Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አንድ




†††ሃይማኖት ምንድን ነው†††
†††ሃይማኖት†††

“ሃይማኖት” ማለት አምነ፣ አመነ ከሚል የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን መዝገበ ቃላታዊ ትርጓሜውም “ማመን፣ መታመን” ማለት ነው፡፡ በምሥጢራዊው ትርጕሙ ግን “ሃይማኖት” ማለት ፍጥረትን ኹሉ ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣ አንድ እግዚአብሔር እንዳለ፣ ለሚታየውም ለማይታየውም ፍጥረት ሠራዒውና መጋቢው እርሱ ብቻ እንደኾነ፣ ልዩ ሦስትነት እንዳለው፣ በዚኽ አለ በዚኽ የለም የማይባል ምሉዕ በኵለሄ እንደኾነ፣ … ማመን መታመን ማለት ነው፡፡

በአጭሩ ግን ስለእምነት (ሃይማኖት) ትርጉም ስናወራ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው አንዱ በአንድ ነገር ላይ እምነት ማሳደር (faith in something or someone) ሲሆን ሁለተኛው ላመኑበት ነገር መታመን (reliance) ነው፡፡

†††ማመን †††
“ማመን” ማለትም ይኾንልኛል ይደረግልኛል ብሎ መቀበል፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ተስፋ ማድረግ፤ አለመጠራጠር ማለት ነው፡፡ ማመን ለሚታየውም ለማይታየውም ፍጥረት ሠራዒ ጠባቂና መጋቢ1 አለው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰራዒ ብቻ ነው የሚሉ አሉ2እምነታችን ከዚህ ይለያል ፈጣሪ ዓለማትን ከፈጠረ በኋላ እንዲሁ አልተዋትም ዘወትር ይመግባታል ይጠብቃታል እንጂ፡፡ ስለዚህም እንዲህ እናምናለን ለሚታየውም ለማይታየውም ፍጥረት ሰራዒ መጋቢ ጠባቂ አለው፡፡

†††መታመን†††
“መታመን” ማለት ደግሞ ያመኑትን እውነት በሰው ፊት በአንደበት መመስከርና በተግባራዊ ሕይወት መግለጥ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይኽን በተመለከተ፡- “ይኽም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ኾነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ብሎ አስተምሯል /ሮሜ.10፡8-10/፡፡ ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ፡- “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትኹ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል” በማለት ከኹሉ አስቀድሞ እምነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳና፤ ቀጥሎም “ማንም ግን በዚኽ መሠረት ላይ በወርቅ ቢኾን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤” በማለት ምግባር ትሩፋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል /1ኛ ቆሮ.3፡10፣12/።

†††ከእምነትና ከእውቀት የቱ ይቀድማል†††?
ከእምነትና ከእውቀት የቱ ይቀድማል3 የሚለው ጥያቄ በፍልስፍናው ዓለም አከራካሪ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ የእምነትንና የሰውን ባሕርያት በሚገባ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነትና እውቀት ተጻራሪ ሳይሆኑ የሚደጋገፉ ናቸው፡፡

†††የእምነት ባሕርያት †††
የእምነት ባሕርያት መካከል አንዱ ምክንያትን የሚቃወም መሆኑ ነው፡፡ በእምነት የሚደረገው አንዳንዴ ምክንያት አልባ ነው በትርጉም በማብራሪያ ሊገለጹ የማይችል ከአእምሮችን በላይ የሆነ ነውና ለማብራርያ ብዙም አንጨነቅም፡፡ ሃይማኖት የሚቀበሉት ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ሁለተኛው የምናምነው ነገር ምክንያታዊ ነው(እምነት አመክናዊ ነው) ለምሳሌ ሰው በጣዖት ቢያምን የምንቃወመው አመክናዊ ትንታኔ በመስጠት ነው፡፡ ሦስተኛው እውቀት በእምነት የተገነባ ነው፡፡ ሰው በማያምነው ነገር ላይ እውቀት ሊሰበስብ አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ የታሪክ ጽሑፍ የሚያነብ ሰው ቅድሚያ በጸሐፊው ወይም በጽሑፉ ላይ እምነት ያሳድራል፡፡ ታሪኩን የሚቀበለው እንደምንጭ የሚጠቅሰው አስቀድሞ እምነት ስላሳደርንበት ነው፡፡ ሰው ሳያምን አይቀበልም ሳይቀበል አይመረምርም አያጠናም፡፡ስለዚህም ያለ እምነት እውቀት አይገኝም የማያምን ቢኖር ግን ፍጹም እምነት ስለሌለው ለማወቅ ተነሳሽነት የለውም፡፡የሚያምንና የማያምን ሰው ነገሮችን የሚረዱት እንደ እምነታቸው መጠን ነው፡፡
በርግጥ ሰው በተፈጥሮ እውቀቱ በፍኖተ አእምሮ በእግረ ልቡና አምላኩ ወደ ማወቅ ሊደርስ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ ከተጓዙት መካከል አባታችን አብርሃም በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች አምላካቸውን ወደ ማወቅ የደረሱት ሁለት ነገር አስተባብረው በመገኘታቸው ነው፡፡ማመንና መታመንን፡፡ ያለ እምነት በእውቀት በአመክንዮ ወይም በሳይንስ የሚደረግ ምርምር ውጤቱ አምላክን ወደ መካድ የሚመራ ነው፡፡ አባታችን አብርሃም ሰማይና ምድርን የፈጠረው ማን እንደሆነ ባያውቅም አንድ ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እንዳለ አስቀድሞ አመነ፡፡ በኋላም አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ ብሎ በእምነት ወደ አምላክ ጸለየ፡፡እምነቱን በመታመን ገለጸ፡፡ ስለዚህ አብርሃም በፍኖተ አእምሮ ቢጓዝም እንዲጓዝ ያደረገው እምነቱ ከእግዚአብሔር መገለጥ ጋር ተዳምሮ ለእውነተኛ እምነት በቅቷል፡፡ማመን ከእውቀትና ከምክንያት በላይ መልካም ፈቃድና ፍላጎት ይጠይቃል፡፡ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ ‹‹የማምነው ለማወቅ እንድችል ነው--I believe in order that I may know›› ይላል፡፡ ሮማዊው ቅዱስ ኦገስቲን በበኩሉ ‹‹በነገረ ሃይማኖት ረገድ ዕውቀት በምክንያት አትወሰንም፤በልብ መሻት እንጂ…እምነትን የተመለከተ አመክንዮ በነጠላ ግለሰብ አይደመደምም (በማዕከላዊት) ቤተ ክርስቲያን እንጂ-- [to believe] is an act of intellect determined not by the reason, but by the will….the final authority for the determination of the reason in faith lies not with the individual, but with the Church itself.›› ይላል፡፡
ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያትም ይህንን በተመለከተ በመልክታቸው በጎልህ አስፍረውታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከማወቅ በፊት አስቀድመን ማመን እንዲገባ ሲነግረን ‹‹ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት…›› ኤፌ 4÷13 ቅዱስ ዮሐንስም ይህንን በተመለከተ ሲገልጥ ለተቀበሉት በስሙም ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው›› ይህም አስቀድሞ በእምነት መቀበል እንዲገባ የሚያስገነዝብ ነው (ዮሐ 1÷13) በወንጌልም ሰፍሮ እንደምናነበው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ እንሆንህ አምነናል አውቀናልም›› ብሏል (ዮሐ 6÷69) ከላይ ለዘረዘርነው ነጥብ አስረጅ ነው፡፡
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment