሚገባ ያምናሉ አማላጅነታቸውንም ይቀበላሉ
*      ለጽድቅ አምነትና መልካም ሥራ ያስፈልጋል ብለው ያለምናሉ
*      ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሰባት ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አላቸው፡፡ በሥርዓተ አፈጻጸም ላይ ግን በሜሮንና በቀንዲል ላይ ልዩነት አላቸው
*      ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በቅዳሴ ጊዜ ኅብስቱ ወደ ቅዱስ ሥጋው ወይኑ ወደ ክቡር ደሙ እንደሚለወጥ ያምናሉ
*      በምሥጢረ ክህነት የክህነት ደረጃዎች 1. ዲቁና 2. ቅስና 3. ጵጵስና ብለው በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ይከፈላሉ፡፡
*      ሁለቱም ገዳማት አሏቸው
*      መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት ሁለቱም 66 በተጨማሪ ሁለተኛ ቀኖና(Deuterocanonical) መጽሕፍትን ይቀበላሉ

በምሥራቅ ኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያሉ ልዩነቶች
የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያት
የምዕራብ(የካቶሊክ) ቤተ ክርስቲያን
*      የመንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሰረጸ ነው የሚለው ትምህርት ነው ይህ ትምህርት ከዚህ በፊት ያልነበረ ስርዋጽ ነውና ይህን በመቃወም የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሮም ቤተ ክርስቲያን ፖፕን ወቀሱ መናፍቅ ነህም አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጉባኤው ተደረገ የሮም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነችና የእኛ ሐሳብ ያደመጥ አለች ይህንን ምሥራቃውያን ተቃወሙት ፓፕ ኒኮላስም በዚህ ጉባኤ ላይ የስሕተት   ትምህርቱን አጸደቀው፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እስካሁን ድረስ ዘሰረጸ እምአብ ወእም ወልድ ብለው ያስተምራሉ፡፡ (the filioque in the creed, which referred to the Holy Spirit emanating from God the Father and the Son.)
*                  መንፈስ ቅዱስ ዘሰረጸ እምአብ ወእም ወልድ ከአብና ከወለድ የሰረጸ ነው  ብለው ያምናሉ
*                   የፖፑ የበላይነት
ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያ ነው የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉም፡፡ በሐዋርያት መካከል የሥልጣን ልዩነት የለም የሚል አቋም አላቸው፡፡ማር 935-36 ሮምም የሁሉ የበላይ አድርገው አይወበሉም[15]
*                  የፖፑ የበላይነት
ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያ ነው የሚለውን ሐሳብ በመያዝ እንዲሁም ጥቅሶችን ጭምር በመግለጽ ሮምና የሮሙ ፖፕ ከሁሉ አብያተ ክርስቲያናት የበለይ ነው ብለው ያስተምራሉ
*                  ፖፑ አይሳሳም አይባልም
*                  የፓፑ የማይሳሳት መባሉ(The infallibility of the pop)
*                  እመቤታችን ጥንተ አብዞ አለባት
*                  እመቤታችን ጥንተ አብሶ የለባተም[16]
*                  ቀሳውስትና ዲያቆናት ሊያገቡ ወይም ላያገቡ ይችላሉ
*                  ቀሳውስትና ዲያቆናት በድንግልና ሕይወት መኖር አለባቸው
*                  ሥጋና ደሙን ያቀብላሉ
*                  ሥጋውን ብቻ እንጂ ደሙን አያቀበሉም
*                  ቅዱስ ቁርባንን ለማዘጋጀት ከቦካ ኅብስት ነው
*                  ቅዱስ ቁርባን ለማዘጋጀት ያልቦካ ኅብስት ይጠቀማሉ



[1] የአቡሊናርዩስ ትምህርት
[2] የአውሳብዩስ ትምህርት
[3] የመቅዶንዩስ ትምህርት
[4]የቢላጊዩስ ትምህርት
[5] The Council of Ephesus proclaimed the Virgin Mary as the Theotokos (Greek Η Θεοτόκος, "Mother of God").
[6] የንስጥሮስ ትምህርት
[7] ይህን ጉባኤ ልዮን የሮም ፖፕ ጉባኤ ፊያት(የወንበዴዎች ጉባኤ) ብሎ ጠራው የእርሱ መልክተኞች ስላልተሳተፉ
[8] The Council again dealt with the issue of the two natures of Christ, as monophysitism had spread through Christianity despite the decisions of Chalcedon. The Council met from May 5 until June 2, 553 in eight sessions during the pontificate of Pope Vigilius,
[9] ዳግመኛ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ 449 ኤፌሶንን ጉባኤ አደረገ ነገር ግን አውጣኪ አንድ ባሕርይ በመጠፋፋት ካለው ትምህርት ለጊዜውም ገሸሽ ብሎ እምነቴ የሠለስቱ ምዕትና የቅዱስ ቄርሎስ ነው በማለቱ ከእስራቱ ፈትውታል፡፡ በኃላ ላይ ግን ይህን ትምህርት መልሶ በማስተማሩ ዳግመኛ ተወግዞል፡፡
[10] በትምህርተ ሃይማኖት ምሥጢረ ተዋሕዶን በሚገባ ከልስ
[11] The Council repudiated Monothelitism, and reaffirmed that Christ, being both human and divine, had both human and divine wills.
[12] ይህ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት ቁጥር 7 ሲሆን እንደዓለማቀፋዊ ጉበኤ ግን 2ቱን ብቻ እንደምትቀበል አንዳንድ መዛግብት ይጠቁማሉ
[13] የእግዚአብሔርመንግስት ታሪክ በምድር ላይ(ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ) ሁለተኛ መጽሐፍ ቀሲስ / ምክረ ሥላሴ /አማኑኤል 2002 . ገጽ 131 ምዕራፍ ስድስት
[14] but it also led to a schism, because the emperors and patriarchs of Constantinople interpreted themselves as the true descendants of the Roman Empire dating back to the beginnings of the Church.Pope Nicholas I had refused to recognize Patriarch Photios I of Constantinople, who in turn had attacked the pope as a heretic, because he kept the filioque in the creed, which referred to
The Council met in ten sessions from October 869 to February 870 and issued 27 canons.
[15] በኬልቄዶን ጉባኤ በቀኖና 28 ላይ ሮም የበላይ መሆኑን ቢስማሙም ቅሉ ይህ ግን የክብር ነው ብለው ይተረጉምታል፡፡
[16] ጥንተ አብሶ ተብሎ የሚታወቀው ስምና ጽንሰ ሐሳብ በተብራራ መልኩ የገለጸው አጉስቲን የተባለው የካቶሊክ የነገረ መለኮት ሊቅ እመቤታችን ጥንት ስትጸነስ ጀመሮ የውርስ ኃጢያት የለበትም የሚል ነው ይህ የካቶሊካዊያኑ አባባል ግን ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ብለው የሚተቹት አሉ(በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በስፍት በሚቀጥሉት ምዕራፎች ይከታተሉ)

No comments:

Post a Comment