Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሰባት




አስማተ አምላክ(የአምላክ ስሞች)
ስሙ ማን ነው? /ዘጸ.3፡13/
የአንድ አምላክን መኖር ለአመነ ሰው የአምላኩን ስም ማወቅ ይጠቅበታል፡፡ ሰው የአምላኩን ስም የሚያውቀው ጠርቶ እንዲገናኝበት ብቻ ሳይሆን ስመ ባሕርይውን የሚገልጥ ክቡር ነውና የሚገባውን ክብር እንዲሰጥም ነው፡፡ የአምላካችን ስሙ በራሱን ለሰው የገለጠበት እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አገላለጽ ከሆነ እግዚአብሔር ‹‹እግዚአብሔር›› ነኝ ሲል የገለጠው ከሙሴ በኋላ ነው ከዚያ በፊት ግን ‹‹ሁሉን ቻይ አምላክ›› ነኝ እያለ ይገለጥ ነበረ ከነአብርሃም በኋላ ሙሴንም በደብረ ሲና ያለው ይህንኑ ነው፡፡(ዘጸ 3÷6) በኋላ ግን ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ(ኤልሻዳይ) ተገለጥሁ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር›› ብሎታል(ዘጸ 6÷3) ይህም እግዚአብሔር በስሙ የሚገለጠውን ክብሩን አውቆ ለመጥራት ማስተዋልና ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ እንደሚገባን ያስገነዝበናል፡፡
የእግዚአብሔር ስም ሥራውን ባሕርዩ ይገልጻል፡፡ (ዘጸ 15፥3) ኩሉ በላይ የእግዚአብሔር ስም ሥርውን እንደሚገልጽ እግዚአብሔር ወልድ በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ የወጡለት ስሞች ይገልጻሉ፡፡ ኢየሱስ ማለት አዳኝ ማለት ነው ይህም አምላክነቱን ይገልጻል፡አምላካችን እግዚአብሔር በተለያዩ ቋንቋዎች የተለያዩ ስሞች አሉት፡፡ በእያንዳንዱ ቋንቋ ውስጥ የእግዚአብሔርን ስም ብንመረምረው እግዚአብሔርን የሚጠሩት በፈጣሪነቱ ፥ በኃያልነቱ ፥ በቸርነቱ ፥ ሁሉን በአድራጊነቱ ፥ በዘላለማዊነቱ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ሁሉም በየቋንው ለፍጡር ሊሰጠው በማይገባ ስም አምላኩን እንደሚጠራ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ስሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ ስፍራ ተጽፎ እናገኟለን፡፡
1. የአንድነት ስሞች (On the Level of Ousia) ፡- አምላክ /መዝ.17፡31/፣ መለኮት /ሮሜ.1፡20-22/፣ ኤልሻዳይ /ዘፍ.17/፣ ያህዌ /ዘጸ.6፡3-8/፣ አዶናይ- ጌታ ማለት ነው /አዶኒ ማለት ጌታዬ / ማለት ነው፡፡ /ሕዝ.7፡2-5/፣ እግዚኣ ፀባዖት /ኢሳ.6፡3/፣ ኤሎሄ /መዝ.21፡1፣ ማቴ.27፡45/፡፡ ኤል- ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ኃያል አምላክ ማለት ነው፡፡ ያህዌ15- ያለና ሚኖር ማለት ነው፡፡ (ዘፍ 22፥14)፣ (ዘጸ 17፥15 ፣ ዘጸ 3፥13-14) ቴዎጎሎስ- የግሪክ ቃል ሲሆን እግዚአብሔር ወይም አምላክ ማለት ነው፡፡ ኪሪዮስ- በአማርኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ተብሎ ተተርጉሟል፡፡

2. የሦስትነት ስሞች (On the Level of Hypostasis) ፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ /የአካላት ስም፣ ማቴ.28፡19-20/፣ ልብ ቃል እስትንፋስ /የኵነታት ስም፣ መዝ.32፡6-11፣ ዮሐ.1፡1-30/፣ ወላዲ አሥራፂ ተወላዲ ሠራፂ /የግብራት ስም፣ መዝ.2፡7፣ 109፡3፣ ዮሐ.15፡26/፡፡
እነዚኽ ስሞች ስለ አንዱ እግዚአብሔር ሕላዌ መለኮትና ስለ ቅድስት ሥላሴ (ልዩ ሦስትነት) መታወቅ የተነገሩና በውስጣቸው እጅግ ብዙ ምሥጢራትን የቋጠሩ ናቸው፡፡ ከያዙት ምሥጢር በተጨማሪም በገዛ ራሳቸው ጠቋሚና አመላካች እንዲኹም አንጸባራቂ ናቸው፡፡ አስቀድሞ የገለጻቸውም ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ ሰዎች የተናገሯቸው አይደሉም፡፡ በሌላ አገላለጽ እግዚአብሔርን የምንጠራው ርሱ ራሱ ርሱን እንድንጠራበት በገለጠው መንገድ ነው፡፡
ነገር ግን እነዚኽ ከላይ የተጠቀሱት ስሞች ምናልባት ከእግዚአብሔር ባሕርይ ግብሮች አንዱን ያብራሩ እንደኾነ እንጂ ኹለንተናውን መግለጥ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ስለ ፈጠረ ፈጣሪ፣ ስለሚመለክ አምላክ፣ ሕያው ስለሚያደርግና ስለሚያድን ማኅየዊ፣ ስለሚያስተዳድርና ስለሚመግብ መጋቢ ሠራዒ፣ ኹሉን ስለሚችል ኤልሻዳይ፣ ኃያል አምላክ ስለኾነ ኤል፣ እንደ ባሕርዩ ስለሚሠራ ያህዌ፣ የዓለም ጌታ ስለኾነ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ ከዚኽ ባለፈ ግን ከቅዱሳን ወገን አንድ ስንኳ የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ ይኽ ነው ብሎ የተናገረ የለም፡፡ እግዚአብሔር ራሱም የባሕርይ ስሜ ይኽ ነው ብሎ የተናገረበት ኹናቴ የለም፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ፡- “እኔ ፊተኛ ነኝ፤ እኔም ኋለኛ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ አምላክ የለም” ብሎ እንደተናገረ /ኢሳ.44፡6/ ልዩ፣ ቅዱስ ስለኾነ የሰው ልጅ ልቡና የእግዚአብሔርን የባሕርይ ስም የመረዳት ዐቅሙ ውሱን ነው፤ ዳግመኛም የሰው ልጅ ቋንቋ የእግዚአብሔርን ስም ለመግለፅ ዓቅም የለውም፡፡
አረጋዊ መንፈሳዊ ይኽን መግለጽ ቢያቅተው የጸለየውን ጸሎት እስኪ አብረን እናድምጠው፡- “አቤቱ በምን ስም እጠራኻለኁ? አንተን የምጠራበት ስም አላውቅም፡፡ አምላክ ብልኽ የባሕርይ ስሜ አይታወቅም ትለኛለኽ፡፡ አኹንም እገሌ ተብሎ መጠራት፤ ይኽን ይመስላል ተብሎ መመሰል ካንተ የራቁ ናቸው፡፡ ክቡር ገናና ሆይ! ምን ብዬ እጠራኻለኁ? በምን እመስልኻለኁ?” /አረጋዊ መንፈሳዊ፣ ድርሳን 43፣ ገጽ 319/፡፡
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ ብቻ ሳይኾን፣ የመላእክትና የነፍስ የባሕርይ ስማቸውም ከማወቅ የራቀ እንደኾነ እንዲኽ ሲል ያስረዳናል፡- “ወዳጄ ሆይ! ጳውሎስ የተናገረውን አስተውል፡፡ አስቀድሞ የክብሩ መንጸባረቅ ካለ በኋላ ቀጥሎም በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ ብሏልና /ዕብ.1፡3-5/፡፡ ሐዋርያው የባሕርይ ስሙን የሚያስረዳ ስም ባያገኝ በግርማው ቀኝ ብሎ ተናገረ፡፡ በግርማው ቀኝ የሚለው አገላለጽ በራሱ ግን የባሕርይ ስሙን አያስረዳም፡፡ ይኽም አስቀድሜ ከተናገርኩት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድን ነገር እንረዷለን፤ ኾኖም እንደሚገባ አድርገን በቋንቋ መግለጥ አንችልም፡፡ የእግዚአብሔርን ምላቱን ስፋቱን ርቀቱን እንረዷለን፤ እንደሚገባ አድርገን ግን መናገር አይቻለንም፡፡ የጌታ የባሕርይ ስሙም እንደዚያ ነው፡፡ የባሕርይ ስሙን መርምረን ልናውቀው አንችልም፡፡ ወዳጄ ሆይ! የጌታን የባሕርይ ስሙ አይታወቅም ስለተባለ አትደነቅ፡፡ የእግዚአብሔርንስ ተወውና የአንድ መልአክ የባሕርይ ስሙም አይታወቅም፡፡ የነፍስም እንዲኹ ነው፡፡ ነፍስ ማለት የሥጋ ሕይወት መኾኗን ብቻ ያስረዳል እንጂ የባሕርይ ስሟ አይደለምና፤ ለባሕርይዋ የሚስማማ ስም የላትም፡፡” /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 2፡179-198/፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ የእግዚአብሔር የባሕርይ ስሙ ማን እንደኾነ ጠይቆ ነበር /ዘጸ.3፡14/፡፡ ርሱም፡- “ያለና የሚኖር (የምኾን፣ ኋኝ) እኔ ነኝ” ብሎታል፡፡ ነገር ግን ይኽ አገላለጽ የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ህልውናውን የሚናገር ቅጽል እንጂ የባሕርይ ስሙን አያስረዳም፡፡ ይልቁንም በዚኽ አነጋገሩ እግዚአብሔር ብቻውን እንደሚኖርና የሌሎች ፍጥረታት መኖር ከርሱ ዘለዓለማዊነት አንጻር ሲታዩ እንደሌሉ የሚያስቈጥር መኾኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የባሕርዩ ስም ያለመታወቁ ምሥጢርም እዚኹ ጋር ነው፡፡ የባሕርይ ስሙ መመርመር የማይቻለው እግዚአብሔር ለአኗኗሩ፣ ለህልውናው፣ ለኋኝነቱ ምክንያት፣ መነሻ፣ ጥንት ስለሌለው ነው፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ለመንገዱ ፍለጋ የለውም” እንዳለው ነው /ሮሜ.11፡33/፡፡ አስቀድመን “ባሕርይ ማለት አካል ከህልውና ላለው አካል የሚነገር ሲኾን ትርጓሜውም ለዚኽ ህልውና አለው ለተባለው አካል ለህልውናው (ለመኖሩ) ምክንያት፣ ምንጩ፣ ሥሩ፣ መፍለቂያው፣ መገኛው፣ ጥንቱን የሚያስረዳ ቃል ነው” ብለናልና እግዚአብሔር አስገኝ ስለሌለው የባሕርይ ስሙም አይመረመርም፡፡
ሰማዕቱ ዮስጢኖስ (Justin the Martyr) ይኽን አንቀጽ የበለጠ ሲያብራራው እንዲኽ ብሏል፡- “ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ አዳምንና ሔዋንን ሲያስታቸው ልክ እንደ ርሱ እግዚአብሔርን አልታዘዝ ቢሉ፥ እንደ እግዚአብሔር የባሕርይ አማልክት እንደሚኾኑ ነገራቸው፡፡ በዚኽ አነጋገሩም ከእግዚአብሔር ውጪ የሌሉትን አማልክት እንዳሉ አስመስሎ አሳያቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔርን አንታዘዝም ቢሉ እንደነዚኽ አማልክት እንደሚኾኑ ለማታለል እንዲመቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ይኽን የዲያብሎስ ትምህርት ያውቃል፡፡ በመኾኑም ያለና የሚኖር እኔ ነኝ በማለት ከእነዚኽ ሕላዌ ከሌላቸው ብቻ ሳይኾን ከየትኛውም ፍጥረት ጋር የማይነጻጸር መኾኑን ለሙሴ ነገረው፡፡ ሰው የዲያብሎስን ማታለል አመነ፡፡ እግዚአብሔርን አልታዘዝ ብሎም ከገነት ወጣ፡፡ ከገነት ሲወጣ ግን ከእግዚአብሔር ሳይኾን ከዲያብሎስ በተማረው መሠረት ህላዌ የሌላቸውን የሌሎች አማልክት መኖርን በልቡናው ይዞ ወጥቷል፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት እንዲወጡ ያደረጋቸው የተሰጣቸው ትእዛዝ ከባድ ስለነበረ አይደለም፤ የባሕርይ አማልክት መኾን ስለፈለጉ እንጂ፡፡ ከገነት ሲወጡ የእግዚአብሔር ትእዛዝ በመተላለፋቸው እንጂ ሌሎች አማልክት አሉ በማለታቸውም ጭምር እንደወጡ አልገባቸውም ነበር፡፡ እንዲኽም በመኾኑ ከርሱ በኋላ የተገኙ ሰዎችን እንኳን አማልክት ብለው ለመጥራት አላንገራገሩም፡፡ ይኽ የአማልክት መኖር የሐሰት ትምህርት ኹሉ የተማሩት ከሐሰት አባት ከዲያብሎስ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ብዙ አማልክት የሚለው የሐሰት ትምህርት በሰው ልጆች ላይ እንደነገሠ ዐውቆ ይኽን አስተሳሰብ ከልጆቹ ያርቅ ዘንድ ወድዶ ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ ያለና የሚኖር እኔ ነኝ አለው፡፡ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ለመምራት ከኹሉም በፊት እግዚአብሔር ብቸኛው አምላክ መኾኑን ማወቅ ነበረበትና፡፡” / ANF01. The Apostolic Fathers with Justin Martyr and Irenaeous, Wm. B. Eerdmans Publishing Co., reprint 2001, pp 464/፡፡
ከዚኽ መረዳት እንደምንችለው እነዚኽ በዲያብሎስ የተዋወቁት ጣዖታት ጥንት፣ መነሻ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለአኗኗሩ መነሻ የለውም፡፡ ስለዚኽም “ያለና የሚኖር፣ ኋኝ እኔ ነኝ” አለ፡፡
ይቆየን ይቀጥላል
                                                                                                                                      ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment