Monday, 24 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሃያ ስምንት (የመጨረሻ ክፍል)





የሰው ልጆች ትንሣኤ
የሰው ልጅ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረው ለሞት አልነበረም፡፡ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ኃጢአት በደልን ሰራ፡፡ ቀዳማዊ አዳምና እናታችን ሔዋን የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በማፍረሳቸው የሞት ባሪያ ተገዢ ሆኑ፡፡ (ዘፍ 2÷17 ዘፍ3÷18-27 ሮሜ 5÷-20-26 ሮሜ 6÷23) ሞት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል፡-
የሥጋና የነፍስ መለያየት/እንቅልፍ/
ከእግዚአብሔር መለየት /የሞት ሞት/
የሥጋ እና የነፍስ መለያየት /እንቅልፍ/
ይህ የሞት ዓይነት ለማንኛውም ሰው የማይቀር ነው፡፡ ይህ ሞት በመጽሐፍ ቅዱ እንቅልፍ በማለት ነቢያት ሆኑ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠርተውታል፡፡ ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን ይህንን የሞት ዓይነት ዕረፍት ብላ የምትጠራው (ዳን 12÷2 ሐዋ 7÷-60' ማቴ 9÷24 ዮሐ 11÷11-13) ይህን ሞት የሞቱ ሰዎች በፍጻሜ ዘመን በክብር ወይም በኃሳር ይነሣሉ፡፡
ትንሣኤ ዘለክብር፡- የሚነሡት ጻድቃን የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያትን ሲሆን ሲነሡ ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው እንደ ፀሐይ እያበሩ ወንዶች 30 ዓመት ጎልማሳ ሴቶች 15 ዓመት ቆንጆ ሆነው ለዘላለም በደስታ በሕይወት ለመኖር የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ (ራዕ 21÷1-5 2ተኛ መቃ 13÷8-14)
ትንሣኤ ዘለኃሣር -ይህን ትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች በዚህች ምድር ሳሉ እግዚአብሔርን ሲበድሉ በክህደት በምንፍቅና የሚኖሩ ትንሣኤ ልቡና ያላገኙ ሰዎች የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ ትንሣኤ ዘለኃሣር የሚነሡት ኃጥአን ከቁራ ሰባት እጅ ጠቁረው የግብር አባታቸውን ሰይጣንን መስለው ለዘላለም ትሉ በማያንቀላፋበት እሳቱ በማይጠፋበት በገሃነመ እሳት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ (1 መቃ 13÷9-11' ማቴ 13÷-42)
ከእግዚአብሔር መለየት/ የሞት ሞት/
ይህ የሞት ዓይነት በበደል በኃጥአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ከእርሱም አንድነት መውጣት ነው፡፡ የሰው ልጅ በደልን ኃጢአት ሰርቶ በንስሐ ካልተመለሰ መጨረሻው ከሰይጣንና ከሠራዊቱ ጋር ወደ ገሃነመ እሳት መጣል ነው፤ ይህም የሞት ሞት ይባላል፡፡
መልካሙንና ክፉዉን የሚያስታውቀውን ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና (ዘፍ 2÷16-17) እግዚአብሔር አዳምን ያዘዘው ይህን ትዕዛዝ ነበር፡፡ ነገር ግን አዳም ይህን ትዕዛዝ በተላለፈ ጊዜ ወዲያው ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ ፀጋውም ተገፈፈ ከገነት ወጣ የሥጋ ሞት አላጋጠመውም፡፡ ከዚህም የምንረዳው የሞት ሞት የተባለው በኃጥአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየትን ነው፡፡ በተጨማሪም (ሮሜ 5÷12 ኤፌ 5÷14-20) ተመልከቱ፡፡
ለሰው ልጆች ትንሣኤ የተነገሩ ትንቢቶች
እግዚአብሔር አምላክ ለሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ በነቢያት ትንቢት አናግሯል፡፡ ካናገራቸው ትንቢት መካከል የሰው ልጅ በፍርድ ቀን ከሞት እንደሚነሣ የተናገሩት ትንቶች አሉ፡፡ እነርሱም፡- .ዳን 12÷1-3 ‹‹በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነሣሉ እኩሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ እፍረትና ጉስቁልና›› መዝ 70/71÷20 ‹‹ብዙ መከራና ጭንቀት አሳይተኸኛልና ተመልሰህ ሕያውም አደረከኝ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኝ›› ኢሳ 26÷19 ‹‹ሙታን ሕያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሣሉ በምድርም የምትኖሩ ሆይ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም›› (ዮሐ 5÷28-29' 1 ቆሮ 15÷1' 19-26' 2 መቃ 13÷8-11)
ልጆች ትንሣኤ የተደረጉ ምሣሌዎች
ለሰው ልጆች ትንሣኤ ትንቢት እንደተነገረ ሁሉ ሙታን ለመነሣታቸው የተደረጉ ምሣሌዎች አሉ፡፡ ይኸውም በኋለኛው ትንሣኤ ለሚሆነው ነገር ግን በዚህ ምድር ሲኖሩ ሞተው በኋላ በቅዱሳን ጸሎት ከሞት የተነሡ ሰዎች ናቸው፡፡
ዮሐ 11÷44- የአልዓዛር መነሣት
ማቴ 9÷25- ጌታ ያስነሣው የመኮንኑ ልጅ
ሉቃ 7÷15- ጌታ ያስነሣው የመበለቲቱ ልጅ
ሐዋ 9÷36- .ጴጥሮስ ያስነሣት ጣቢታ
2 ነገ 4÷32- ኤልሳ ያስነሣው ብላቴና እንዲሁም(2 ነገ13-20) ተመልከቱ
1 ነገ 17÷21 ኤልያስ ያስነሣው ብላቴና

ዕለተ ምጽአት/ ዳግም ምጽአት/
ዕለተ ምጽአት /ዳግም ምጽአት/ የምትባለው ዕለት ዳግመኛም ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ሆኖ የተወጋ ጎኑን የተቸነከረ እጅና እግሩን እያሳየ ለጻድቃን ሊፈርድላችሁ ለኃጥአንና ለሰይጣን ሊፈርድባቸው ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣበት ዕለት ናት፡፡ (መዝ 49/50÷2-3' ራዕ 22÷12
የሰው ልጆች አነሣሥ
የሞትህ ተነሥ የሚል አዋጅ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ይታወጃል፡፡ ሦስት ረቂቃን ነጋሪት አሉ፡፡ ነጋሪት ሲባል ነጋሪት አይደለም የጌታ ትዕዛዝ ነው ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና (1 ተሰ 4÷16) እንደተባለ
Ø  የመጀመሪያው ረቂቅ ነጋሪት ሲመታ አውሬ የበላው ነፋስ የበተነው ያለቀው የደቀቀው ሁሉ ራስ በፈረሰበት ቦታ ላይ ይሰበሰባል፡፡ (ያዕቆብ ዘሥሩግ .91)
Ø  ሁለተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ ተዋሕደው ሳይንቀሳቀስ ትኩስ ሬሳ ይሆናል፡፡ አጥንትና ጅማቶች ከሥጋ ከደም ጋር ይያያዛሉ እስኪነሡ ያለመንቀሳቀስ ፍጹም በድን ይሆናሉ፡፡
Ø  ሦስተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ በቀዋሚ አካል የምትናገር አንደበት ከራስ ጸጉራቸው ሳይከፈሉ በአርባ ቀን በእናቱ ማህጸን ደም ሆኖ የወረደው ጽንስ ሳይቀር በጎም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ይነሣሉ፡፡(ገላ 6÷7) ‹‹አትሣቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም ሰው የዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፡፡ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና በመንፈስ የሚዘራ ግን በመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል›› (ማቴ 25÷35-46) ተብሎ እንደተጻፈ፡፡

ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ይመሰላሉ
ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ተመሰሉ ቢባል የበጎች ተፈጥሮ ከጻድቃን ሥራ ጋር የፍየል ተፈጥሮ /ግብር/ ከኃጥአን ጋራ ስለሚመሳሰል ነው ምክንያቱም፡-
. በጎች በደጋ እንጂ በቆላ አይኖሩም፡፡ ተስማሚያቸው ደጋ ነው ጻድቃን በመከራ ሥጋ እንጂ በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን ክደው በምግባር ብልሹነት አይገኙም፡፡ ፍየሎች በቆላ እንጂ በደጋ አይኖሩም፤ ኃጥአንም በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን በወርቅ በብር ይለውጣሉና፡፡
. በጎች እረኛቸው ባሰማራቸው ሥፍራ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ጻድቃንም እረኛቸው ክርስቶስ ባሰማራቸው በአንዲት ሃይማኖት ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ፍየሎች እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ጸንተው እንደማይኖሩ ኃጥአንም እንዲሁ በሃይማኖት ጸንተው መኖር አይቻላቸውምና፡፡
. በጎች ጥቂት ሳር ካገኙ ተፋቅረው አብረው ይበላሉ ጻድቃንም ያለቻቸውን ተካፍለው ይኖራሉና፡፡ ፍየሎች ግን ሣር ቅጠሉ ሞልቶ ለሁላቸው ሲበቃ ሳለ ይጣላሉ፡፡ ኃጥአንም ሀብት ንብረት ተትረፍርፎላቸው ለወገናቸው አያካፍሉም፡፡ ለገንዘብ ብለው እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ ዘለው የሌላውን ሀብት ንብረት ለማግኘት ሲሉ የማይገባ ሥራ ይሠራሉና፡፡
. የበጎች ላታቸው የተከደነ ሐፍረተ ሥጋቸው የተሸፈነ ነው፡፡ የጻድቃንም ኃጢአታቸው በሰው ዘንድ የተጋለጠ አይደለም፡፡ ኃጢአት ቢሰሩ ሌላ ሰው ሳይሰናከልባቸው ንስሐ ይገባሉ፡፡ የፍየሎች ላታቸው የተሰቀለ ሐፍረተ ሥጋቸው የተጋለጠ ነው፡፡ የኃጢአተኞችም ሥራ በሰው ዘንድ የተጋለጠ ለሚሰሩት እኩይ ሥራ የማያፍሩ በየአደባባዩ ኃጢአትን የሚፈጽሙ ናቸውና፡፡
. በጎች አቀርቅረው እንጂ አሻቅበው አያዩም ጻድቃንም ሁልጊዜ ዕለተ ሞታቸውን በማሰብ ወደ አፈር እንደሚመለሱ እያሰቡ በትህትና ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሀብት' ንብረት' ዕውቀት እያላቸው ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ ፍየሎች አሻቅበው ነው የሚያዩት አንገታቸውን ያንጠራራሉ ኃጥአንም ደካማ ሆነው ሳሉ ብርቱ ነን ይላሉ ባገኙበት ሀብት ዕውቀት ይመካሉ ትዕቢተኞች ናቸው፡፡ ትሕትና በእነርሱ ዘንድ የበታችነት ምልክት ነው፡፡
. ከበጎች ውስጥ አንዲቱ ተኩላ ቢነጥቃት ሁለተኛ ወደዚያ ቦታ ተመልሰው አይመጡም፡፡ ጻድቃንም እኩይ ሞት ከእነርሱ አንዱን ከወሰደ ነገም የእነርሱ ተራ እንደሆነ ተረድተው ከኃጢአት ሥራቸው በንስሐ ይመለሳሉ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ፡፡ ፍየሎች ግን ከመካከላቸው ነብር አንዲቱን ቢወስድ ለጊዜው ደንብረው ይሄዳሉ፡፡ ኋላ ግን ተመልሰው እዚያው ቦታ ይመጣሉ ኃጥአንም ከመካከላቸው አንዱ ሳያስቡት በሞት ቢወሰድ ለጊዜው ደንግጠው ከኃጥአት ሥራቸው ይታቀባሉ በኋላ ግን የሞተው ሰው ከህሊናቸው ሲጠፋና የዓለም ሁኔታ ሲማርካቸው ወደ ኃጢአት ግብራቸው ይመለሳሉና፡፡
የግራ እና የቀኝ ምሳሌ
ጻድቃን በቀኝ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው
ቀኝ ቅን ነው ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ቅን ናቸውና
ቀኝ ፈጣን ነው ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ፈጣን ናቸውና
ቀኝ ብርቱ ነው ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ብርቱ ናቸውና

ኃጥአን በግራ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው
ግራ ጠማማ ነው ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመሥራት ጠማማ ናቸውና
ግራ ዳተኛ ነው ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመስራት ዳተኞች ናቸውና፡፡ ቤተክርስቲያን ለምን አትሄዱም ሲሏቸው እዚህ ቦታ ደርሼ መጥቼ ደከመኝ ጸልዩ ሲባሉ ራሱ እግዚአብሔር ፍላጎቴን ያውቅ የለ ስገዱ ጹሙ ሲባሉ ምክንያት አያጣቸውምና
ግራ ሰነፍ ነው ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት አይችልም ኃጥአንም በምግባር በሃይማኖት በኩል ጠንከር ያለ ነገር ሲገጥማቸው ደከመን ሰለቸን ብለው ይተውታል፡፡ ለኃጢአት ግን አይደክሙም ሌሊት ጨለማን ተገን አድርገው ሲዘርፉ ሲዘሙቱ ይዉላሉና፡፡
ማጠቃለያ
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣው በአባቱ ሥልጣን በራሱ ሥልጣን በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ነው
የሰው ልጆች ከሞት በኋላ ፈርሰው በስብሰው አይቀሩም በኋላ በፍጻሜ ዓለም ጌታችን በመጣ ጊዜ ይነሣሉ፡፡
የሰው ልጆች ከሙታን ከተነሡ በኋላ ጻድቃን ወደ ዘለዓለም ዕረፍትና ሕይወት ኃጥአን ደግሞ ወደ ዘለዓለም ዕፍረትና ጉስቁልና ይሄዳሉ፡፡
የትንሣኤያችን በኩር የድንግል ማርያም ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment