ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን
ትንሣኤ የሚለው ቃል ተንሥአ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን መነሣት ማለት ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ማለት የሙታን መነሣት ማለት ነው፡፡ ይህም ተለያይተው በተያየ ስፍራ ይኖሩ የነበሩ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው መነሣት ከሞት በኋላ በነፍስና በሥጋ ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ይህ የሙታን መነሣት ሁኔታ በሰው ልጅ አእምሮ ሊደርስበትና ሊታወቅ የማይችል ረቂቅ ጥበብ ስለሆነ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ተብሎ ይጠራል፡፡
በዚህ በምስጢረ ትንሳኤ ሙታን ትምህርት ውስጥ ሁለት ዐበይት ክፍሎች አሉ እነርሱም፡-
U የክርስቶስ ትንሣኤ
U የሰው ልጆች ትንሣኤ ናቸው
የክርስቶስ ትንሣኤ
መድኀንዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም በገባው ቃልኪዳን መሠረት በአይሁድ እጅ መከራ መስቀልን ከተቀበለ በኋላ ነፍሱን በራሱ ስልጣን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ዐርብ በ11 ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ መስፍኑ ጲላጦስን አስፈቅደው ከመስቀል አውርደው ዮሴፍ ራሱ ባሰራው መቃብር በንጹህ በፍታ ገንዘው ቀብረውት ገጥመው ሲሄዱ ጸሐፍት ፈሪሳውያንና መስፍኑ በመቃብሩ ላይ ማኅተማቸውንና ጠባቂዎችን አኖሩ፡፡ (ማቴ 27÷57-66 ማር 15÷42 ሉቃ 23÷50 ዮሐ 19÷38-42)
በሦስተኛው ቀን እሑድ በእኩለ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ ይጠብቁ የነበሩ ጠባቂዎችም ደንግጠው ተበታተኑ በመቃብሩ ዙሪያ ቅዱሳን መላዕክት ታዩ (ማቴ 28÷1-15 ማር 16÷11-15 ሉቃ 24÷1-43 ዮሐ 20÷1-25 1ኛ ቆሮ15-1 ሮሜ 6÷9-15)
ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ3ኛው ቀን ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣው በባሕርይ አባቱ በአብ ሥልጣን በራሱ ስልጣን እንዲሁም በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ነው፡፡ (ሐዋ 2÷32' 1ኛ ቆሮ 15÷15 ሮሜ 6÷4 ፤ ዮሐ 2÷19-22 ዮሐ 10÷17-18 ሮሜ 8÷11)
ለክርስቶስ ትንሣኤ የተነገሩ ትንቢቶች
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ተሰቅሎ በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት አድሮ ለመነሣቱ ከተነገሩት ትንቢቶች መካከል
o መዝ 3÷5 ‹‹እኔ ተኛው አንቀላፋሁ እግዚአብሔር ደግፎኛልና ነቃሁ››
o መዝ 67/68÷1-2 ‹‹እግዚአብሔር ይነሣ ጠላቶቹም ይበተኑ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሸሹ ጢስ እንደሚበተን እንዲሁ ይበተኑ››
መዝ 77/78÷65 ‹‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ የዘላለም ኃሣር ሰጣቸው (መዝ 11/12÷5-6 ዮሐ 2÷19 ማቴ 17÷20-23)
ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የተመሰሉ ምሳሌዎች
ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ትንቢት እንደተነገረ ሁሉ የተመሰሉ ምሳሌዎች አሉ፡፡
ዘፍ 22÷1-14 በዚህ ምዕራፍ እንደምናገኘው እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አብርሃም በኮሬብ ተራራ አንድ ልጁን እንዲሠዋ ባዘዘው ጊዜ ለመሥዋዕት የሚያስፈልገውን እሳት' እንጨት' ካራ/ቢላ/ይዞ ሦስት ቀን ሄዶ በኮሬብ ተራራ በእፀ ሳቤቅ የታሰረ በግ ተሰጠው፡፡ በልጁ ምትክ በጉ ተሠዋ፡፡ ይህ ምሳሌነት አለው
o ይስሐቅ በአብርሃም ኅሊና ከሦስት ቀን በፊት መሠዋቱ/መታረዱ/ ክርስቶስ በሥጋ የመሞቱ ምሳሌ
o ከሦስት ቀን በኋላ ልጁ ይስሐቅ ሞት ሳያገኘው ወደ ቤቱ መመለሱ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የመነሣቱና በአባቱ ቀኝ የመቀመጡ ምሳሌ
o ቢላው በይስሐቅ ላይ አለማረፉ ጌታ በባሕርየ መለኮቱ ሕማም እንደሌለበት ያስረዳል፡፡ ቢላው በበጉ ላይ ማረፉ ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ መሞቱን የሚያስረዳ ነው
o አብርሃም የእግዚአብሔር አብ ይስሐቅ የወልድ በግ የሥጋ ኮሬብ ተራራ የጎለጎታ እንጨትና እሳት የ13ቱ ሕማማተ መስቀል ምሳሌ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ይህ ሁኔታ የክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ጽፏል፡፡ (ዕብ 11÷17-19)
ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት መዓልት ሦስት ለሊት በከርሠ መቃብር አድሮ መነሣት
ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል ዮናስ ሦስት ቀንና ሦስት ለሊት ማደሩ ስለ ራሱ ሞትና መቃብር እንዲሁ መነሣት ምሳሌ አድርጎ ጌታችን ራሱ የተናገረው ንግግር ነው፡፡ (ማቴ 12÷40)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምበት የቀን አቆጣጠር መዓልት ይስህቦ ለሌሊት ወሌሊት ይስህቦ ለመዓልት ማለትም አንድ ድርጊት ቀን ቢፈጸም ሌሊቱን ስቦ/ሌሊቱና ቀኑ በአንድነት በአንድ ቀን ይቆጠራል፡፡ እንደዚሁ ሌሊት አንድ ሥራ ቢሰራ ቀኑን ስቦ ከቀኑ ጋር አንድ ሆኖ ይቆጠራል፡፡
በዚህ አቆጣጠር ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር የተቀበረው ወይም ያደረው አርብ 11፡00 ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ ስለሆነም አርብ ቀን አርብ ሌሊትን (በተለምዶ ሐሙስ ሌሊትን) ስቦ በአንድነት አንድ ቀን አንድ ሌሊት ቅዳሜ ቀን ቅዳሜ ሌሊትን ስቦ( በተለምዶ አርብ ሌሊትን) ሁለት ቀን ሁለት ሌሊት ይሆናል፡፡ እሑድ ሌሊት (በተለምዶ ቅዳሜ ሌሊት) ማለትም ጌታ የተነሣበት ሌሊት ቀኑን ስቦ ከቀኑ ጋር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በመሆን ይቆጠራል፡፡ በዚህ የተነሣ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አደረ ተብሎ ይነገራል፡፡
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment