Monday, 24 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሃያ አራት



                                  
ምሥጢረ ቁርባን
ቁርባን የሚለው ቃል የሱርስት ሲሆን ትርጉሙም መንፈሳዊ አምኃ 'መባዕ ለአምላክ የሚቀርብ የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ ቁርባን ከእህል ወገን ነው የሚዘጋጀው፡፡ በምሥጢረ ቁርባን ካህኑ በጻሕል ወይኑን በጽዋ አድርጎ በጸሎተ ቅዳሴው ባርኮት ሕብስቱ ወደ ሥጋ መለኮት ወይኑ ወደ ደመ መለኮት የሚለወጥበት ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን የቁርባን ምሳሌዎች
የመልከ ጼዴው መሥዋዕት
አብርሃም አባታችን ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ ሲሄድ መልከጼዴቅ ሕብስተ አኮቴት እና ጽዋዕ በረከት ይዞ መገናኘቱ የቁርባን ምሳሌ ነው፡፡ (ዘፍ 14÷17) መልከጼዴቅ የክርስቶስ አብርሃም የምዕመናን ዮርዳኖስ የጥምቀት ሕብስተ አኮቴት የሥጋው ጽዋዐ በረከት የደሙ ምሳሌ ናቸው፡፡ አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ በረከትን መቀበሉ ምዕመናንም ከተጠመቁ በኋላ የጌታን ሥጋ እና ደም የመቀበላቸው ምሳሌ ነው፡፡

እስራኤላውያን በምድረ በዳ የወረደላቸው መና (ዘጸ 16÷13' ዮሐ 6÷25)
እስራኤላውያን የምዕመናን ደመናው የእመቤታችን መናው የቅዱስ ሥጋው ውሃው የክቡር ደሙ ከነዓን የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናቸው፡፡ እስራኤላውያን መናውንና ውሃውን እየጠጡ ወደ ከነዓን እንደገቡ እኛም የጌታን ሥጋ እና ደም የተቀበልን የዘላለም ሕይወት ለማግኘታችን መንግሥተ ሰማያት ለመግባታችን ምሳሌ ነው፡፡

ኢሳይያስ ከለምጽ የዳነባት ፍሕም (ኢሳ 6÷6-8)
መልአኩ የዲያቆናት አንድም የቀሳውስት ኢሳይያስ የምዕመናን ጉጠቱ የዕርፈ መስቀል አንድም የሥልጣነ እግዚአብሔር ፍሕሙ የደሙ አንድም የሥጋ ወደሙ ለምጹ የፍዳ የመርገም ኃጢአት ምሳሌ ነው፡፡ ኢሳይያስ ከለምጹ በፍሕሙ እንደዳነ ምዕመናንም ሥጋ ወደሙን ተቀብለው የኃጢአት ሥርየት የማግኘታቸው ምሣሌ መልአኩ ፍሕሙን በእጁ ሣይሆን በጉጠቱ መያዙ ዲያቆናትም ሥጋ ወደሙን በእጃቸው መንካት አይቻላቸውምና፡፡
የፋሲካው በግ(ዘጸ 12÷1-52)
ይህ እውነተኛ ታሪክ በኋላ ዘመን /ለሐዲስ ኪዳኑ የጌታ ሥጋና ደም/ ለሚሆነው ምሣሌ ነው፡፡ እንዴት ቢሉ ግብጽ የሲኦል ፈርኦን የዲያብሎስ እስራኤል ዘሥጋ ለእስራኤል ዘነፍስ የተሠዋው በግ የክርስቶስ በጉን ተሰብስበው የበሉበት ቤት የቀራንዮ ምሳሌ ነው፡፡ ይህንን ምሳሌ በዝርዝር ስንመለከተው፡-

ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት
እስራኤል ዘሥጋ የተባሉት እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ለመውጣት የተመገቡት በግ ቀንዱ ያልከረከረ' ጥፍሩ ያልዘረዘረ' ያላረጀ በመካከለኛ እድሜ ላይ ያለ ነውር የሌለበት ንጹህ በግ ነበር ይህም ምሣሌነቱ እስራኤል ዘነፍስ ያዳናቸው በፋሲካው በግ የተመሰለው ጌታ ነውር ነቀፋ ኃጢአት በደል የለበትምና እንደዚህ አለ፡፡
አጥንቱን አትስበሩ ሥጋውን ብሉ
የፋሲካው በግ አጥንቱ እንዲሰበር አልተፈቀደም ነበር ለጊዜው በአጥንት የተመሰሉት እስራኤላውያን መከራ አያገኛቸውም ለማለት ሲሆን ለፍፃሜው ግን ክፉ ንግግር አጥንትን የመስበር ያህል ይሰማልና የእግዚአብሔር በግ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የክህደት ቃል አትናገሩ ሲል አንድም የፋሲካው በግ አጥንቱ እንዳልተሰበረ ሁሉ ጌታ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ በሚሰቀልበት ጊዜ አጥንቱ አለመሰበሩ ምሳሌ ነው፡፡ (ዮሐ 19÷34)
በእሳት የተጠበሰውን ብሉ
የበጉን ጥሬ ሥጋና በውሃ ተቀቅሎ የፈረሰውን ሥጋ አትብሉ ተብለዋል፡፡ ምክንያቱም ጥሬውን ቢበሉ በሥጋ ውስጥ ደም ይኖራል በደም ውስጥ ደግሞ ነፍስ ታድራለችና ጥሬውን አትብሉ አለ፡፡ የተቀቀለውን አትብሉ መባሉ የተቀቀለ ሥጋ ይፈርሳልና ከአጥንቱ ይለያያልና እንደዚሁ ጌታ በመቃብር ሳለ ፈራርሶ ሙስና መቃብር አገኘው አትበሉ ሲል ነው፡፡ በእሳት የተጠበሰውን ብቻ ብሉ መባሉ በበግ የተመሰለው የጌታ ሥጋ እና ደም መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው መሆኑን አምናችሁ ተቀበሉ ለማለት
ከመራራ ቅጠል ጋር ብሉት
ከመራራ ቅጠል ጋር ብሉት መባሉ ለጊዜው የበሉት እንዲዋሐዳቸው በኋላ ደግሞ የፋሲካን በዓል ባከበሩ ቁጥር ያንን የግብጽን መራራ መከራ /ባርነት/ እንዲያስቡ እግዚአብሔርም ከዚያ እንዳዳናቸው እንዲያስተውሉ ነው፡፡ ለፍጻሜው ግን ጌታ ለእኛ ሲል መራራ ሞትን እንደተቀበለ ሥጋ ወደሙ ስንቀበል እንድናስታውስ ነው፡፡ (ዮሐ 19÷28) አንድም ሥጋ ወደሙ ከመቀበላቸው በፊት አፋችሁ ምሬት እስኪሰማው ድረስ (18 ሰዓት ያህል) ጾማችሁ ተቀበሉ ለማለት፡፡
ወገባችሁን ታጥቃችሁ ጫማ አድርጋችሁ በትር ይዛችሁ ተመገቡ
ለጊዜው እስራኤል መንገደኞች ነበሩና እንዲዘጋጁ ለፍጻሜው ግን የጌታን ሥጋ እና ደም ስተቀበሉ ወገባችሁን ታጥቃችሁ አለ ንጽሕናን ቅድስናን ገንዘብ አድርጋችሁ ሲል ነው፡፡ (ሉቃ 12÷35) ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁ የበራ ይሁን እንደተባለ ጫማችሁን ታጥቃችሁ ሲል ወንጌልን ተምራችሁ በትር ይዛችሁ መባሉ የጌታን መስቀል ጋሻ መከታ አድርጋችሁ ሥጋዬን ደሜን ተቀበሉ ሲል ነው
ፈጥናችሁ ተመገቡት /ትበሉታላችሁ/
ከዚህ ተአምራት በኋላ ነፃ ስለምትወጡ ወደ ከነዓን ጉዞ ስለምትጀምሩ ጊዜ ሳታባክኑ ፈጥናችሁ ብሉ ተባሉ፡፡ ለፍፃሜው ግን ምዕመናን ሞት እንዳለባቸው አውቀው ዛሬ ነገ ሳይሉ ሥጋ ወደሙን ተቀብለው ተዘጋጅተው መጠበቅ እንዳለባቸው ሲያጠይቅ
ከቤት አትውጡ ደሙም ምልክት ይሁናችሁ
እስራኤላውያን በጉን ሠውተው ደሙን በመቃኑና በጉብኑ ላይ ረጭተው ነበርና መልአከ ሞትም ያንን አይቶ ያልፋቸው ነበር፡፡ እንደዚሁ የደሙ ምልክት እስራኤልን ከሞት መቅሰፍት እንዳዳናቸው እኛም እስራኤል ዘነፍስ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለማግኘት የሞት ሞትን ላለመሞት የጌታን ሥጋና ደም መቀበል ግድ ይላልና ከቤት አትውጡ መባሉ ከሃይማኖት አትናወጹ በአንዲቱ ሃይማኖት ጸንታችሁ ጠብቁ ሲል ነው፡፡(ዕብ 3÷14)
U  ሰባት ሁናችሁ ብሉ መባሉ ሰባት በዕብራውያን ፍጹም ቁጥር ነው የጌታን ሥጋና ደም ስትቀበሉ በንስሐ ፍጹማን ሁኑ ሲል
U   አሥር ሆናችሁ ብሉ መባሉ አሥር በዕብራውያን ሙሉ ቁጥር ነው አንድም የአስርቱ ትዕዛዛት ምሳሌ ነው፡፡ በእምነት በምግባር ምሉዓን ሆናችሁ አሰርቱ ትዕዛዛትን ጠብቃችሁ ሥጋ ወደሙን ተቀበሉ ሲል ነው፡፡
U   አሥራ ሁለት ሆናችሁ መባሉ የአሥራ ሁለቱን የሐዋርያት ስብከት አምናችሁ ሲል
U  በልታችሁ የተረፋችሁን በእሳት አቃጥሉት መባሉ የተቻላችሁን መርምራችሁ የተቀረውን አንተ ታውቃለህ በሉ ሲል ነው፡፡
U  ለአንዱ የተሠዋውን ለሌላ ቤት አትውሰዱ መባሉ አንዱ ቤተ ክርስቲያን የተሠዋውን ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን አትውሰዱ ሲል ነው
U  የፋሲካው በግ 430 ዘመን በባርነት የነበሩትን እስራኤልን ነፃ ለማውጣት ምክንያት እንዲሆን የጌታ ሥጋ እና ደም 5500 ዘመን ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ምክንያት ነውና የፋሲካው በግ ለሐዲስ ኪዳን ለጌታችን ሥጋ ወደሙ ምሣሌ መባሉ ለዚህ ነው፡፡

በዘመነ ብሉይ የነበሩ መሥዋዕቶች
U  በዘመነ ብሉይ የነበሩ መሥዋዕቶች የጌታ ሥጋና ደም ምሣሌ ናቸው፡፡ በኦሪት ቅዱሳን አባቶች ያቀርቡት የነበረ መሥዋዕት ፍጹም ድኅነት አያሰጥም ነበር ነገር ግን ተስፋ ድኀነት ነበረው፡፡
ለምሳሌ፡-
U  አዳም ባቀረበው መሥዋዕት ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ተስፋ ተሰጥቶት ነበር (ገላ 4÷4)
U  ኖኅ ባቀረበው መሥዋዕት ምድርን ዳግመኛ በንፍር ውሃ እንደማያጠፋት እግዚአብሔር አምላክ በቀስተ ደመና ቃል ገብቶለታል፡፡ (ዘፍ 9÷8-18)
U  አበ ብዙኀን አብርሃም ባቀረበው መሥዋዕት በዘሩ አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ተስፋ ተሰጥቶታል (ዘፍ 12÷3)
U  መልከጼዴቅ ባቀረበው መሥዋዕት ክህነቱ ዘለዓለማዊ እንደሆነ ተነግታል (መዝ 131÷11)

ይቆየን ይቀጥላል

                                                                                                                             ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment