በዲ/ን ያሬድ መለሰ
ዛሬ የጽዋ ማኅበራት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱትን አስተዋጽዖና ችግሮች በተመለከተ ጥቂት ለማለት ወደድኩ ይህን ጽሑፍ በምታነቡበት ወቅት በእናንተ ሰብሳቢነት ወይም በአቅራቢያችሁ በሰፈራችሁ የሚሰበሰቡ በተለያየ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችን ልታስቡ እንደምትችሉ እገምታለሁ፡፡የጽዋ ማኅበራት ዓላማ
ጽዋ ማኅበራት ዓላማቸው ቅዱሳንን መዘከር ነው በቅዱሱ ስም ነዳይ ማብላት የተቸገረን መርዳት የቅዱሱን ገድል እያሰቡ(እየዘከሩ) መልካም ማድረግ ለድሆች መራራት ነው፡፡ ይህም መሠረቱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ቃል ላይ ነው ‹‹ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢዩን ዋጋ ይወስዳል ጻድቁንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል››ማቴ 10፡41 ብሎልና ማኅበራቱም ይህን በማሰብ በየወሩ ቅዱሱን እየዘከሩ ከቅዱሱ ረድኤት በረከት እንዲያገኙ ይማጸናሉ
እነዚህ ማኅበራት ከላይ ከጠቀስነው ዓላማ ጋር መጓዝ ሲገባቸው ከዚህ በተለየ መልኩ ሌላ ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ እየበረከቱ ስለመምጣታቸው ዕለት ዕለት የምንታዘበው ሐቅ ነው፡፡ ይህ ከሁለት ነገር ይመነጫል አንድ ከመሥራቾቹ የእውቀት እጥረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እያወቁ ከዓላማው ፈቀቅ ማለትን ነው፡፡ጽዋ ማኅበራቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማጥናትና አንዳች መፍትሄ መስጠት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡ለመሆኑ ችግሮቹ ምንድር ናቸው?
- መንፈሳዊ ዓላማ
ጌታችን አማላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር ስለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሲመሰክር ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ ምን ልታዩ መጣችሁ ብሎ የመጡበትን ዓላማ ሲያስታውሳቸው እናገኛለን፡፡(ማቴ 11፡7) ለመንፈሳዊ ሰው መንፈሳዊ ዓላማ ያስፈልገዋል፡፡ ያለመንፈሳዊ ዓላማ ወይም ተጨማሪ ዓላማ (3 ኛ ዮሐ 1፡19) አንግቦ መጎዝ ለመንፈሳዊ ሰው የሚገባ አይደለም፡፡ አንዱን ይመርጥ ዘንድ ግድ ነው፡፡ (ዮሐ 6፡ 67 ) ስለዚህም በቅድምያ ማኅበራቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ በግልጽ ማስቀመጥ በእርሱም መጓዝ ይገባቸዋል፡፡
- የጽዋ ማኅበራትን ትውፊት አለመጠበቅ
ሌላው ማኅበራቱ ላይ የምናየውና የምናስተውለው ችግር የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ትውፊት አለመጠበቃቸው ነው፡፡ ጽዋ ማኅበራት ሆነው ቢሰየሙም ቅሉ ነገር ግን አባቶቸ ባስቀመጡልን ትውፊት (ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የጽዋ ማኅበራት ትውፊት አላት) አይመሩም ይህም አብዛኞቱ ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበራቱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መመራት እንደሚገባቸው ማስረዳት ከሁላችን የሚጠበቅ ነው፡፡
- ለሌሎች ትምህርቶች ተጋላጭ መሆን
ከተለመዱ የተሐድሶ ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ ብዙ ውስጠ ወይራ የሆኑ የጽዋ ማኅበራትን መመሥረት፣ ጉባኤያትን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ እንዲካሄዱ እገዛ ማድረግ፣ በተቻለ መጠን የውስጥ ለውስጥ ሥራዎችን በይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ነው ፡፡ ይህ የጽዋ ማኅበራቱን ምን ያህል ለተሐድሶ ትምህርት ተጋላጭ እንደሚያረጋቸው አስተውሉ፡፡ ምክንያቱም መናፋቃኑ ውስጥ ለውስጥ በመሥራት ማኅበራቱን ወደ ማይፈልጉት ዓላማ እንደሚመራቸው ከቤተ ክርስቲያንም ጉያ እንደሚነጥሎቸው የታመነ ነው፡፡
አንዳንድ በጽዋ ማኅበራት ስም ራሳቸውን የሚጠሩ ነገር ግን ሌላ ዓላማ አንግበው በጽዋ ማኅበራት ከውጭ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የፕሮቴስታንት ተሐድሶን ትምህርት የሚያስተምሩ መናፋቃን እናዳሉ ሁሉ ምንም ሳያውቁ በመሠረቱት ጽዋ ማኅበር ሰባኪ በመምሰል ሰርጎ በመግባት የኛ ያልሆነን ትምህርት በማስተማር ማኅበሩን ወደ ምንፍቅና ሊወሰድ ይችላልና ተጋላጭነታቸው የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች በኩል መሥራት ይገባታል፡፡
- የዕውቀት እጥረት
አብዛኞቱ ማኅበራት ስለቤተ ክርስቲያን ጠለቅ ያለ እውቀት በሌላቸው ሰዎች የሚመሠረቱ ናቸው፡፡ ይህም የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ አንደኛ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አለማወቅ ሁለተኛ በቂ የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀት እጥረትና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር አለማወቅ በዚህም ምክንያት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር አብሮ ያለመሥራት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህንንም መቅረፍ የቤተ ክርስቲያኒቱ ድርሻ ነው ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች በኩል አለያም ሌላ የማስተማርያ መንገድ ለወጣቱ ማመቻቸት አለባት
- ጉዞ ላይ ብቻ አተኩሮ መሥራት
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቋቋሙ ማኅበራት ደግሞ ሌሎች መንፈሳዊ መንገዶችን በመርሳት መንፈሳዊ ጉዞዎችን ብቻ ላይ መሥራት ማኅበሩ ስለአባላት መንፈሳዊ ሕይወት ግድ ላይኖረው ይችላል፡፡ ጉዞው መደረጉ መልካም ነው ነገር ግን በዚህ ብቻ በመጠመድ መንፈሳዊ ሕይወታችንን መዘንጋት የለብንም፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment