Saturday, 29 July 2017

ሩካቤ ሥጋ ለምን?ትክክል የማይሆነው መቼ ነው?


                                                                                           ትርጉም በዲ/ን ፍሬው ለማ
በብጹዕ አቡነ ሙሳ የግብጽ ቤተክርስቲያን የወጣቶች ጳጳስ
በዘመናችን ብዙ ጩኸቶችን እንሰማለን ሰዎች «እግዚአብሔር ይህን ሃሳብ ለምን በእኛ ውስጥ ፈጠረ ለምንስ ያስጨንቀናል» ሲሉ እናደምጣቸዋለን ይህ የሥጋ ሃሳብ የሰውልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ በምድር ላይ ብዙ ችግሮችን ፣ውጣ ውረዶችን አምጥቷል ለእነዚህም የሰዶምና የገሞራ ሰዎችን ማንሳት እንችላለን ዮሴፍም ለእስር የተዳረገው በጲጥፋራ ሚስት ውስጥ በነበረ የዝሙት ሃሳብ ነው ይህ ብቻ አይደለም በኦሪት ዘሌዋውያን የምናገኛቸው ታሪኮች፣የሶምሶን መውደቅ፣የነገደ ብንያም በደል፣የዳዊት ኃጢአት እነዚህ ሁሉ ከዚህ የሥጋ ፈቃድ ጋር የተያያዙ ናቸው
በዚህ ጊዜ ዓለምን ለመምሰል የሚደረግ ሩጫ በብዙ እንመለከታለን በጓደኝነትም በብዙሃን መገናኛዎች(ሚዲያዎች) ይህን መስማት የተለመደ ነገር እየሆነ ነው በሃገራች በድብቅ ከመከናወን ያለ ኀፍረት በአደባባይ ወደ መደረግ ተሸጋግሯል
እውን ጌታ ሩካቤ ሥጋን የፈጠረው ነፍሳችንን ሊያስጨንቃት ነውን?
ብዙ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰማያዊውን መንግስት የሚናፍቁ ክርስቲያን ወጣቶች በዚህ ሃሳብ አዕምሯቸው ሲጨነቅ ይስተዋላል ከዚህ ጋር በተያያዘ ድኅነታቸው ከባድ እንደውም የማይቻል ይመስላቸዋል ቅዱስ ጳውሎስ ግን በሮሜ13፡11 ላይ«ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ወደ እኛ ቀርቧል » ይላል

ታዲያ ለምን ጌታ ሩካቤ ሥጋን ፈጠረ?

ጌታ የሰው ዘርን በምድር ላይ ማቆየት ቢፈልግ በሁለት ጾታ ሳይሆን ሁላችንም የተለያየን አድርጎ ሊፈጥረን ይችል ነበር ከሩካቤ ሥጋ ውጭ በራሳቸው ብቻ የሚራቡ ዕፅዋት እና ጥቃቅን ተህዋስያን አሉና ይህም ማለት በ(self-pollination እና binary production) የሚራቡ አሉና እንደነርሱ ያደርገን ነበር ወይም ደግሞ በአብዛኞቹ እንስሳት ውስጥ እንዳለ ጌታ ይህን ስሜት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ንቁ የሚሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚጠፋ ሊያደርገውም ይችል ነበር ነገር ግን ጌታ ሩካቤ ሥጋን የፈጠረው የሰው ዘርን በምድር ከማቆየት በላይ ዓላማ ስላለው ነው የእግዚአብሔር ሃሳብ በእኛ መካከል ፍቅርን መተሳሰብን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ ህብረትን የሚመስል በእኛ መካከል መፍጠር ነው
ይህም እጅግ በተረዳ መልኩ በምስጢረ ተክሊል ይገለጻል አንድ ክርስቲያን ለሌላ ሁለተኛ ሰው ራሱን አሳልፎ በመስጠት ከሁለትነት ወደ አንድነት በመንፈስ ቅዱስ የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ነው ለዚህም ነው ከዚህ ከተቀደሰ ሩካቤ ሥጋ ያፈነገጡ ሁሉ ከእውነተኛው የህይወታቸው መስመር ጭምር የሚያፈነግጡት
ሩካቤ ሥጋ ትክክል የማይሆነው እንዴት ነው?
ከሩካቤ ሥጋ ጋር የተያያዙ የዝሙት የማመንዘር ኃጢአቶች ከሥጋ ብቻ የሚመነጩ አይደሉም ነገር ግን በርከት ካሉ ከሰው ጋር ከተያያዙ ስሜቶች፣ፍላጎቶች ነው። በሥጋችን ላይ የምናሳያቸው ነገሮች የእነዚህ ስሜቶቻችን ውጤቶች ናቸው። እነዚህ ውስጣዊ ሃይሎች ናቸው አንድን ሩካቤ ሥጋ ከትክክለኛው ነገር እንዲያፈነግጥ የሚያደርጉት እነዚህ ውስጣዊ ስሜቶች አራት ናቸው እነዚህም

1.ራስ ወዳድነት(ego centrism)
ያለ ጥርጥር እንደሚታወቀው እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በህብረት እንዲኖር ነው ራሱ ጌታ እንዲህ ብሏልና«ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደልም»ዘፍ 2፡18 ከዚህም በተጨማሪ ጌታ ደስታዬ በአዳም ልጆች ነው ብሏል ከእርሱም ጋር ህብረት እንዲኖረን ይፈልጋል ነገር ግን የሰው ልጅ ስህተት የሚጀምረው ስለራሱ ብቻ ማሰብ ሲጀምር ነው ጌታንም ሌሎቹንም ሲተው ነው ይህ በራስ ብቻ የሚል ስሜት ራስ ወዳድነት ነው ይህ ከሌሎች መገንጠል ሩካቤ ሥጋን አፈንጋጭና ጎጂ ከሚያደርጉት ሃሳቦች ዋነኛው ነው
የሰው ልጅ በራሱ መደሰት፣ራሱን መውደድና ራሱን ወደ ማምለክ እና በራሱ ወደ መኩራራት ሲያመራ ሌሎቹን ለራሱ ሲል ለማጥፋት ይነሳሳል ይህ መሰረታዊ የሆነና ለምኞት የሚያነሳሳን ነው አንድ ሰው ራሱን የሚወድና ራሱን ለማስደሰት ሌሎችን ሲጠቀም (ከእርሱ ውጭ ያሉትን ሰዎች ለእርሱ መደሰቻ ብቻ ሲያደርግ) ራስ ወዳድነቱ ይገለጣል
ክርስቶስን በማወቅ ወደ እርሱም በመጠጋት ለጸጋ ሥራዎች ራስን ክፍት በማድረግ የሕወትን ትክክለኛ መስመር ማወቅ ይቻላል ክርስቶስ ነፍስህን ከዚህ ራስን ማግለል(መገንጠል) ያወጣት ዘንድ በጽኑ ያፈልጋል «እኅቴ ወዳጄ ርግቤ መደምደሚያዬ ሆይ በራሴ ጠል በቆንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ»መኃ፭፡፪
ወዳጄ ሆይ ጌታ አንተን እየጠራህ ነው ልብህን ለእርሱ ከፍተህለታል? ከእርሱ ጋር መነጋገርስ ትፈልጋለህ?ህይወትህንስ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላ ራስ ወዳድነት ትድን ዘንድ በፍቅሩ ትኖር ዘንድ ትፈልጋለህ?
በቅዳሴ ላይም «ያንተን ስም ሰምቶ ሞት ይደንግጥ ቀላያትም ይሰንጠቁ አለማመን ይራቅ…»ቅዳሴ እግዚእ እንላለን ጸሎት በቅዳሴ መሳተፍ ስሙን መከታ ማድረግ ከዚህ መጎምዠት ያላቅቀናል

2.ማቴሪያሊዝም(በቁስ አካል ብቻ መደስት)
የሰው ልጅ በሩካቤ ሥጋ የተለየ ደስታን የሚያገኝ ይመስለዋል ይህ ግን በቅጽበት ወደ ባዶነት ና ድብርት ይቀየርበታል ይህም ሩካቤ ሥጋን ከእውነተኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቅር ስለገነጠሉት ነው ይህም ከቅዱስ ጋብቻ ውጭ ያጣጥመው ዘንድ ስለሞከሩ ነው
የብዙ ክርስቲያን ወጣቶች ችግር በጌታ የሆነ የንጽሕና ህይወትን ለመኖር አለመፈለግ ነው የሥጋ ህይወታቸው አድካሚ እንደሆነ የህይወትን እውነተኛ ትርጉም እንደሚያዛባ ቢያውቁ ኖሮ መንፈሳዊ ህይወትን ጥልቅ በደስታዎች የተሞላ እውነተኛ ህይወት እንደሆነ ይረዱ ነበር
የሰው ልጅ በምድራዊ እና ደስታ ብቻ መጠመዱ የሰው ልጅን የሥጋ ትኩረት ብሎም በሚያየው ነገር የማያየውን እግዚአብሔርን ና ጸጋውን መለወጡን ያመለክተናል ሰዎች አብዝተው ምድራዊ ነገር ብቻ ህይወትና ደስታ እንደሚሆናቸው ያስባሉ ይህ በቀዳማዊው አዳም የተጀመረ ነው ነገር ግን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ወደ ምድር በመውረድ እኛን በመምሰል አዲስ ነገርን አሳይቶናል ይህም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ መመራትን በጸጋ እግዚአብሔር መኖርን ነው በቤተክርስቲያን ምስጢራትም በመሳተፍ ይህን እናሳያለን በገዛ ሜቶቻችን በምድራዊ ነገሮች ብቻ አንገደብም የምናየው ብቻ ደስታ ይሰጠናል አንልም መርካታችን በሥጋ ብቻ አይሆንም
ወዳጄ ሆይ በንጽሕና ለመኖር አስበህ ታውቃለህ ?ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌምን ትናፍቃታለህ? እይታህን ቀስ ብለህ መርምር በሁሉም ፍጥረት ላይ እግዚአብሔር ይታይሃል? ይሄኔ እይታህ ፣መውጣት መውረድህ ሁሉ ንጹህ ይሆናል

3.ስንፍና
የሰው ልጅ በስንፍና ይኖር ዘንድ አይችልም በሕይወት ውስጥ ዓላማ ሳይዙ መጓዝ ህይወትን ባዶ ያደርጋታል ዓላማ ቢስነት ያለ ምክንያት መጓዝ እነዚህ ሁሉ በብዙዎች ውስጥ የሞሉ አሳቦች ናቸው ብዙዎች ህይወት ትመራቸዋለች ትርጉሙ ይርቅባቸዋል በመኖራቸው ምን እንደሚያገኙ አይገነዘቡም የሰውልጅ ዓላማውን ከሳተ ህይወቱ አሳዛኝ ይሆናል
ጌታ አዲስ የእይታ አድማስን ከፍቶልናል «እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ »ዮሐ13፡34 በማለት የሰው ልጅ የፍቅር መልዕክተኛ እንደሆነ አድርጎ ራሱን ሊያስብ ይገባል ይህን ጊዜ ራሱን ይረሳል ሌላውን ከራስ ወዳድነት በጸዳ ይወዳል
ስለ ሥጋዊ ስሜቶቻችን ብቻ አብዝታችሁ አታስቡ ወጣ በሉ በየመንገዱ ከመንጋው የጠፉ በጎችን ታገኛላችሁ ወዳጡት ፍቅርም ጋብዟቸው ወደ ቤተክርስቲያን ወደ ተቀደሰው ህብረትም ቀላቅሉአቸው
ወዳጄ ሆይ የህይወት ጣዕሟን በማጣትህ ብቻ ወደ ሥጋ ፈቃድ ለምን አዘነበልክ? አንተ እኮ በዓላማ ነው የተፈጠርከው ጌታን በሙሉ ልብህ ታገለግለዋለህ ?ወይስ ምድራዊ ህይወትን ብቻ ትመራለህ በመንፈስም በገንዘብም ድሃ የሆነውን ለምን ትረሳለህ
ህይወትህ ዓላማ አለው አጭር አይደለም ረዥም ነው የተፈጠርከው ከጌታ ጋር ለመኖር ነው

4.ጭንቀት
ወጣቶች ሁል ጊዜ በጭንቀት የተሞሉ ናቸው የወደፊቱን በማሰብ በቤተሰባዊ ማኅበራዊ ና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ዘወትር የሚጨነቁ ናቸው ስለዚህም ከእነዚህ ነገሮች ለማረፍ ወደ ኃጢአት ዓይናቸውን የሚያነሱ ጥቂቶች አይደሉም ያልሞከሯቸውን ነገሮች በመሞከር ደስታቸውን ይፈልጓታል
ስለዚህ በንጽህና ህይወት ውስጥ ያሉ ወጣቶች በምንም ሃሳብ ሊጨነቁ ስለየትኛውም ችግር ብቻ በማሰብ ጊዜአቸውን ሊያጠፉ አይገባም በአስተማማኙ በጌታ እጅ ውስጥ እንዳሉ ሊሰማቸው ይጋባል በልበ ሙልነት አባቴ የሙሉት እግዚአብሔር እንዳለ ሊያውቁ ይገባል እርሱ ፍላጎቶቻቸውን ሳይነግሩት የሚያውቅ የሚያስፈልጋቸውንም በትክክለኛው ጊዜ የሚቀርብ ነውና
ከጌታ ጋር በፀጥታ ስለ ቤተሰባዊ ፣ሥጋዊ ችግሮችህ በመነጋገር የውስጥህ ሰላም እንደሚመለስ እነግርሃለሁ ስለዚህ ስሜቶችህ ሊጎዱ አይገባም ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአት ና ባልተገቡ ልማዶች መውደቅ የለብህም ተነሣ ጌታም ይደግፍሃል
እርሱ በሥጋ መነ ር ብቻ ነጻነት የሚመስለው ካለ ተሳስቷል እንደውም የሥጋ ምኞት የሥጋ ቀንበር የሰይጣን ደሞዝ ነው እውነተኛ ደስታም በውስጡ የለም ይልቁንም በኃጢአት የተሞላ ነው የሰው ልጅን በባዶ የሚያስርበው የህይወቱን ጣዕም የሚያበላሸው እርሱ ነው አንተ ግን ከጌታ ጋር እንዲህ በል «እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ በአንተ ምክር መራኸኝ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ»መዝ72፡24
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

የመተጫጨት ሕይወት (ክፍል አንድ)


በዲ/ን ያሬድ መለሰ

መነሻ

በወጣትነት ሕይወት ውስጥ በብዙ ወጣቶች ዘንድ እንደ ጥያቄ የሚቀርበው ጉዳይ ነው የመተጫጨት ሕይወት ፡፡ በክርስትና የሕይወት መስመር ውስጥ አንድ ክርስቲያን ሁለት ምርጫዎች አሉት፡፡ የመጀመርያው የምንኩስና ሕይወት ሲሆን ሁለተኛው የትዳር ሕይወት ነው፡፡ ከመጽሕፍት ትምህርት እንደምንረዳው ሁለቱም ሕይወት እግዚአብሔር የባረካቸው ናቸው፡፡(ማቴ 19:1-6) (ዕብ 13፡4) (1ቆሮ 7፡1-7) ብዙ ቅዱሳን አባቶችም የሄዱበት የሕይወት መስመር ነው፡፡ይህን አስደሳች የሕይወት መስመር ጣፋጭ ለማድረግ ታድያ እግዚአብሔርን አስቀድሞ መለመን ወደ እርሱም መመለስ ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ያልታከለበት ምርጫ የመተጫጨት ሕይወት ፍጻሜው ያማረ አይሆንም፡፡ ስለዚህም በሕይወት ምርጫችን እግዚአብሔርን ማስቀደም ይሆንብናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ በመተጫጫት ሕይወት ውስጥ መንፈሳዊ ወጣቶች ሊያደርጉት የሚገባውንና ማድረግ የሌለባቸውን የሚዳስስ ነው፡፡ ዓላማውም ስለመተጫጨት ሕይወት ማስተማር ነው፡፡
ስለመተጫጨት ሕይወት ከማየታችን በፊት ስለትዳር አንዳንድ ነጥቦችን መዳሰስ አስፈላጊ ነው፡፡

የጋብቻ አጀማመር

ጋብቻ የተጀመረው በመጀመሪያው የሰው ዘር አባትና እናት በሆኑት በአዳምና በሔዋን ነው፡፡መሥራቹም ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ በመሥራቹም የጋብቻ ክቡርነትና ፀጋነት ታወቀ፡፡በዚህም ምክንያት የቤተሰብን የኅብረተሰብን ምንጭ መሠረተ (ዘፍ 2፡18-23) (ኩፋ 4፡6) በአዳምና በሔዋን መካከል ያለው ጋብቻ መወሰን ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም ለአዳም ብዙ ሴቶች አለመፈጠራቸው ለአንድ ወንድ አንዲት ሴት እንጂ አያሌ ሴቶች ያልተፈቀዱለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ይህንም በብሉይ ዘመን ከነበሩ ደጋግ አባቶች ዘንድ ብንመለከት የጸና ነው፡፡ ለምሳሌ የኖኅ ጋብቻ የተባረከ ሕጋዊ ጋብቻ ነበር፡፡ የአብርሃምም እደዚሁ፣ የይስሐቅና የርብቃ፣ የዮሴፍና የአስናት ጋብቻም የተባረከና ቅዱስ ነበር፡፡
ጋብቻ በሕገ ልቡና እንደነበሩ አባቶች በኦሪትም የነበሩ ቅዱሳን አባቶች አክብረውታል፡፡ ስለዚህም የቤዛዊተ ዓለም የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተሰቦች በቅዱስ ጋብቻ የተገኙ ናቸውና፡፡ እዲሁም የዘካሪያስና የኤልሳቤጥም ጋብቻ መለኮትን ያጠመቀ ዓለም የሰበከ ቅዱስና ነብይ ወሰማዕት መጥምቁ ዮሐንስን አስገኝቷል፡፡
በብሉይ ኪዳን የነበሩት የአባቶቻችን የተባረከና ቅዱስ ጋብቻ እንደነበረ የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ የይስሐቅና የርብቃ ጋብቻ መመልከት ይቻላል፡፡በዚህ ዘመን የዘመድ ጋብቻ ሲመረጥ ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም በምድር ላይ ሰው ዘር ባለመብዛቱ ነው፡፡ (ዘፍ 24፡1-) (ዘፍ 23፡1-5) (ዘፍ 28፡29) (1 ኛሳሙ 18፡22-29) ኦሪት ከተተካ በኋላ ግን ይህ የሥጋዊ ዝምድና ጋብቻ ቀርቷል፡፡ ዘመድም ከዘመዱ እንዳይጋባ ትዕዛዝ ወጥቷል፡፡ (ዘፍ 18፡6-18) (ዘፍ 20፡17)
የሐዲስ ኪዳንን የጋብቻ ክቡርነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ገልጦልናል፡፡ (ዮሐ 2:1-11)ጌታም ስለ ጋብቻ ሲያስተምር፡-ጋብቻ ሰው በዘፈቀደ ሊፈታው የማይገባ ጽኑዕ የውሕደት ማሰሪያ እግዚአብሔር አምላክም የሚገኝበትና የሚያዝበት ትልቅ ምሥጢር እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ (ማቴ 19:1-6) (ዕብ 13፡4)

 የጋብቻ ለምን

የጋብቻ መሰረታዊ ዓላማዎች ሦስት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
1. በኑሮ ለመረዳዳትና ሕይወትን በጋራ ለመምራት ነው
‹‹ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት›› (ዘፍ 2፡18) በዚህ ቅዱስ ቃል መሠረት የምንረዳው ጋብቻ ሲመሠረት ዓላማው መረዳዳት መሆኑን ነው፡፡ መረዳዳት ሲባልም በፍቅርና በመተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር የሴቷ ብቸኛ ግዴታ ሳይሆን የወንዱም ኃላፊነት ነው፡፡ 1ጴጥ 3፡1-7
2. ለመባዛትና ዘር ለመተካት ነው፡፡
• ወላጆች አምሳያቸውን ልጅ በመውለድ ሲተኩ የሰው ዘር ከገጸ ምድር እንዳይጠፋ ይረዳል፡፡
• ጋብቻን ያጠናክራል ያጸናል፡፡
• የተጋቢዎችንም ቤት በደስታና በፍቅር ይሞላል፡፡
ይህ ዘር የመተካቱ ነገር ግን እግዚአብሔር በፈቀደ የሚደረግ ነው፡፡ ተጋቡ ማለት ዘር ይተካሉ ማለት አይደለም፡፡ ቀዳሚውና ዋናው በነፍስ በሥጋ በሃይማኖት መተሳሰብ መረዳዳትና መተጋገዝ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

3. ከዝሙት ኃጢአት ለመጠበቅ ነው፡፡
የጋብቻ አስፈላጊነት ሰው ለፈቀደሰው ሥጋውን ዝርው አድርጎ በነፍስም በሥጋም እንዳይጎዳ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ዝሙት ጠንቅ በተናገረበት ወቅት በባልና በሚስት መካከል ሚስት በገዛሥጋዋ ላይ ሥልጣን እንደሌላት ባልም በገዛ ሥጋው ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደሌለው ይገልጽልናል፡፡
‹‹በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላል›› ጋብቻ ከፈቃደ ሥጋ ለሚመጣ ማንኛውም ፈተና ፍቱን መድኃኒት ነውና፡፡ (1ቆሮ 7፡1-7) (ዕብ 13፡3)
ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት
የጋብቻ መቅድሙ መተጫጨት ነው፡፡ ቅዱስ ጋብቻን ለመመሥረት (ይህም ከእጮኝነት ዘመን የሚጀምር ነው) የሚያስብ ሰው አስቀድሞ ከግምት ውስጥ ሊያስገባቸው የሚገቡ ጉዳዎችን አሉት፡፡

1. በሃይማኖት አንድ መሆን፡- ሃይማኖት የሁሉ ነገር መሠረት ነው በጋብቻ ሕይወት በአንድ ላይ ለመኖር የተጫጩ እጮኛሞች አንድ ሃይማት ሊኖራቸው ይገባል (2ኛ ቆሮ 6፡14)
2. ድንግልናቸውን መጠበቅ፡- የተክሊልን ብርሃን ለማግኘት ድንግልና አስፈላጊና ዋናው ነገር ነው ድንግል ማለትም ወንድ ያላወቃት ሴት ወይም ከሴት ያልደረሰ ወንድ ማለት ነው፡፡
3. የሁለቱም ፈቃደኝነት፡- መተጫጨታቸው በቤተሰብ በኩል ከሆነ የታጩት ሰዎች ፈቃደኛ መሆን አለባቸው፡፡ያለ ተጋቢዎቹ ፈቃድ የሚደረግ መተጫጨት ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡ ከወላጆቻቸው ፈቃድና መስማማት በኋላ በቅድሚያ ለመምህረ ንስሐ በመንገር ወደ ጋብቻው ቃል ኪዳን ያመራሉ፡፡
4. በጸሎት ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ፡- ሁለቱም ተጋቢዎች የሕይወትን ክብር የሆነውን የጋብቻን ሕይወት ለማግኘት ጉጉት ከመጀመራቸው ከማስተዋል ጋር በተሰበረ ልብ ሆነው በፍጹም አሳብ የልዑል እግዚአብሔርን እርዳታ በጸሎት ማማከር አለባቸው
5. የዕድሜ ገደብ፡- ወጣቶች በሚጋቡበት ጊዜ በተፈጥሮ ሕግ በሃይማኖት በሥርዓትና በማኅበረሰባዊ የጋብቻ ድንጋጌ መሠረት በእድሜ የማይቀራረቡ ከሆነ በጋብቻው ላይ ችግር እንደሚያስከትል ከወዲሁ መታወቅ ሊኖርበት ይገባል፡፡ ዕድሜን በተመለከተ ወንዶች ከ 20 በላይ ሴቶች ከ 15 ዓመት በላይ ሲሆናቸው መተጫጨትና መጋባት የሚፈቀድላቸው መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ተመልክቶአል (ፍት.መን. 24 ም.3 ክፍል 2)
6. ሁለገብ መመጣጠን፡- ሁለገብ መመጣጠን ሲባል በዕድሜ፣ በጠባይ፣ በመንፈስና በአእምሮ ተመጣጣኝ ደረጃ እንዲኖራቸው በቂ ጊዜ መውሰድና ትልቅ ጥናት ማድረግ ይህም ለወደፊትና ለቀጣዩ ሕይወታቸው ሰላማዊነት ይረዳል፡፡
7. መንፈሳዊ እውቀት፡- የሚተጫጩ የፍቅር አጋሮች ስለ ሃይማኖታቸው፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሊማሩና ሊያውቁ ይገባል፡፡
8. የዝምድና ሁኔታ፡- ትልቁን ሊጠነቀቁለት የሚያስፈልገው ጉዳይ በተጋቢዎች መካከል ያለው የዝምድና ሁኔታ ነው፡፡ ይህንንም በ 3 መንገድ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በትዳር አብራኝ የምትኖረውን የሕይወት አጋሬን እንዴት መምረጥ እችላለሁ?፣ የተሳሳተ የእጮኝነት ሕይወት፣ መተጫጨት ለምን፣ የመሳሰሉትን ርዕሰ ጉዳዮች በሚቀጥለው ክፍል ይከታተሉ፡፡


Monday, 24 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሃያ ስምንት (የመጨረሻ ክፍል)





የሰው ልጆች ትንሣኤ
የሰው ልጅ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረው ለሞት አልነበረም፡፡ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ኃጢአት በደልን ሰራ፡፡ ቀዳማዊ አዳምና እናታችን ሔዋን የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በማፍረሳቸው የሞት ባሪያ ተገዢ ሆኑ፡፡ (ዘፍ 2÷17 ዘፍ3÷18-27 ሮሜ 5÷-20-26 ሮሜ 6÷23) ሞት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል፡-
የሥጋና የነፍስ መለያየት/እንቅልፍ/
ከእግዚአብሔር መለየት /የሞት ሞት/
የሥጋ እና የነፍስ መለያየት /እንቅልፍ/
ይህ የሞት ዓይነት ለማንኛውም ሰው የማይቀር ነው፡፡ ይህ ሞት በመጽሐፍ ቅዱ እንቅልፍ በማለት ነቢያት ሆኑ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠርተውታል፡፡ ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን ይህንን የሞት ዓይነት ዕረፍት ብላ የምትጠራው (ዳን 12÷2 ሐዋ 7÷-60' ማቴ 9÷24 ዮሐ 11÷11-13) ይህን ሞት የሞቱ ሰዎች በፍጻሜ ዘመን በክብር ወይም በኃሳር ይነሣሉ፡፡
ትንሣኤ ዘለክብር፡- የሚነሡት ጻድቃን የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያትን ሲሆን ሲነሡ ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው እንደ ፀሐይ እያበሩ ወንዶች 30 ዓመት ጎልማሳ ሴቶች 15 ዓመት ቆንጆ ሆነው ለዘላለም በደስታ በሕይወት ለመኖር የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ (ራዕ 21÷1-5 2ተኛ መቃ 13÷8-14)
ትንሣኤ ዘለኃሣር -ይህን ትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች በዚህች ምድር ሳሉ እግዚአብሔርን ሲበድሉ በክህደት በምንፍቅና የሚኖሩ ትንሣኤ ልቡና ያላገኙ ሰዎች የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ ትንሣኤ ዘለኃሣር የሚነሡት ኃጥአን ከቁራ ሰባት እጅ ጠቁረው የግብር አባታቸውን ሰይጣንን መስለው ለዘላለም ትሉ በማያንቀላፋበት እሳቱ በማይጠፋበት በገሃነመ እሳት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ (1 መቃ 13÷9-11' ማቴ 13÷-42)
ከእግዚአብሔር መለየት/ የሞት ሞት/
ይህ የሞት ዓይነት በበደል በኃጥአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ከእርሱም አንድነት መውጣት ነው፡፡ የሰው ልጅ በደልን ኃጢአት ሰርቶ በንስሐ ካልተመለሰ መጨረሻው ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ጋር ወደ ገሃነመ እሳት መጣል ነው፤ ይህም የሞት ሞት ይባላል፡፡
መልካሙንና ክፉዉን የሚያስታውቀውን ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና (ዘፍ 2÷16-17) እግዚአብሔር አዳምን ያዘዘው ይህን ትዕዛዝ ነበር፡፡ ነገር ግን አዳም ይህን ትዕዛዝ በተላለፈ ጊዜ ወዲያው ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ ፀጋውም ተገፈፈ ከገነት ወጣ የሥጋ ሞት አላጋጠመውም፡፡ ከዚህም የምንረዳው የሞት ሞት የተባለው በኃጥአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየትን ነው፡፡ በተጨማሪም (ሮሜ 5÷12 ኤፌ 5÷14-20) ተመልከቱ፡፡
ለሰው ልጆች ትንሣኤ የተነገሩ ትንቢቶች
እግዚአብሔር አምላክ ለሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በነቢያት ትንቢት አናግሯል፡፡ ካናገራቸው ትንቢት መካከል የሰው ልጅ በፍርድ ቀን ከሞት እንደሚነሣ የተናገሩት ትንቶች አሉ፡፡ እነርሱም፡- .ዳን 12÷1-3 ‹‹በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነሣሉ እኩሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ እፍረትና ጉስቁልና›› መዝ 70/71÷20 ‹‹ብዙ መከራና ጭንቀት አሳይተኸኛልና ተመልሰህ ሕያውም አደረከኝ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኝ›› ኢሳ 26÷19 ‹‹ሙታን ሕያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሣሉ በምድርም የምትኖሩ ሆይ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም›› (ዮሐ 5÷28-29' 1 ቆሮ 15÷1' 19-26' 2 መቃ 13÷8-11)
ልጆች ትንሣኤ የተደረጉ ምሣሌዎች
ለሰው ልጆች ትንሣኤ ትንቢት እንደተነገረ ሁሉ ሙታን ለመነሣታቸው የተደረጉ ምሣሌዎች አሉ፡፡ ይኸውም በኋለኛው ትንሣኤ ለሚሆነው ነገር ግን በዚህ ምድር ሲኖሩ ሞተው በኋላ በቅዱሳን ጸሎት ከሞት የተነሡ ሰዎች ናቸው፡፡
ዮሐ 11÷44- የአልዓዛር መነሣት
ማቴ 9÷25- ጌታ ያስነሣው የመኮንኑ ልጅ
ሉቃ 7÷15- ጌታ ያስነሣው የመበለቲቱ ልጅ
ሐዋ 9÷36- .ጴጥሮስ ያስነሣት ጣቢታ
2 ነገ 4÷32- ኤልሳ ያስነሣው ብላቴና እንዲሁም(2 ነገ13-20) ተመልከቱ
1 ነገ 17÷21 ኤልያስ ያስነሣው ብላቴና

ዕለተ ምጽአት/ ዳግም ምጽአት/
ዕለተ ምጽአት /ዳግም ምጽአት/ የምትባለው ዕለት ዳግመኛም ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ሆኖ የተወጋ ጎኑን የተቸነከረ እጅና እግሩን እያሳየ ለጻድቃን ሊፈርድላችሁ ለኃጥአንና ለሰይጣን ሊፈርድባቸው ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣበት ዕለት ናት፡፡ (መዝ 49/50÷2-3' ራዕ 22÷12
የሰው ልጆች አነሣሥ
የሞትህ ተነሥ የሚል አዋጅ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ይታወጃል፡፡ ሦስት ረቂቃን ነጋሪት አሉ፡፡ ነጋሪት ሲባል ነጋሪት አይደለም የጌታ ትዕዛዝ ነው ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና (1 ተሰ 4÷16) እንደተባለ
Ø  የመጀመሪያው ረቂቅ ነጋሪት ሲመታ አውሬ የበላው ነፋስ የበተነው ያለቀው የደቀቀው ሁሉ ራስ በፈረሰበት ቦታ ላይ ይሰበሰባል፡፡ (ያዕቆብ ዘሥሩግ .91)
Ø  ሁለተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ ተዋሕደው ሳይንቀሳቀስ ትኩስ ሬሳ ይሆናል፡፡ አጥንትና ጅማቶች ከሥጋ ከደም ጋር ይያያዛሉ እስኪነሡ ያለመንቀሳቀስ ፍጹም በድን ይሆናሉ፡፡
Ø  ሦስተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ በቀዋሚ አካል የምትናገር አንደበት ከራስ ጸጉራቸው ሳይከፈሉ በአርባ ቀን በእናቱ ማህጸን ደም ሆኖ የወረደው ጽንስ ሳይቀር በጎም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ይነሣሉ፡፡(ገላ 6÷7) ‹‹አትሣቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም ሰው የዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና በመንፈስ የሚዘራ ግን በመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል›› (ማቴ 25÷35-46) ተብሎ እንደተጻፈ፡፡

ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ይመሰላሉ
ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ተመሰሉ ቢባል የበጎች ተፈጥሮ ከጻድቃን ሥራ ጋር የፍየል ተፈጥሮ /ግብር/ ከኃጥአን ጋራ ስለሚመሳሰል ነው ምክንያቱም፡-
. በጎች በደጋ እንጂ በቆላ አይኖሩም፡፡ ተስማሚያቸው ደጋ ነው ጻድቃን በመከራ ሥጋ እንጂ በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን ክደው በምግባር ብልሹነት አይገኙም፡፡ ፍየሎች በቆላ እንጂ በደጋ አይኖሩም፤ ኃጥአንም በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን በወርቅ በብር ይለውጣሉና፡፡
. በጎች እረኛቸው ባሰማራቸው ሥፍራ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ጻድቃንም እረኛቸው ክርስቶስ ባሰማራቸው በአንዲት ሃይማኖት ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ፍየሎች እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ጸንተው እንደማይኖሩ ኃጥአንም እንዲሁ በሃይማኖት ጸንተው መኖር አይቻላቸውምና፡፡
. በጎች ጥቂት ሳር ካገኙ ተፋቅረው አብረው ይበላሉ ጻድቃንም ያለቻቸውን ተካፍለው ይኖራሉና፡፡ ፍየሎች ግን ሣር ቅጠሉ ሞልቶ ለሁላቸው ሲበቃ ሳለ ይጣላሉ፡፡ ኃጥአንም ሀብት ንብረት ተትረፍርፎላቸው ለወገናቸው አያካፍሉም፡፡ ለገንዘብ ብለው እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ ዘለው የሌላውን ሀብት ንብረት ለማግኘት ሲሉ የማይገባ ሥራ ይሠራሉና፡፡
. የበጎች ላታቸው የተከደነ ሐፍረተ ሥጋቸው የተሸፈነ ነው፡፡ የጻድቃንም ኃጢአታቸው በሰው ዘንድ የተጋለጠ አይደለም፡፡ ኃጢአት ቢሰሩ ሌላ ሰው ሳይሰናከልባቸው ንስሐ ይገባሉ፡፡ የፍየሎች ላታቸው የተሰቀለ ሐፍረተ ሥጋቸው የተጋለጠ ነው፡፡ የኃጢአተኞችም ሥራ በሰው ዘንድ የተጋለጠ ለሚሰሩት እኩይ ሥራ የማያፍሩ በየአደባባዩ ኃጢአትን የሚፈጽሙ ናቸውና፡፡
. በጎች አቀርቅረው እንጂ አሻቅበው አያዩም ጻድቃንም ሁልጊዜ ዕለተ ሞታቸውን በማሰብ ወደ አፈር እንደሚመለሱ እያሰቡ በትህትና ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሀብት' ንብረት' ዕውቀት እያላቸው ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ ፍየሎች አሻቅበው ነው የሚያዩት አንገታቸውን ያንጠራራሉ ኃጥአንም ደካማ ሆነው ሳሉ ብርቱ ነን ይላሉ ባገኙበት ሀብት ዕውቀት ይመካሉ ትዕቢተኞች ናቸው፡፡ ትሕትና በእነርሱ ዘንድ የበታችነት ምልክት ነው፡፡
. ከበጎች ውስጥ አንዲቱ ተኩላ ቢነጥቃት ሁለተኛ ወደዚያ ቦታ ተመልሰው አይመጡም፡፡ ጻድቃንም እኩይ ሞት ከእነርሱ አንዱን ከወሰደ ነገም የእነርሱ ተራ እንደሆነ ተረድተው ከኃጢአት ሥራቸው በንስሐ ይመለሳሉ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ፡፡ ፍየሎች ግን ከመካከላቸው ነብር አንዲቱን ቢወስድ ለጊዜው ደንብረው ይሄዳሉ፡፡ ኋላ ግን ተመልሰው እዚያው ቦታ ይመጣሉ ኃጥአንም ከመካከላቸው አንዱ ሳያስቡት በሞት ቢወሰድ ለጊዜው ደንግጠው ከኃጥአት ሥራቸው ይታቀባሉ በኋላ ግን የሞተው ሰው ከህሊናቸው ሲጠፋና የዓለም ሁኔታ ሲማርካቸው ወደ ኃጢአት ግብራቸው ይመለሳሉና፡፡
የግራ እና የቀኝ ምሳሌ
ጻድቃን በቀኝ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው
ቀኝ ቅን ነው ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ቅን ናቸውና
ቀኝ ፈጣን ነው ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ፈጣን ናቸውና
ቀኝ ብርቱ ነው ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ብርቱ ናቸውና

ኃጥአን በግራ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው
ግራ ጠማማ ነው ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመሥራት ጠማማ ናቸውና
ግራ ዳተኛ ነው ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመስራት ዳተኞች ናቸውና፡፡ ቤተክርስቲያን ለምን አትሄዱም ሲሏቸው እዚህ ቦታ ደርሼ መጥቼ ደከመኝ ጸልዩ ሲባሉ ራሱ እግዚአብሔር ፍላጎቴን ያውቅ የለ ስገዱ ጹሙ ሲባሉ ምክንያት አያጣቸውምና
ግራ ሰነፍ ነው ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት አይችልም ኃጥአንም በምግባር በሃይማኖት በኩል ጠንከር ያለ ነገር ሲገጥማቸው ደከመን ሰለቸን ብለው ይተውታል፡፡ ለኃጢአት ግን አይደክሙም ሌሊት ጨለማን ተገን አድርገው ሲዘርፉ ሲዘሙቱ ይዉላሉና፡፡
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣው በአባቱ ሥልጣን በራሱ ሥልጣን በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ነው
የሰው ልጆች ከሞት በኋላ ፈርሰው በስብሰው አይቀሩም በኋላ በፍጻሜ ዓለም ጌታችን በመጣ ጊዜ ይነሣሉ፡፡
የሰው ልጆች ከሙታን ከተነሡ በኋላ ጻድቃን ወደ ዘለዓለም ዕረፍትና ሕይወት ኃጥአን ደግሞ ወደ ዘለዓለም ዕፍረትና ጉስቁልና ይሄዳሉ፡፡
የትንሣኤያችን በኩር የድንግል ማርያም ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር