Monday, 16 January 2017

ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሮሜ.፮፥፬



በዲ/ን ያሬድ መለሰ          
ከጌታችን መወለድ ሥድስት ወር ተቀድሞ የተወለደው የካህኑ ዘካርያስና የኤልሳቤጥ ፍሬ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ  ከምድረ በዳ ወጥቶ በዮርዳኖስ ዙርያ “መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ”እያለ በማስተማር የንስሐን ጥምቀት ማጥመቅ ጀመረ :: (ሉቃ ፫፥፩ ሉቃ ፫፥፫) ሕዝቡም ትምህርቱን በመቀበል ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በንስሐ ጥምቀት ይጠመቁ ነበር:: (ማቴ ፫፥፫) የትምህርቱን እውነተኛነት ባወቁ ጊዜ ዮሐንስን ክርስቶስ ነው ብለው ጠረጠሩ:: (ሉቃ ፫፥፲፭) ዮሐንስም እንዲህ ሲል እውነቱን ነገራቸው " እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ። የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።  ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤  እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ። በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።"(ዮሐ ፩፥፳) እውነት የሚናገር የእውነት ምስክር የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ ምስክርነቱ ድንቅም ጥልቅም ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ንባብ ስለራሱ ማንነትና ስለሚመጣው መሲህ ክርስቶስ ማንነት ስናገር ሲያነጻጽር እናገኛለን፡፡  እንዲህም ብሎ መሰከረት የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ ባሕርዩን እመረምረው ዘንድ የማይቻለኝ እርሱ ያጠምቃችሃል የእኔ ጥምቀት በማይ ነው የእርሱ ከዚህ ያይደለበመንፈስ ቅዱስ እሳት ያጠምቃል በጀ ብትሉ በመንፈስ ቅዱስ እንቢ ብትሉ በገሃነመ እሳት ያጠምቃችኃል ብሎ ስለ ጌታ መሰከረ፡፡
የዮሐንስን ጥምቀት ይጠመቅ ዘንድ ጌታችን ወደደ
በጌታ ሠላሳ ሲሞላው በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደነበረው የዮርዳኖስ ባሕር መጣ፡፡ ይህስ እንደምን ይደንቃል? እንኳን ሰማያዊ ንጉሥ ይቅርና ምድራዊ ንጉሥ አገልጋዩ ወደ እርሱ ይመጣል እንጂ ወደ አገልጋዩ አይሄድም፡፡ ይህን ግን መምህረ ትኅትና የሆነው አምላክ አደረገው፡፡ ይህን ያየው ዮሐንስም ቀድሞ የለመደው ሥርዓት ልምድ ሆኖበት ጌታን ባየው ጊዜ ዮሐንስ እንዲህ አለ ጌታ በባርያው ይጠመቃል እንጂ እንዴት ባርያ ጌታውን ያጠምቃል?ጌታም ጽድቅን እንፈጽም ዘንድ ይገባል አለው፡፡ ጽድቅን ማለቱ ትኅትናን አንድም የሠራልንን ሥርዓት  ሲል ነው፡፡ ዛሬ ይህ ሥርዓት ሆኖ በስሙ ያመኑት ሲጠመቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ይገለገላሉ እንጂ ንጉሥ ነኝና ካህኑንና መጥተህ አጥምቀን አይሉትም፡፡ ዮሐንስም ጌታን በማጥመቁ መጥምቀ መለኮት ተሰኝቷልና ጽድቅን እንፈጽም ዘንድ ይገባል አለ፡፡ አርአያ ምሳሌ የሆነን በባርያው እንዲጠመቅ ራሱን ዝቅ ያረገ የጌታችን ትኅትና ምንኛ ድንቅ ነው?
ለጌታስ የዮሐንስ ንስሐ ጥምቀት አይገባውንም እጸድቅ አይል ጻድቅ፤ እከብር አይል ክቡር፣ እቀደስ አይል ቅዱስ የነገሥታት ንጉሥ፣ የኃያላን ኃያል፣ የአማልክት አምላክ፣ የባሕርይ አምላክ የሁሉ ጌታ ነውና(ሮሜ፱፥፭፣ ፩ዮሐ ፭፥፳፣ ፩ተሰ ፫፥፲፩፣ ቲቶ፪፥፲፩፣ ኢሳ ፱፥፮፣ ፩ጢሞ ፮፥፲፭፣ ራእይ ፲፱፥፲፩-፲፮) ጥምቀተ አይሁድም አይገባውም፡፡ ታዲያ ይህ ክቡር አማላክ መጠመቁ አርአያ ሊሆነን (ተጠመቁ ሊለን) ጥምቀታችንን ሊባርክልን ለዘመናት ተሰሽጎ የኖረውንና በጭላንጭል ለአንዳንድ የብሉይ ኪዳን አበው ብቻ የተገለጠውን ምሥጢሩን ሊገልጥ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡
 

      የጌታ ጥምቀት

በጥምቀተ እግዚእ የምሥጢረ ሥላሴ መገለጥ
ስለእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት መገለጽ በብሉይ ከተነገሩት ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የአብርሃም ታሪክ(የሥላሴ በቤተ አብርሃም መገኘት) ነው፡፡ በሐዲስ ውስጥም በየትኛውም ታሪክ ይሁን የእግዚአብሔር ሦስትነት ምሥጢር በይፋ የተገለጠው በዮርዳኖስ ወንዝ በእደ ዮሐንስ ጌታ ሊጠመቅ ከገሊላ በመጣ ጊዜ ነው፡፡ ነገረ ሥላሴ በብሉይ ኪዳን የተሸሸገ ለእስራኤላዊያን ያልተገለጠ ነው፡፡ አንዳንድ ጭላንጭሎች ካልሆነ በቀር አንድ አማላክ እንደሆነ ብቻ እየገለጠ በነቢያቱ አማካኝነት መልእክት እያስተላለፈ ቆየ ይህም የሆነበት ምክንያት ምሥጢሩ ለእስራኤል ተገልጦ ቢሆን ኖሮ ምሥጢሩን ካለመረዳትና ካለመገንዘብ ሦስት አማልክት ብለው ባመለኩት ነበር ይህን የልባቸውን ነገር የሚያውቀው ቅዱስ እግዚአብሔር ለእስራኤል ለአንዳንድ ቅዱሳን ካልሆነ በቀር ሦስትነቱ ሳይገለጽኖሯል፡፡
በጌታ ጥምቀት ታላቅ ምሥጢር ተገለጠለው ያለምክንያት አይደለም በዚህ ወቅት ነበር ሰማይ ተከፍቶ መለኮታዊ መገለጥ በገሃድ የታየው፡፡ ምንም ባጭሩ ቢጻፍ ድርጊቱ ግን ከሰማይና ከምድር ከበደ ነው፡፡ አሮጌውዓለም በምሥጢረ ጥምቀት እንዲታደስና አዲስ ፍጥረረት እንዲሆን በቅድስት ሥላሴ መባረኩን እናያለን፡፡ የጌታ መጠመቅና የሥላሴ መገለጥ ከሰው ልጆች ድኅነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን አስደናቂ መገለጥ በአጭሩ ሲገልጥ ‹ተጠምቆም ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት ታይቷል:: አብም " “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ይህ ነው ብሎ መስክሯል: (ማቴ ፫፥፲)
በክርስቶስ ጥምቀትና ጸሎት ሰማያት ተከፍተው ሰማያዊ ምሥጢር መገለጡን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወቅቱን አስተርዮ(መገለጥ) ጋር ታያይዘዋለች፡፡ በመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ንስሐ ገብተው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው የመንግስተ ሰማየት መቅረብ አውቀው ለሚጠባበቁ ሰዎች  ሁሉ የሥላሴ ምሥጢረ ሥላሴ ምሥጢር ተገልጦላቸዋል፡፡እንግዲህ በዚህ መለኮታዊ ክስተት ውስጥ ሦስት መሠረታዊ ገነር እንመለከታለን፡፡ የመጀመርያው የመንፈስቅዱስ በአካል መልክ በርግብ አምሳልመገለጥ ሁለተኛው የአብ በደመና መገለጥ ሲሆን ሦስተኛው በእደ ዮሐንስ የተጠመቀው ክርስቶስ የአብየባሕርይ ልጅ እንደሆነ አመልካች የሆነው የአብ ምስክርነት ነው፡፡
በጥምቀት ወደ እርሱን ወደ መምሰል መለሰን
እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ፈጥሮ ባገባደደበት በዕለተ አርብ ከፍጥረታት ሁሉ ልዩ ንዑድ ክቡር የሆነውን አዳምን ፈጠረ፡፡ በኦሪት ዘልደት መጽሐፍ ተጽፎ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ‹‹ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር››ብሎ በመልኩና በምሳሌ ፈጠረው፡፡ (ዘፍ. 1÷26) ሰው ገና ሲፈጠር በጸጋ አምላክ እንዲሆን ተደርጎ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የመፈጠሩ ጉዳይ ኦርቶዶክሳዊያን አባቶቻችን በብዙ ትርጉም ይተረጉሙታል፡፡ ይህም እግአዚአብሔርን የመምሰላችንን ጉዳይ በስፋትና ጥልቀት የሚተነተን ነው፡፡
ቅዱስ ባስልዩስ አርአያ ለሁሉ የተሰጠ ነው ምሳሌ (አምሳል) ስንል ግን  በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፣ ትሑትና የዋኅ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ሳለ ከክብሩ በኃጢያት ምክንያት ተዋረደ፡፡ በአዳም ምክንያት ሞት በሰው ሁሉ ላይ ታወጀ፡፡ ቅድስና እንደመርገም ሆነ ቅዱሳን ከሲኦል እስራት የሚፈታቸውን በመፈገለግ ተጨነቁ በዚህን ጊዜ አምላክ አንደኛ ልጁን ወደ ምድር ላከ(ዮሐ. 3፥16) አምላኩን መምሰል ያቃተው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ ከሕግጋቱ እየፈጸመ በሕይወቱ የጎለበተ ይሆን ዘንድ ሕግን እየፈጸመ አሰለጠነው፡፡የሰለጠነበትና የገዛውን ዲያቢሎስን በመስቀሉ ድል አደረገው፡፡ እግዚአብሔርን ይመስል ዘንድ ዳግመኛ ሕጉን  አጸናለት፡፡ ትዕዛዙንም የሚፈጽሙት ሁሉ ወደ እርሱ መምሰል ይቀርቡ ዘንድ፡፡ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በአንድነት ‹‹ሰው በጸጋ አምላክ ይሆን ዘንድ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ››ብለው ያስተምራሉ፡፡ቅዱስ ያሬድም በዜማ ድርሰቱ ‹‹ ቃል ሥጋ ኮነ … ደመረ መለኮቶ ምስለ ሥጋ ዚአነ››የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ በተመለከተ ይሀም ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለው የሰውና የእግዚአብሔር ተዋሕዶ ምሥጢረ ሥጋዌን እግዚአብሔር ጋር መመሳሰል ጋር በእጅጉ ያገናኘዋል፡፡ በጥምቀቱና በትንሣኤውም ዳግመኛ መነሳትን አደለው ከሙታን ጋር እነዳይቆጠር ወልደ እግዚአብሔር ሞትን ድል አድርጎ ወደ ቀደመ መምሰሉ መለሰው፡፡ ቀድሞም ሲፈጠር የሚተኛና የሚነሳፍጥረት አድርጎ መፍጠሩ አዳም ሕያው ፍጥረት መሆኑን አመልካች ነው፡፡
በጥምቀእኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡ በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ ‹‹በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም››ይለናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ‹‹የማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም፡፡ በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል››ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ለዚህ መልስ ሲሰጥ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡››ይላል (ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)
አሁን ወደ ቀደመ መምሰላችን በጥምቀት ተመልሰናል፡፡ በጥምቀት ከሞቱና ከትንሣኤው ጋር እንተባበራለን፡፡ ቅዱስ አባታችን ባስልዮስ እንዳለ በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ቀና መንገድ ልንጀምር ይገባል፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረገውን እያሰብን በእርሱ የቅድስና መንገድ ልንጓዝ ይገባል፡፡ አሁን እንደብሉይ ኪዳን አበው መልካሙን መንገድ ማን ያሳየናል በለን አርአያ(ምሳሌ) ፍለጋ እንዳንባዝን ሆነናልና፡፡ እርሱን እንድንመስለው በቅድስና እንድኖር የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን አበው ምልጃና ጸሎት አይለየን
ስብሐት ለእግዚአብሔር



ዋቢ መጻሕፍት
*      ወንጌል ቅዱስ አንድምታ
*       ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
*      መጽሐፈ አክስማሮስ
*      ብሉይ አንድምታ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት



No comments:

Post a Comment