ምሥጢረ ሥላሴ በዘመነ ብሉይ በብሉይ ኪዳን ከተገለጠው
ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት በመጽሐፍ ቅዱስ በዘመነ ብሉይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል
- (ዘፍ 1፥26) “እግዚአብሔርም አለ ሰውን ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” ከዚህ አባባል የምንረዳው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በአካል አንድ ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ “እግዚአብሔርም አለ” የሚለው ቃል በመለኮታዊው ባሕርይ አንድ መሆኑን ሲገልጽ “በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” የሚለው ደግሞ ብዛትን ከአንድ በላይ መሆኑን ይገልጽልናል፡፡
- (ዘፍ 3፥22)”እግዚአብሔር አምላክም አለ እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡፡” “እግዚአብሔር አምላክም አለ” ብሎ አንድነቱን “ከእኛ” የሚለው አባባል ደግሞ እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው የሚለው እምነት ፍጹም ስህተት መሆኑን ይገልጽልናል፡፡ አንድ ቢሆን ኖሮ “እንደ እኔ ሆነ” ባለ ነበር፡፡ ይህ አባባል ሁለትና ከዚያ በላይ መሆኑን ያስረዳል፡፡
- (ዘፍ 11፥6-7) “እግዚአብሔርም አለ ……ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማ ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው፡፡” ሁለት ገጽ የሚለው ስህተት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ምክንያቱም ሁለት ቢሆኑ ኖሮ “ና እንውረድ” ባለው ነበርና፡፡
- (ዘፍ 18፥1-15)ያለውን ገጽ ንባብ ስንመለከት የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ እስኪ ገጸ ንባቡን እንመልከት፡-
“በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር
በመምሬ አድባር ዛፍ ስር ተገለጠለት” ይህ ንባብ እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደተገለጠለት በግልጽ ያስረዳል፡፡ ቀጥሎም “ዓይኑንም
አነሳና እንሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፡፡ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ”› ብሎ ሦስትነታቸውን ያስረዳል፡፡
ከዚያም ከቁጥር 3 ላይ እንዲህ ይላል “እንዲህም አለ፡- አቤቱ ከፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምንሀለው”
ብሎ በአንድነቱ ሲያናግረው እናያለን “ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ ከዚህ ዛፍ በታች ዕረፉ ጥቂት እንጀራም ላምጣላችሁ
ልባችሁን ደግፉ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መታችኋልና፡፡ እነርሱም እንዳልክ አድርግ አሉት” ይህ ደግሞ በሦስትነታቸው
እያናገራቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አብርሃምም ወደ ድንኳኑ ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና ሦስት መስፈሪያ (ሦስተነቱን)የተሰለቀ
ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ ለውሽውም (አንድነቱን)…….. እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፡፡ “እነርሱም በሉ” ሲል ደግሞ ሦስትነቱን
ያመጣዋል፡፡ በቁጥር 9 ላይ ደግሞ እንዲህ የሚል ንባብ እናገኛለን “እነርሱም ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት አሉት” ብሎ ሦስትነታቸውን
ሲገልጽ ዝቅ ብሎ ቁጥ 10 ላይ ደግሞ ‹‹እነርሱም (ሦስትነታቸውን) የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደናነንተ በእውነት እመለሳለሁ
ሚስትህ ሣራ ልጅን ታገኛለች አለ” ይህ ደግሞ የበለጠ የእግዚአብሔርን አንድነት እና ሦስትነት ያስረዳል ምክንያቱም “እነሱም” ብሎ
ጀመረና “እመለሳለው”፣ “አለ” ብሎ ንግግሩን ይቋጫል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ምእራፍ ላይ የእግዚአብሔርን አንድነት እና ሦስትነት
መረዳት እንችላለን፡፡
በተጨማሪም (ኢሳ48፥16 ፣ ዘኁ6፥24 ፣ ዘፍ32፥5 ፣ መዝ1171 ፥ 6-17 ፣ ኢሳ6፥8) ተመልከት፡፡
ምሥጢረ ሥላሴ በዘመነ ሐዲስ
በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔር አንድነት በግልጽ በጉልህ ተጽፎ የምናገኘበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ
(ማቴ 3፥17) “እነሆ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ በርግብ አምሳል ሲወርድ (መንፈስ ቅዱስን) በርሱም ላይ ሲቀመጥ
(በወልድ ላይ) አየ እነሆም ድምጽ ከሰማያት በርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው (አብ) “
§ ማቴ 28፥19 “……በአብ፣ በወልድ
በመንፈስ ቅደዱ ስም…….”
§ ሉቃ 3፥21-22 በጌታችን ጥምቀት
ጊዜ የተገለጠው ነው፡፡
§ ሉቃ 1፥35 “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል የልዑል ኃይልም ይጸልልብሻል(አብን) ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ
ይባላል(ወልድን) “ በተጨማሪም (1ኛ ቆሮ 1፥1-2፣ 1ኛ ዮሐ 5፥8) ተመልከት
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment