Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አስራ አራት





   የስም ሦስትነት
ይህም የሥላሴ አካል ስም ያለው ነው ስለዚህም በስም ሦስትነት አላቸው እንላለን፡፡ ስማቸውም አብ ወለድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ (ማቴ 28፥19) “እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ፣በወለልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርቴ አድርጓቸው…..”(2ኛ ቆሮ 13፥14)
የሥላሴ የስም ሦስትነት የአንዱ ወደአንዱ አይፋለስም ይህም አብ ይባላል እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይባልም፣ ወልድም አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይባልም፣መንፈስ ቅዱስም ወልድ ወይም አብ አይባልም፡፡ አብም አብ ነው፣ ወልድም ወልድ ነው፣መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሦስቱም በየስማቸው በያካላቸው ጸንተው ይኖራሉ/አግናጢቲዎስ ሰማእት 4.ሃይማኖተ አበው ምዕ11 ክፍል1 ቁጥር7-8/
አካልና ስም
በሕገ ፍጥረት አካልና ስም ተከታትለው የሚመጡ ነገሮች እንደሆኑ እናስተውላለን፡፡ አካል ይቀድማል ስም ተከትሎ ይመጣል፡፡ የሰው ልጅ ስም የሚወጣው በልደት ሥጋዊ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ ነው መጽሐፍ ቅዱስም ይህንን የሕገ ተፈጥሮ መዝግቦ እናገኛለን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ስም ይወጣለታል(ሉቃ 1÷70) ሌላው ሥነ ፍጥረት ብንመለከት እስከ እለተ ሠሉስ ያሉትን እግዚአብሔር ስም ያወጣላቸው ሲሆን የጠቀሩትን አዳም ስም ሰጥቶቸዋል፡፡(ዘፍ 2÷1)
ይህ ከላይ የጠቀስነው እውነት ለሥነ ፍጥረት ሁሉ የሚሠራ ሐቅ ነው፡፡ ለቅድስት ሥላሴ ግን እንዲህ አይደለም በሥላሴ ዘንድ
አካላትአስማትን አይቀድምም አካል ስም አንድ ሆኖ በአንድ ጊዜ የተገኘ እንጂ፡፡ በእርግጥ አስማትም ሆኑ አካላት የተገኙበት ጊዜ አለ
ማለታችን አይደለም፡፡ ተገኙ ማለታችን እኛ ፍጡራኑ ያወቅንበትን ጊዜ ለማመልከት ነው እንጂ፡፡ ይህም የሆነው አካልና አካላዊ ግብር የማይቀዳደሙ በመሆናቸው ነው ይህን ግብር ይገለጥ ዘንድ የምንጠራው ይህ ስምም ከአካሉ መገኘት በኋላ የተገኘ ነው አንልም፡፡
የግብር ሦስትነት
ይህም የሥላሴ ስም ግብር ያለው ነው በግብርም ሦስትነት አለው፡፡ ወሠለስቱ ግብራት እንዲሉ አበው በግብር ሦስት ናቸው ስላሉ ግብር የተባለው ሁሉ አይደለም በተለየ ግብር ሦስት ናቸው ስንል ነው እንጂ የተለየ ግብራት ምንድን ናቸው ቢሉ መውለድ ማስረጽ መወለድ መስረጽ ናቸው፡፡ ይህም ማለት አብ ወላዲ አስራጺ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ነው፡፡ ይህም ማለት አብ ወልድን ይወልዳል መንፈስ ቅዱስን ያሠርጻል፣ ወልድ ይወለዳል፣ መንፈስ ቅዱስ ይሰርፃል፡፡ በሥላሴ ዘንድ በግብር መፋለስ የለም ይህም ማለት፡፡
  1.         አብ ይወልዳል ያሠርጻል እንጂ እንደ ወልድ አይወለድም፣ እንደ መንፈስ ቅዱስ አይሠርጽም
  2.   ወልድ ይወለዳል እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም፣ እንደ መንፈስ ቅዱስ አይሠርጽም
  3. መንፈስ ቅዱስ ይሠርጻል እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም፣ እንደ ወልድ አይወለድም
የአብ ከዊን ልብነት የመንፈስ ቅዱስ ከዊን እስትንፋስ እንደሆነ ሁሉ የወልድም ከዊን ስሙ ቃል ነው፡፡ከልብ ተገኝቶ ከአንደበት ወጥቶ ሩቅ ሄዶ ሥራ የሚሰራ ቃል እንጂ እስትንፋስና ልብ አይደሉም፡፡ ወልድም ረድኤተ እግዚአብሔር ሩቅ ወደ ነበረች ዓለም መጥቶ ዓለምን አድኖ መልሶ አርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ቃል ይህንን ሲሰራ ከልብ ወጥቶ ተለይቶ ከእስትንፋስ ተለይቶ አይደለም ከልብ ይነቃል በእስትንፋስ ሠረገላነት ወደ ውጭ ይወጣል ከልብ አይታጣም ከእስትንፈስ አይለይም ማለት ነው፡፡ወልድም ሰው የሆነው ባለመለየት ነው፡፡ ለእመቤታችን መልአኩ ሲያበስራት መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ብሏታል የአብን ሱታፌ ቅዱስ ኤፍሬም ሲናገር ፈነወ ለነ መዝራእቶ ልዑለ ብሏል(ውዳ ማር ዘሰኑይ) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ሰው መሆኑን አበው ከአባቱ ዕሪና ሳይለይ በማኅጸነ ድንግል ተወሰነ ከእርሷም ተወለደ ብለዋል(ሃይ አበ ም48÷2)
አብ አስገኝና መሠረት ስለመሆኑ
መወለድና መስረጽ አንድ ወገን ሆኖ አብ አስገኝ የሁሉ መገኛና ምንጭ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ አብ አይወለድም አይሰርጽም እርሱ ወላዲ አስራጺነው እንጂ እርሱ ሁሌም በአስገኝነቱ የጸና ነው አብ አባት የሌለው አባት አስገኝ የሌለው አስገኝ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ ሃይ አበው ኪራኮስ ገጽ 397)
ስለዚህ የአብ ግብሩ ወልድና መንፈስቅዱስን መውለድና መስረጽ ቢሆንም ቅሉ ወላዲውና አስራጺው አብ ቀዳሚ ነው ማለት አይደለም፡፡ በማዕረግ አይበላለጡም በዘመን አይቀዳደሙም፡፡ መጻሕፍትም የአብን አስገኝነት ይመሰክላሉ በወንጌል እንደምናነበው ጌታችን ‹‹ እስመ አነ እምኀበ እግዚአብሔር አብ ወጻእኩ ወመጻእኩ ዮሐ 8÷42 እንዲሁም ስለመንፈስ ቅዱስ ሲናገር ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ ዘይወጽእ እምኀበ አብ ውእቱ ሰማዕትየ ብሏል (ዮሐ 15÷26)
ቀድመን በምሳሌ እንደጠቀስነው የመወለድንና የመስረጽን ሁኔታ በፀሐይ ምሳሌነት ማወቅ እንችላለን ከብርሃን አክልና ባሕርይ ብርሃን እንደሚወጣ ከሙቀት አካልና ባሕርይ ሙቀት እንደሚገኝ እንዲሁም ወለድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ መለኮታዊ አካልና ባሕርይ ይገኛሉ ይወጣሉ፡፡ ይህም ለሥላሴ ምሳሌ ነው፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ ተብሎ በጸሎተ ሃይማኖት የጠገለጠው ክፍለ ንባብ ለዚህ አስረጅ ነው (ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ 3 ማቴ 3፥17 ዕብ 1፥5 ሉቃ 1፥35 ዮሐ 3፥16-18 ዮሐ 15፥26)

በሥላሴ ዘንድ መቅደም መበላለጥ የለም
አብ ወልድን ቢወልድ መንፈስ ቅዱስን ቢያሠርጽ አይበልጣቸውም፡፡ በሥላሴ ዘንድ መቅደም መበላለጥ የለም፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እኩል ናቸው፡፡ አብ የነበረበት ወልድና መንፈስ ቅዱስ ያልነበሩበት ዘመን የለም ፡፡ ወልድ የነበረበት አብና መንፈስ ቅዱስ ያልኖሩበት ዘመን የለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ የነበረበት አብና ወልድ ያልነበሩብት ዘመን የለም፡፡ ሦስቱም መጀመሪያና መጨረሻ ናቸው፡፡
ዳግመኛ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብን እንዲበልጠው በሥላሴ መበላለጥ አለባቸው ቢሉ አብርሃም ይስሐቅን የበለጠው በልደት መቀዳደም ስላለባቸው ነው ለሥላሴ እንዲህ አይደለም አብርሃም በፍጥረት ሥርዓት ይስሐቅን እንደሚያዛው አይደለም ለሥላሴ እንዲህ አይደለም እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም
ወልድ ከአብ ተወለደ ሲሉና ይስሐቅ ከአብርሃም ተወለደ ሲሉ ልዩነት አለው፡፡ የወልድ ልደት የብቻው ነው መገናኛ የላቸውም የብቻው ነው ማለታችን ሰው በሕገ ተፈጥሮ ከእናት ከአባት ይወለዳል ወለድ ግን እምቅድመ ዓለም ያለ እናት ተወልዶልና ይህ ልደት ከምድራዊው ልደት ይለያል፡፡ ሌላው ሰው ሲወለድ ከእናት ከአባት ባሕርይ አካል ከፍሎ ይወለዳል የወለድ ልደት ግን ተከፍሎ የለበትም፡፡ ወለድ አካሉ ከአብ አካል ሳይከፈል እንበለ ዘር ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምኣካል ከአብ ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምኣካል ሠረጸ እንላለን እንጂ በሕገ ተፈጥሮ እንዳለው አይደልም፡፡አብ ወልድን ወለደው ማለት ከአካሉ ከባሕርይው አስገኘው ማለት ነው፡፡ ወልድ ከአብ ተወለደ ማለት አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡ አብ መንፈስ ቅዱስን አሠረጸው ማለት ከአካሉ ከባሕርይው አስገኘው ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሠረጸ ማለት አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡
መስረጽና መወለድ ሁለቱም ከአብ መገኘት ናቸው ልዩነት የላቸውምን
ተወለደም ወጣ ሠረጸም ወጣ ነው እንዲህ ከሆነ ወልድ ሠረጸ መንፈስ ቅዱስን ተወለደ ማለት ይገባልን የሚለውን ጥያቁ መመለስ ያሻል፡፡ ይህንን አባቶች በምሳሌ ያብራሩታል፡፡ ከልብ ቃልና እስትንፋስ ይወጣል ስለወጣ ግን ቃልን ተናገረ እንላለን እስትንፋስን ተነፈሰ እንላለን እንጂ ቃል ተነፈሰ እስትንፋስን ተናገረ አንልም እንደዚሁ ሁሉ ተወለደን ሠረጸ ሠረጸን ተወለደ ሊሉ አይገባም፤፤
ነገረ መንፈስ ቅዱስ
የመንፈስ ቅዱስ መስረጽ
በጉባኤ ቁስጥንጥንዮስ አራተኛ ጉባኤ ላይ የተነሳው የመንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሰረጸ ነው የሚለው ትምህርት የሮም ቤተ ክርስቲያን ከጉባኤው በፊት በነበረው የሃይማኖት መግለጫ(አንቀጸ ሃይማኖት) ላይ መጨረች፡፡ 27 ይህ ትምህርት ከዚህ በፊት ያልነበረ ስርዋጽ ነውና ይህን በመቃወም የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሮም ቤተ ክርስቲያን ፖፕን ወቀሱ መናፍቅ ነህም አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ጉባኤው ተደረገ የሮም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነችና የእኛ ሐሳብ ይደመጥ አለች ይህንን ምሥራቃውያን ተቃወሙት ፓፕ ኒኮላስም በዚህ ጉባኤ ላይ የስሕተት ትምህርቱን አጸደቀው፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እስካሁን ድረስ ዘሰረጸ እምአብ ወእም ወልድ ብለው ያስተምራሉ፡፡
የካቶሊካዊያን ትምህርት
ዘሰረጸ እምአብ ወእም ወልድ
የካቶሊክ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት የሚቀዳው ከአጉስቲን ከተባለ የካቶሊክ የነገረ ለመለኮት ሊቅ ነው፡፡ በዚህ ሰው ትምህርት መሠረት በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት የአብ ተወላዲነትና የመንፈስቅዱስ መስረጽ በደንብ አልተብራራም ይህንን ለመፍታትም አጉስቲን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ባሕርይ አንዱ ፍቅር ነው፡፡ አባት(እግዚአብሔር አብ) ፍጹም ፍቅር ነውይህንንም ለልጁ ያጋራዋል ስለዚህም ልጁ(እግዚአብሔር ወልድ) ፍቅሩን የሚያጋራ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ የፍቅር ሕብረት ነው ወይም አጣማሪ ነው፡፡ በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ፍቅር ለእግዚአብሔር ባሕርይ ነው፡፡
ይህ ትምህርትን በአጉስቲንም አማካኝነት የተስፋፋ ትምህርት ነው፡፡ በወቅቱ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ የነበረው ፒዮትዮስ ይህንን ትምህርት መቀበል እንደሌለባቸው አሳማኝ በሆነ አቀቀራረብ ተቃወመ፡፡ ‹‹አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ተመሳሳይ ግብራትን አይጋሩም አይ ይጋራሉ ምንል ከሆነ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሰርጻል ካልን ከራሱ ከመንፈስ ቅዱስም መስረጽ አለበት የሚል ነው ስለዚህም አለ በመደምደሚያው ቄጶዶልቅያ አባቶች ትምህርት ትክክል ስለሆነ ሌላ መጨመር አያስፈልግም›› በማለት ትምህርቱን ከመቀበል እንቢ አለ፡፡

የኦርቶዶክስ ትምህርት
የካቶልክ ትምህርት
የፒዮትዮስ መልስ
አብ ወላዲ አስራጺ
አብ ወላዲ አስራጺ
አብን ወላዲ አስራጺ
ወለድ ተወላዲ
ወለድ ተወላዲ አስራጺ
ወለድ ተወላዲ አስራጺ
መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ
መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ
መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ አስራጺ
የካቶሊካዊያኑ የነገረ መለኮት ሊቅ አጉስቲንና በእኛ መካከል ያለው የአስተምህሮ ልዮነት መነሻው ይህ ቅድስት ሥላሴ ከአብና ከወልድ ይሰርጻል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የአጉስቲንም አቀራረብ ይህን ትምህርት ለማስገባት ይመስላል መንፈስ ቅዱስ የፍቅር ሕብረት ነው ለአብና ለወልድ ብሎ ያስቀመጠው ከአብም ከወልድም የሰረጸ ነው ለማለት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለመንፈስ ቅዱስ መስረጽ ምን ይላል
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ወሶበ መጸአ ጰራቅሊጦስ ዘአነ እፌኑ ለክሙ እምኅበ አብ መንፈስ ጽድቅ ዘይወጽእ እምኅበ አብ ውእቱ ሰማዕየ›› ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል፡፡ ይህ ቃል ስለመንፈስ ቅዱስ ጌታችን የተናገረበት ክፍለ ትምህርት ነው ስለመንፈስ ቅዱስ ሲነግረን ከአብ የሚወጣ ማለቱን ልብ በሉ ከአብ የሚወጣ አለ እንጂ ከእኔ የሚወጣ አላለም ስለዚህም የመስረጽ ግብር የማን እንደሆነ የማስረጽ ግብር የማን እንደሆነ በዚህ የመጽሐፍ ክፍል በጉልህ ተጽፎ እናገኛለን፡፡(ዮሐ 1526 ዮሐ 1416)
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment