Thursday, 15 June 2017

‹‹የበኩር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም››ማቴ 1÷25


የበኩር ትርጉም

በኩር የግእዝ ቃል ነው ትርጉሙም ‹‹የመጀመሪያ ልጅ›› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሴን ‹‹በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማኀጸንን የሚከፍት በኩር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ የእኔ ነው›› (ዘጸ 13÷1) ብሎ በተናገረው ቃል መሰረት የእናቱን ማኅጸን የሚከፍት ሁሉ በኩር ይባላል፡፡ አንድ ሰው በኩር ለመባል (ለመሆን) የግድ ተከታይ ሊኖረው አያስፈልገውም፡፡
አባ ጄሮም፡- ‹‹ብቸኛ ልጅ ሁሉ የበኩር ልጅ ይባላል፡፡ የበኩር ልጅ ሁሉ ግን ብቸኛ ልጅ አይደለም›› እንዳለ አዲስ የተጋቡ ወላጆች የመጀመሪያ ልጃቸውን በኩር እንዲባል ሁለተኛ ልጅ መውለድ አይጠበቅባቸውም፡፡ አንድ ብቻ ቢሆንም ተከታይ የሌለው በኩር ይባላል፡፡ ይህን ለማስረዳትም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው መልእክቱ ዕብ 1÷6 ላይ ‹‹ደግሞ በኩርን ወደ ዓለም ሲያስገባ….›› በማለቱ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እግዚአብሔር ወልድ በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ሆኖ ወደ ዓለም መምጣቱን ያመለክታል፡፡ በኩር በመባልም ተከታይ እንደሌለው ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹እግዚአብሔርን ያየው ማንም የለም በአባቱ ዕቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› (ዮሐ 1÷18) በማለት የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ብኩርናን አንድ ልጅ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
እንግዲህ ‹‹የበኩር ልጅዋን›› መባሉ መጻሕፍት አስተባብረው በኩር፣ በኩር ብለው የተናገሩለት፣ ቅድመ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን የፈጠረ፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለውን አምላክ፣ ልዑል ባሕርይን ወለደች ለማለት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ በኩር በማለት ረቀቅ ባለ አመለካከት (አመሰጣጠር) ያስተምራሉ፡፡ እንደ ሊቃውንቱ አባባል በኩር የሚለው ቃል ለክርስቶስ በ3 መንገድ ይፈታል፡፡
በልደቱ፡- ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም ያለ አባት በመወለዱ በዚህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንደኛ ተመሳሳይ የሌለው ብቸኛ በመሆኑ በኩር ተብሏል፡፡
በሞቱ፡- ‹‹ነፍሴን እኔ በፍቃዴ እኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም›› (ዮሐ 10÷18) እንዳለ የሞትን ጻእር አርቆ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በመለየት የሙታን በኩር ተብሏል፡፡ በዚህም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንደኛ ተመሳሳይ የሌለው ብቸኛ ነው፡፡
በትንሣኤው፡- ‹‹ነፍሴን ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ስልጣን አለኝ›› ብሎ እንደተናገረ (ዮሐ 10÷18) መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በገዛ ስልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳቱ፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው የማይቻለው መሆኑን በመግለጡ፤ ለሞት ተገዢዎችም ትንሣኤን በመስጠቱ ከሞት ለሚነሡ ሁሉ በኩር ሆነ፡፡ በገዛ ስልጣኑም ከሞት ተነሥቶ ትንሣኤን ለሙታን በመስጠቱ የሚመስለው የሌላ ብቸኛ፤ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንደኛ ነው፡፡
በአጠቃላይ በኩር የሚለው ቃል ለክርስቶስ ሲተረጎም
ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንደኛ
ተመሳሳይ፣ አቻ፣ እኩያ ተፎካካሪ የሌለው ብቸኛ ማለት ነው፡፡

የ ‹‹እስከ›› ትርጉም

ለስም አጠራርዋ ክብር ይግባትና ‹‹የበኩር ልጅዋን እስከትውልድ ድረስ አላውቃትም›› የሚለውን ኃይለ ቃል በመያዝ መናፍቃን ዮሴፍም እመቤታችንን ጌታን ከወለደች በኋላ በግብር አውቋታል በማለት በድፍረት ያስተምራሉ፡፡ ይህ ትምህርት ትክክል እንዳልሆነና እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና ያላት መሆንዋን የሚከተለው ሐተታ ቀርቧል፡፡
‹‹እስከ›› - በመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዓይነት አገባብ(ትርጉም) አለው
ፍጻሜ ያለው እስከ ፍጻሜ ላገኙ ነገሮች መግለጫ
ፍጻሜ የሌለው እስከ ፍጻሜ ላላገኙ (ፍጻሜ ለሌላቸው) ነገሮች መግለጫ
ፍጻሜ ያለው ‹‹እስከ››
ምሳሌ፡-
‹‹እስክነግርህ ድረስ በግብጽ ተቀመጥ›› (ማቴ 12÷13)
‹‹ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ›› (ማቴ 12÷15)
‹‹ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፤ እርሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ›› (ኢያ 7÷6)
ፍጻሜ የሌለው ‹‹እስከ››
ምሳሌ፡-
‹‹ቁራም ውኃው በምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያ ወዲህ ይል ነበር›› (ዘፍ 7÷8) የጥፋት ውሃ ከደረቀ በኋላስ ተመልሷልን? ይህ ቃል ቁራው ተመለስ ማለት ሳይሆን ለሁልጊዜ ወይም ጭራሽ አለመመለሱን ስለሚያመለክት ፍጻሜ የሌለው እስከ ይባላል፡፡
‹‹የሳኦል ልጅ ሜልኮልም እስከሞተችበት ድረስ አልወለደችም›› (2ኛ ሳሙ 6÷23) የሚለው ኃይለ ቀል ሜልኮል ከሞተች በኋላ ወልዳለች ማለት ነው? ከሞት በኋላ መውለድ የለም፡፡ (ማቴ 22÷30) ይህ ማለት ሜልኮል ለዘለዓለም ልጅ አልወለደችም ለማለት ነው፡፡ ከተረገመች ጊዜ አንሥቶ መካን ሆና እንደቀረች ለማመልከት ነው፡፡
‹‹እንሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› (ማቴ 28÷20) ከዓለም ፍጻሜ በኋላስ ከእነርሱ ጋር አይኖርም ማለት ነውን? ይህ ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው
የ‹‹አወቀ›› ትርጉም
ተረዳ፣ ተገነዘበ፣ልብአለ፣አስተዋለ ማለት ነው፡፡
ምሳሌ፡- ‹‹ኖህም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ ታናሹ ልጁ /ካም/ ያደረገበትን አወቀ›› (ዘፍ 9÷24) - ምን እንዳደረገበት ተረዳ፣ ተገነዘበ
ተገናኘ፣ በግብር አወቀ (በግብረ ሥጋ)
ምሳሌ፡- ‹‹አዳም ሄዋንን አወቃት›› (ዘፍ 4÷1)
ስለዚህ ‹‹አላወቃትም›› ሲል፡-በግብር እውቀት አላወቃትም ሊል ነው መልኳን አላወቀም/አልተረዳም/፡፡ በአንድ ኅብረ መልክዕ አላውቃትም፡፡ መልኳ ይለዋወጥ ነበርና ጌታን እንደጸነሰች ለማጠየቅ መልኳን ይለዋውጠው ነበር፡፡የብርሃን ጎርፍ ይፈስባት ነበርና፡፡ እንኳን የፀሐየ ጽድቅ ሰሌዳ የሆነች እመቤት ሙሴስ እግዚአብሔርን በማናገሩ ብቻ ስላናገረ ኃላፊ ብርሃን ቢሳልበት እስራኤል ‹‹ተገልበብ ለነ›› ተሸፈንልን ይሉት ነበር፡፡ (ዘዳ 34÷29)
አንድም፡- በነቢያት ወልድ የተባለ እርሱ ድንግል የተባለች እርስዋ እንደሆነች
አላወቁም ነበር፡፡
ምነው መልአኩ ነግሮት አልበረምን? ቢሉ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹አንድ ዓይን አያስረገጥ አንድ ምስክር አያስደነግጥ›› እንዲሉ ለምስክርነት አላወቃትም አለ፡፡
ምነው ዮሴፍ መልአኩ ባይነግረውስ ቀድሞ የተነገረውን ትንቢት አያውቅምን? ቢሉ ነቢያት (ነቢዩ) ድንግል አለ እንጂ እሷ ናት አላለውም ልጅ አለ እንጂ አምላክ አላለውምና፡፡
አንድም፡- ዮሴፍ በእጮኛ ስም ለእመቤታችን አገልጋይዋ፤ ተላላኪዋ፣ ሆኖ የተመረጠበት ምስጢር ምን እንደሆነ አላወቀም ነበር፡፡
መጻሕፍት በኩር ያሉትን ስሙን ኢየሱስ ያሉትን ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፡፡

ዮሴፍ 5 ነገሮች አይቶ እስኪረዳ ድረስ አላወቀም /አልተረዳም/

  • ምጽአተ ሰብአ ሰገል ዘምስለ አም
  • ሑረተ ኮከብ በካልእ ፋ
  • ሥርቀተ ስብሐተ እግዚ
  • ዓቢይ ቅዳሴ መላእክ
  • ፍርሃተ ኖሎት

2 comments:

  1. መልስ የሚያሻው ጉዳይ ነው። ጥሩ አስተማሪ ጽሑፍ ነው ቃለ ሕይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ጥሩ መልስ ነዉ

    ReplyDelete