Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አስራ አንድ



                                

የረቡዕ ሥነ ፍጥረታት
“…..እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ፡፡ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሰለጥን ትንሹም ብርሃን በሌሊት ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ……..አራተኛ ቀን” (ዘፍ 1፥14-19)
በዚህ ዕለት በነቢብ ሦስት ፍጥረታትን ተፈጥረዋል፡፡እነሱም ፀሐይ፣ጨረቃና ከዋክብት ናቸው፡፡
እነዚህን መፍጠሩ እጠቀምባቸዋለሁ ብሎ አይደለም፡፡ ለሰዎችና በዚህ ዓለም ለሚገኙ ፍጡሮች እንዲያበሩላቸው ብሎ እንጂ አንድም ቀን እና ሌሊትን ዘመናትን ዓመታትን ለመለያየት ተፈጥረዋል፡፡
ምሳሌነታቸው፡- የዕለተ ረቡዕ ደግሞ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምሣሌዎች ናቸው፡፡ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲን ነገር እንደምንድን ነው ቢሉ ቤተ ክርስቲያን የተባሉ ምዕመናን ናቸው፡፡ ጻድቃን በፀሐይ ኀጥአን በጨረቃ ይመሰላሉ፡፡ ፀሐይ ሁልጊዜ ምሉዕ ሆኖ እንዲኖር ጻድቃንም በምድር በሃይማኖት ምሉዐን ናቸውና፡፡ ጨረቃ አንድ ጊዜ ስትሞላ አንድ ጊዜ ስትጎድል እንደምትኖር ኀጥአንም በምግባር በሃይማኖት ጎዶሎዎች ናቸውና፡፡ አንድም፡- ኀጥአን በፀሐይ፣ጻድቃን በጨረቃ ይመሰላሉ፡፡ ፀሐይ ብርሃኑን ሳይለውጥ በምልዐት እንደሚኖር ኀጥአንም በኀጢአት በክህደት ምሉዐን ናቸው፡፡ ጨረቃ አንድ ጊዜ ስትሞላ አንድ ጊዜ ስትጎድል እንደምትኖር ጻድቃን ፍጹማን ከሆኑ በኋላ ቢሰናከሉ በንስሐ ይታደሳሉና ‹‹ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ሰባት ጊዜ ይነሳል››(ምሳ 2417)
የሐሙስ ሥነ ፍጥረታት
‹‹እግዚአብሔር አለ ፡- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸው ተንቀሳቃሾች ታስገኝ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ…..አምስተኛ ቀን›› (ዘፍ 1፥20-23)
በእግር የሚሽከረከሩ
በክንፋቸው የሚብሩ
በደረታቸው የሚሳቡ ናቸው፡፡
እነዚህ ፍጥረታት የወጡት ከውኃ ነው (ዘፍ 1፥20-23)
ከውሃ ተፈጥረው በረው በረው ወደ የብስ የወጡ አሉ፡፡
ከዚያው ከባሕር የቀሩ አሉ፡፡
በየብስ ውለው ለአዳር ተመልሰው የሚመጡ አሉ፡፡

ምሳሌነታቸው የጥምቀት ነው
አንድ ጊዜ የብስ አንድ ጊዜ ወደ ባሕር የሚሉት አንድ ጊዜ ወደ ክርስትና አንድ ጊዜ ወደ ክሕደት የሚሄዱት ምሳሌ
አንድም፡- ባሕር በዕለተ ዓርብ ከጌታ ቀኝ ጎን የወጣው የማየ ገቦ ምሳሌ
በረው በረው ከሕገ ሥጋ ሕገ ነፍስ፣ ከሕገ እንስሳ ሕገ መላእክት ይበልጣል በማለት ከዘመድ ባዳ፣ከሀገር ምድረ በዳ ይሻላል ብለው በዋሻ በፍርክታ ተጠግተው ጤዛ ለብሰው ደንጊያ ተንተርሰው የሚኖሩ የመናንያን ምሳሌ
ከዚው የቀሩ ሚስት ባል አግብተው ወልደው፣ አርሰው፣ ነግደው የሚኖሩ መናንያን ምሳሌ
አንድ ጊዜ ወደ ባህር አንድ ጊዜ ወደ የብስ የሚመላለሱት የገዳም ፈተና ሲያስቸግረው ወደ ተድላ ዓለም፣የተድላ ዓለም ሲሰለቻቸው ወደ ገዳም የሚሄዱ የመናንያን ምሳሌ

በሦስት ወገን አድርጎ መፍጠሩ
ጥምቀት ለሦስት ትውልድ ማለትም ለትውልደ ሴም፣ካም እና ያፌት ለመሰጠቷ ምሳሌ ከዚህ የወጣ ትውልድ የለምና
                                     
የዓርብ ሥነ ፍጥረታት

“እግዚአብሔር አለ ምድር ሕያዋን ፍጥረታት እንደወገኑ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን በምድርም አራዊትን እንደ ወገኑ ታውጣ እንዲሁም ሆነ……..” (ዘፍ 1፥24-25)
በዚህ ዕለት ሁለት ፍጥረታት በነቢብ አንድ ፍጥረት በገቢር ተፈጥሯል፡፡
በዚህ ዕለት እንደ ሐሙስ ያሉ በእግር የሚሽከረከሩ፣ በልብ የሚሳቡ፣ በክንፍ የሚበሩ ሦስት ፍጥረታት ተገኝተዋል፡፡ የዓርብ ፍጥረታት የወጡት ከምድር ነው፡፡ የሐሙስና የዐርብ መሆናቸው በምን ይታወቃል ቢባል በአኗኗራቸው ነው፡፡ የሐሙስ ፍጥረታት በየብስ የዓርብ ፍጥረታት በባሕር ማደር አይሆንላቸውም፡፡
ምሳሌነታቸው፡- የዓርብ ፍጥረታት ምሣሌነቸው በምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን ነው፡፡ በየብስ የሚኖሩ ሦስቱን ፍጥረታትን መፍጠር የሦስት ጊዜ የመለከት መነፋት ምሳሌ ነው፡፡

“እግዚአብሔርም አለ ሰውን በአርያችንና በምሳሌአችን እንፍጠር” (ዘፍ 1፥26)

አጋእዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ በእለተ ዐርብ ከአራቱን ባሕርያተ ሥጋ እና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስን /ለባዊነት፣ ነባቢነት፣ ሕያዊት/ አዳምን የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ አድርገው በማዕከለ ምድር በቀራንዮ ፈጠሩት፡፡ አዳም ማለት በጣም ሳይረዝም እንደ ድንክም ሳያጥር ይህ ቀረው የማይባል መልከ መልካም ማለት ነው፡፡ አዳም ማለት ዐደመ/አማረ፣ተዋበ/ ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ አንድም፡- አዳም ማለት ከመሬት የተፈጠረ፣ ሰው የሆነ ማለት ነው፡፡ ሰው የሚለው ቃል በግእዙ ሰብእ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ሰባት ማለት ነው፡፡ ሰባት ባሕርይ ያለው ማለት ነው፡፡ 7ቱ በሕርያት የሚባሉትም 4ቱ በሕርያተ ሥጋ እና 3ቱ ባሕርያተ ነፍስ ናቸው፡፡
አዳም ከፍጥረታት መጨረሻ ለምን ተፈጠረ?
መጨረሻ የተፈጠረበት ምክንያት እግዚአብሔር አምላካችን በጎ አምላክ ስለሆነ ነው፡፡በጎ አባት ለልጁ አብሮት ሳለ ከብት ያረባለታል፣ጥማድ ያጠምድለታል፣ የኑሮ ጓደኛ ያመጣለታል፡፡ ጌታም እንደዚሁ አስቀድሞ የሚበላውን፣ የሚጠጣውን፣ የሚገዛውንና የሚነዳውን ፈጥሮ በመጨረሻ በሁሉ ላይ ሲያሰለጥነው አዳምን ፈጠረው፡፡
ሌሎቹን ፍጥረታት አስጎንብሶ ሲፈጥራቸው አዳምን አቅንቶ ፈጠረው?
እርሱ ገዢ እናንተ ተገዢ ናችሁ ሲል እንዲሁም እናንተ ፈርሳችሁ በስብሳችሁ ትቀራላችሁ እርሱ ግን ትንሳኤ ሙታን አለው ሲል አቅንቶ ፈጥሮታል፡፡
አዳምን የሚቆም የሚተኛ አድርጎ መፍጠሩ፡-
መቆሙ ሰማያዊ መቀመጡ ምድራዊ ነህ ሲለው ነው፡፡ የሚተኛ የሚነሣ አድርጎ መፍጠሩ ደግሞ በመተኛቱ ሞቱን በመነሣቱ ትንሳኤውን ሲነግረው ነው፡፡
የሔዋን አፈጣጠር
አዳም በተፈጠረ በ8ኛው ቀን ሔዋንን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን በፈጠረበት ሰዓት ‹‹አዳም ብቻውን ይኖር ዘንድ አይገባውም እረዳት እንፍጠርለት ›› በማለት በአዳም ላይ እንቅልፍ አመጣበትና ፈጽሞ ሳይተኛ ፈጽሞ ሳይነቃ ከጎኑ አጥንት አንስቶ ያቺን ሥጋ አልብሶ የአሥራ አምስት ዓመት ቆንጆ አድርጎ ፈጠራት፡፡ (ዘፍ 2፥18) ስሟንም ሔዋን አላት ሔን ማለት ‹ሐይወ› ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም የሕያዋን ሁሉ እናት ማለት ነው፡፡
ፈጽሞ ሳይተኛ ፈጽሞ ሳይነቃ ሔዋንን መፍጠሩ፡-
ፈጽሞ ተኝቶ ቢሆን ኖሮ ምትሐት መስሎት ከየት መጣች ብሎ በፈራት ነበር፡፡ ፈጽሞ ነቅቶ ቢሆን ኖሮ ከአካሉ አጥንት ሲነሣበት ያመው ነበርና በጠላት ነበር፡፡
ከፍ አድርጎ ከግንባር ዝቅ አድርጎ ከእግር ያልፈጠራት ከጎድን ለምን ፈጠራት?፡-
ግንባርና እግር በልብስ አይሸፈንም ጎድን ግን በልብስ ይሸፈናልና ተሰውራ (ተሸፍና) መኖር ይገባታል ሲል ነው፡፡ በሌላ በኩልም ግንባር የባለቤት እግር የቤተሰብ ምሳሌ ነው፡፡ እርሷም ከባለቤት በታች ከቤተሰብ በላይ ሁና ትኑር ሲል ነው፡፡(1ኛ ቆሮ 12፥19-22)
እንዲህ አድርጎ አዳምና ሔዋንን እስከ 40 ቀን ድረስ በተፈጠሩበት በማዕከለ ምድር በቀራንዮ አሰነበታቸው፡፡ መድሐኒታችን ክርስቶስ የሚሰቀልበትን ቦታ ነውና፡፡ በ40ኛው ቀን አዳምን ብርሃን አልብሰው ብርሃን አጎናጽፈው የብርሃን ዘውድ አቀናጅተውት በብርሃን ሰረግላ አስቀምጠውት ወደገነት አስገቡት፡፡ ሔዋንንም በ80 ቀኗ እንደ አዳም ባለ ክብር ወደ ገነት አስገቧት፡፡(ኩፋ 4፥12-15)
የአዳም እግዚአብሔርን መምሰልና አርአያና አምሳል
ቀድመን እንዳየነው እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ፈጥሮ ባገባደደበት በዕለተ ዓርብ ከፍጥረታት ሁሉ ልዩ ንዑድ ክቡር የሆነውን አዳምን ፈጠረ፡፡ በኦሪት ዘልደት መጽሐፍ ተጽፎ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ‹‹ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር›› ብሎ በመልኩና በምሳሌ ፈጠረው፡፡ (ዘፍ. 1÷26) ሰው ገና ሲፈጠር በጸጋ አምላክ እንዲሆን ተደርጎ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የመፈጠሩ ጉዳይ ኦርቶዶክሳዊያን አባቶቻችን በብዙ ትርጉም ይተረጉሙታል፡፡ ይህም እግአዚአብሔርን የመምሰላችንን ጉዳይ በስፋትና ጥልቀት የሚተነተን ነው፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቄሳርያ ‹‹አንድ ሰው ራሱን ካወቀ እግዚአብሔርን ያውቃል እግዚአብሔርን ካወቀ ደግሞ እግዚአብሔርን ይመስላል››ሲል ያስቀምጣል፡፡ የእስክንድርያው አባት ቅዱስ ቀሌምንጦስ ‹‹ወንድምህን አስተውለህ ስትመለከተው እግዚአብሔርን ትመለከተዋለህ›› ይላል፡፡ ዘወትር ቤተክርስቲያን የምትገለገልበትና መጽሐፈ ሰዓታትን ያበረከተው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዩርጊስም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለአዳም በዘዚአሁ አርአያ ወአምሳል››24 ይላል ይህም እግዚአብሔር ሰውን በአርአያና አምሳሉ መፍጠሩን በጉልህ የሚያመለክት ንግግር ነው፡፡
አርአያና አምሳል
የሰው ነፍስ ስንል በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖረውና የማይሞተው ክፍል ነው፡፡25 እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከምድር አፈር ከፈጠረው በኃላ የማይሞት ነፍስን እስትንፋስ እፍ ብሎበት ሕያው ፍጥረት አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ (ትምህርተ መለኮት ዓስራት ገብረ ማርያም) መናፍቃን ግን ረቂቅ ነፍስ ከግዙፍን እናትና አባት አትከፈልም ብለው ይላሉ፡፡ መዝገበ ነፍስ አለ መላእክትን እንዳሰፈራቸው ነፍሳትንም ፈጥሮ በአንድ ላይ አስፍሯል፡፡ ከእኒያ ነፍሳት አንድ አንድ እየመጣ ሥጋን እየፈጠረ በሥጋ ነፍስ ያዋሕደዋል ብለው ተነስተዋል፡፡ ነፍስና ሥጋ በአንድ ላይ ተፈጠሩ እንጂ ተለያይተው አልተፈጠሩም፡፡ ስለዚህም ከላይ የጠቀስነው አባባል ለመናፍቃኑ ትምህርት በር ከፋች ነውና ከምድር አፈር ካበጀው በኋላ የማይሞት ነፍስን ፈጠረለት አንልም፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረችው ነፍሳችን ናት ብሎ ሲያስተምር ‹‹አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ አለህ፤ ነፍስ የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት›› ይላል፡፡ ሰው በነፍስ ተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም ሓላፊነት የሚሰማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ በእነዚህ ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህን ነጥብ ይጋሩታል እግዚአብሔር ሰውን በአርአያው ፈጠረው ማለት በነፍሱ ላይ ሦስቱን ባሕርያት አኑሮ ፈጠረው ማለት እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ እነዚህ ሦስት የነፍስ ባሕርያት ለባዊነት ነባቢነት(ተናጋሪነቱ) እንዲሁም ሕያውነቱ ናቸው በዚህ ባሕርያቱም የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት የሚለይበት ከእግዚአብሔር ጋር ደግሞ የሚመሳሰልበት ነው፡፡ ሌላው አርአያ ስንል አዳም ነጻ ፈቃድ ያለው መሆኑ እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡
ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ግን ነፍሳችንም ሥጋችንም በእግዚአብሔር አርዓያ እንደተፈጠሩ ግልጽ በሆነ መልኩ ሲያስረዳ በአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም (በፈሰሰው ደሙ) ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርአያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡ይለናል፡፡ሰው ሰማያዊት አካል ስላለችው ረቂቁን ዓለም የመረዳት ችሎታ ሲኖረው ምድራዊውም አካል ስላለው ምድራዊውም እውቀት አለው፡፡ ሰውን ከሰማያውያን መላእክትና ከምድራውያን መላእክት ጋር ስናስተያየው ለሁለቱም ዓለማት እንግዳ እንዳልሆነ በሁለቱም ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮአዊ ባሕርይ እንዳለው፣ የሰማያውያንንም የምድራውያንንም እውቀት ገንዘቡ ያደረገ ፍጥረት መሆኑን ስናስተውል በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መፈጠሩን እንገነዘባለን ፡፡
ቅዱስ ባስልዩስ አርዓያ ለሁሉ የተሰጠ ነው ምሳሌ (አምሳል) ስንል ግን በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፣ ትሑትና የዋህ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡
በአርአያና በአምሳሉ የተፈጠረው ሰው ከሕጉ ፈቀቅ አለ
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ሳለ ከክብሩ በኃጢያት ምክንያት ተዋረደ፡፡ በአዳም ምክንያት ሞት በሰው ሁሉ ላይ ታወጀ፡፡ ቅድስና እንደመርገም ሆነ ቅዱሳን ከሲኦል እስራት የሚፈታቸውን በመፈገለግ ተጨነቁ በዚህን ጊዜ አምላክ አንደኛ ልጁን ወደ ምድር ላከ(ዮሐ. 3፥16) አምላኩን መምሰል ያቃተው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ ከሕግጋቱ እየፈጸመ በሕይወቱ የጎለበተ ይሆን ዘንድ ሕግን እየፈጸመ አሰለጠነው፡፡ የሰለጠነበትና የገዛውን ዲያቢሎስን በመስቀሉ ድል አደረገው፡፡ እግዚአብሔርን ይመስል ዘንድ ዳግመኛ ሕጉን አጸናለት፡፡ ትዕዛዙንም የሚፈጽሙት ሁሉ ወደ እርሱ መምሰል ይቀርቡ ዘንድ፡፡ቅዱስሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በአንድነት ‹‹ሰው በጸጋ አምላክ ይሆን ዘንድ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ›› ብለው ያስተምራሉ፡፡ቅዱስ ያሬድም በዜማ ድርሰቱ ‹‹ ቃል ሥጋ ኮነ … ደመረ መለኮቶ ምስለ ሥጋ ዚአነ›› የመለኮትና የሥጋን ተዋሕዶ በተመለከተ ይሀም ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለው የሰውና የእግዚአብሔር ተዋሕዶ ምሥጢረ ሥጋዌን እግዚአብሔር ጋር መመሳሰል ጋር በእጅጉ ያገናኘዋል፡፡
በትንሣኤውም ዳግመኛ መነሳትን አደለው ከሙታን ጋር እነዳይቆጠር ወልደ እግዚአብሔር ሞትን ድል አድርጎ ወደ ቀደመ መምሰሉ መለሰው፡፡ ቀድሞም ሲፈጠር የሚተኛና የሚነሳፍጥረት አድርጎ መፍጠሩ አዳም ሕያው ፍጥረት መሆኑን አመልካች ነው(መጽሐፈ አክስማሮስ)26
እኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡ በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልምይለናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ €oeየማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም፡፡ በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ለዚህ መልስ ሲሰጥ እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና ይላል (ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)
የአዳም ውድቀትና መዳን
አስቀድመን በአዳም በደል ምክንያት አዳምና የአዳም ልጆች ምን አጡ የሚለውን እንመልከት
1. ሞት ሟችነት አገኛቸው
2. የባሕርይ ተጎሳቆል
3. ስደተኛ ሆኑ
4. ሰላም አጡ ተጨነቁ
5. መንፈሳዊ እድገታቸው ተቋረጠ
6. ክብርና ጸጋውን አጡ

መዳን
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ መዳን ምን ማለት ነው የሚለውን ነጥብ መገንዘብ ይገባናል፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መዳን ስንል የኃጢአት ደሞዝ ከሆነው ከሞትና ከቅጣት መዳን ብቻ ወይም ከኩነኔ መዳንና ማምለጠ ብቻ አይደለም፡፡ መዳን ኃጢአት ሥርየትን ማግኘትና ከቅጣት መዳን ብቻ ሳይሆን ከዚያ እጅግ ያለፈ ጥልቅና ሁለንተናዊ ነው፡፡ ይህም መሠረታዊና ዋና ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ እንዳለ ሆኖ በዚያ ላይ የተሰጡን ብዙ ጸጋዎችና ሀብታትም አሉ፡፡ ጌታችን ያደረገልን የመዳን ቸርነትና ሥጦታ ስለእኛ ተገብቶ የኃጢአታችንን ዕዳ መክፈልና እኛን ነጻ ማውጣት ብቻ አይደለም ከዚያ በላይ የሆነ እጅግ በጣም ብዙና ድንቅ ነገር ነው እንጂ፡፡
በአጠቃላይ መዳን ስንል አራት መሠረታዊ ነጥቦችን ያካተተ ነው
1. ኃጢአት ካመጣው ፍዳ ሁሉ መዳን
2. ፈጣሪውን እንዲውቅ መሆን
3. ሐዲስ ተፈጥሮ
4. በቅድስና(እግዚአብሔርን በመመሰል) ማደግ ናቸው፡፡

በፕሮቴስታንት ትምህርት መሠረት ኃጢአታችን በሙሉ በጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ወደ እርሱ የተላለፈበትን ዕዳነቱን የከፈለበት ከሆነ በኃጢአታችን አንጠየቅም የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ምትካችን ከሁለት ሺህ ዓመታት አስቀድሞ ከፍሎታልና(እንደነርሱ አባባል ኃጢአታችን አያስጠይቀንም) የሚል ነው፡፡
ይህ ከሆነ ከዚህ አስተምሮ ወደ የሚከተለው ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል ይኸውም የሰው ልጅ በሙሉ(አመነም ኃጢአት ሠራም አልሠራም) ይድናል የሚለው አስተሳሰብ ነው(universal salvation)ነው፡፡ አለበዚያ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለማዳን ለመረጣቸውብቻ እንጂ ለመላው የሰው ልጅ አይደለም የሚለው አስተሳሰብ (john calvinʼs limited atonements) ሆኖም ሁለቱም አስተሳሰቦች ስህተቶች ናቸው፡፡
የካሊቪን ምትክ ቲዎሪ ይህም የሚድኑ አስቀድመው ለመዳን የተወሰኑ ወይም የተመረጡ ጥቂቶች ናቸው የሚለው ነው፡፡ ይህ ከሉተርን ትምህርት ጋር የሚቃረን ነው ካመነ ይድናል የሚለው ትምህርት ሁሉም ሰው እንዴት ይድናል? የሚለው የጌታ ትምህርት የሚድኑ ጥቂቶች ናቸው ከሚለው ጋር የሚጋጭ ሆነ …
አንዳንዶች እግዚአብሔር አዳም ቀድሞ እንደሚበድል እያወቀ ፈጥሮታል ወይም አስቀድሞ ወስኖበታል የሚል የተሳሳተ ትምህርት ያስተምራሉ፡፡ይህ አስቀድሞ ማወቅና አስቀድሞ መወሰን ልዩነትን ካለመገንዘብ የመነጨ ነው፡፡ አስቀድሞ ያውቃል ስንል እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት እስከ ዕለተ ፍትሕ ሊሆን ያለውን ነገር ምንም ሳይሰወርበት ያውቃል፡፡ እውቀቱም ፍጹም ባሕርያዊ ስለሆነ ወሰን የለበትም፡፡ ይህ ማለት አዳም እንደሚበድልና ሕጉን ቸል እንደሚል ያውቃል እንደሚያድነውም ያውቃል አንድ ሰው ከመወለዱ በፊት ቅዱስ ይሁን ኃጥእ ይህንንም ያውቃል ነገር ግን ቀድሞ አይወስንም፡፡ መወሰንና ማወቅ ፍጹም የተለያዩ ናቸው
አዳም ነጻ ፍቃዱን ተጠቃመ በልቡናው አስቦ ኃጢአትም መረጠ እኛም ዛሬ በፍቃዳችን ኃጢአት እንሰራለን ወይም ጽድቅ እናደርጋለን በሰራነው ጽድቅ ወይም በደል ተጠያቂዎች እኛው ራሳችንን እንደሆንን ሁሉ አዳምም ለበደሉ ተጠቃቂው ራሱ ነው፡፡

የሰው ነጻ ፍቃድ ስንል ምን ማለት ነው እንዴት ይገለጻል
አውግስጢኖስ እግዚአብሔር በቅድሳት መጽሕፍት በሰው ዘንድ ነጻ ፍቃድ እንዳለን ነገረን ካለ በኋላ ሰው የእግዚአብሔር ሕግጋትን በፍቃድ ምርጫው በመፈጸም ተስፋ የተደረጉለትን ሽልማት ያገኛል፡፡ በኃጢአቱም ፍርድ ያገኛል ይህን ፍርድ በማግኘቱ ለምን ብሎ አይጠይቅም ምክንያቱም ነጻ ፍቃዱን ተጠቅሞ ፈጽሞታልና፡፡›› ይላል
እንደ አውግስጢኖስ የሰው በልጅ ነጻ ፍቃድ ‹‹ሕግጋትን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም ያለ ነጻነት ነው ›› ይላል
የሰው ልጅ ነጻ ፍቃድ ስንል ከተጠያቂነት ነጻ የሆነ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ይህ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ነጻነቱ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው፡፡ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ይህንን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል‹‹ ሰው ክፉም ይሁን በጎም ይሥራ ለሚሠራው ሥራ ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡በዚህም መሠረት መልካም ቢሰራ ይሸለማል ክፉ ቢሰራ ይቀጣል፡፡ ለአዳምና ለሔዋን ነጻነት አላቸው ስንል ሕገ እግዚአብሔርን ሊጥሱ ወይም ሊፈጽሙ ይቻላቸዋል ማለታችን ነው፡፡ እነርሱ ግን ሕግ ተላልፈው ተገኝተዋልና እግዚአብሔር ቀጣቸው፡፡ይህም ለሁሉ የሰው ልጅ የተሰጠ ነው፡፡ (ሉቃ 13፥3-4)››
ለመዳንም የሰው ነጻ ፍቃድ ወሳኝ ነው በወንጌል እንደምናነበው ዓይነ ስውሩ ሰውየ ዓይኑን ያበራለት ዘንድ ወደጌታ መጣ የዓይን ቅርጽ ከሰራለት በኋላ ዓይንህ እንዲበራ በሰሊሆን ጠበል ታጠብ አለው፡፡ ጌታ ዓይንን ፈጠረለት ነገር ግን ለመዳን ፍቃደኛ መሆን ስላለበት በሰሊሆም ጠበል እንዲታጠብ አዘዘው፡፡ (ዮሐ 9፥1-) የመጻጉም ታሪክ ለዚህ አመልካች ነው ጌታ ከማዳኑ በፊት ልትድን ትወዳለህ ብሎ ጠይቆት ነበርና፡፡
የሚድኑ እነማን ናቸው
በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት እግዚአብሔር በመዳን ውጭ ያደረገውን ይህን ጸጋ የነፈገው ማንም ሰው የለም፡፡ ሁሉም የተፈጠረው ለመዳን ነው (2ኛ ጢሞ 2፥3-4 ዮሐ 3፥16)
መዳን ለተወሰኑ?
መዳን በእግዚአብሔር ቸርነት ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ጸጋ እንጂ በቅድመ ምርጫና በቅድመ ውሳኔ የሚያምኑ ሉተራዊያንና ካልቪኒስቶች እንደሚሉት አስቀድመው ለተወሰኑ ለጥቂቶች የተሰጠ አይደለም፡፡ በተግባር ስታይ ግን የሚድኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን በራሱ ድክመትና ስንፍና እንጂ አስቀድሞ ለመዳን የማይችል ሆኖ የተፈጠረ ስለሆነ አይደለም፡፡
የሚድኑ የተመረጡ ጥቂቶች ብቻ ከሆኑ ክርስቶስ መከራን መቀበል ለሁሉም ነው አያሰኝም(ዮሐ. 3፥16) ይህም የነገረ ድኅነት ተፋልሶን የሚፈጥር ነው፡፡
ለመዳን ምን ማድረግ ይገባል
1. እምነት ማመን(ዮሐ 5፥24 ዮሐ 3፥15 ዮሐ 4፥5 ዮሐ 5፥10)
2. ለድኅነት አስፈላጊ የሆኑ ምሥጢራትን መፈጸም
*        ጥምቀት
*        ሜሮን
*        ቁርባን
3. መልካም ሥራ

ቅዳሜ
በዚህ ዕለት ምንም ፍጥረት አልተፈጠረም፡፡ ሥራውን ያጠናቀቀበቀት ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ (ዘፍ 2፥1) ‹‹ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሂሉ ተፈፀሙ፡፡እግዚአብሔር የሰራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ከሰራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ፡፡ እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሲያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሷ ዐርፏልና፡፡››
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር



No comments:

Post a Comment