Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አምስት



የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች


አባቶቻችን ሊቃውንት

በቤተ ክርስቲያን ብዙ ሊቃውንት ቅዱሳን የክርስትና እምነት ዶግማን ወይም መሠረተ እምነት ምን እንደሆነ አስተምረውናል፡፡ ይህ ትምህርት ትምህርተ አበው ሃይማኖተ አበው ነው ይህ የአባቶች ትምህርትም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው፡፡
አንዳንዶቹን ቅዱሳን አባቶች ዐቃብያነ እምነት እንላቸዋለን እነዚህ አባቶች መናፍቃንን የረቱና ያሳፈሩ ሃይማኖታችንን ያለነቀፍ ወይም ኑፋቄ ያቆዩ ስለሆኑ ዐቃብያነ እምነት እናላቸዋለን፡፡ እውነትን በሐሰት ለውጠው ከክርስትናው ትምህርት ውጪ የማይገባትምህርት ያስተማሩትን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት አንጻር በመመርመር መልስ የሰጡ ክርስትናን የጠበቁ ናቸውና በእውነትም ስሙ ይገባቸዋል፡፡
ቅዱሳን አበቶቻችን መናፍቃንን በትምህርታቸው ወደ ቀናው መንገድ(ትምህርት) ይመለሱ ዘንድ በፍቅር ያቀኗቸው ነበር እንጂ አላገለሏቸውም ትምህርታቸውንም በነጻነት በየጉባኤያቱ እንዲያስረዱ እድል ይሰጦቸው ነበር፡፡
እነዚህ አባቶች መናፍቃንን በመርታት ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኖች የመንፈሳዊ ሕይወት ልምምድ እንዲያደርጉ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ሕብረት እንዲያነክሩ ያስተምሩ ነበር፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወት እድገት ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን አበርክተዋል፡፡ ያስተማሩትንም በተግባር ኖረውበታል፡፡ እነዚህ አባቶች ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ናቸው ለዚህም ነወ ሕይወታቸውን ትምህርትታቸውን የምናጠናው የምንዘክራቸው ይህ ምክንያቱ አንድና አንድ ነው ትምህርት ቤቶቻችን ጭምር ናቸውና ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ትጠቀምባቸዋለች ለመሠረተ እምነታችን መሠረት የሚሆን ትምህርት አስተምረው አልፈዋልና፡፡

ቀኖና


ቀኖና ማለት ሕግ፣ ሥርዓት፣ ደንብ፣ ፍርድ፣ ቅጣት፣ መጠን፣ ልክ ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ) መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ 799/፡፡ በግሪኩ ካኖን ሲኾን በዕብራይስጡ ቃኒህ ይሉታል፡፡ ይኸውም አንድን ነገር ለመለካት፣ ለመመዘን፣ ትክክል መኾኑንና አለመኾኑን ለመለየት፣ መጠኑን ለማወቅ የሚያገለግል መለኪያ ወይም መስፈርት ነው፡፡
ማኅበረ ሰብእ እስካለ ድረስ ሕግ አለ፡፡ ሕግ እንዲኖር የኹለት ሰዎች በአንድ ላይ መኖር በቂ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞአሐቲ ጕባኤእንዲል የምእመናን ስብስብ ስለኾነች የራሷ ሕግ አላት፡፡ አባቶችያልተገራ ፈረስ የባለቤቱን ጥርስ ይሰብራልእንደሚሉት ይኽ የምእመናን ስብስብ ሰላማዊ እንዲኾን የሚያደርገው የቤተ ክርስቲያን ሕግ ወይም ሥርዓትም ቀኖና ይባላል፡፡
ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው ሕግ ኹለት ዓይነት ነው፤ ተፈጥሮአዊ ሕግና የስምምነት ሕግ፡፡ የተፈጥሮ ሕግ የምንለው የእግዚአብሔርን ሕግ ነው፡፡ ሰዎች ይኽን የእግዚአብሔር ሕግ ሊለውጡት አይችሉም፡፡ ለምሳሌ ወንድ ከሴት ጋር መጋባት አምላካዊ ሕግ ነው፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትም ይኽን የተፈጥሮ ሕግ የሚቃረን ነው፡፡ ፈረስና አህያ ተዳቅለው በቅሎን ይወልዳሉ፡፡ ነገር ግን በቅሎ ራሷን መተካት አለመቻሏ ከሕገ ተፈጥሮ ውጪ የተወለደች መኾኗን ነው የሚነግረን፡፡ ጦጣና ዝንጀሮ ተዳቅለው የሚወልዷቸው እንስሳትም አሉ፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ በቅሎ ራሳቸውን መተካት አይችሉም፡፡ ለምን? ስንልም ከሕገ ተፈጥሮ ማለትም ከእግዚአብሔር ሕግ ውጪ የተወለዱ ናቸውና፡፡ ስለዚኽ ተፈጥሮአዊ ሕግጋትን ተቃርነን የምናደርጋቸው ነገሮች ትርፉ ድካምና በራስ ላይ ጉዳትን መጨመር ብቻ ነው የሚኾነው፡፡
የስምምነት ሕግ የምንለው ደግሞ በፓርላማ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጣውን ሕግ ማለታችን ነው፡፡ ምንም እንኳን የስምምነት ሕግ ብለን ብንጠራውም ቅዱስ ሲኖዶስን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ስለኾነ እንዲኹ የሰዎች ስምምነት ነው ብለን የምንወስደው ወይም ዝቅ አድርገን የምንመለከተው አይደለም፡፡ እነዚኽ ሕጎች ኹለት መሠረታዊ ጠባያት አሏቸው፡፡ ጥቅል ወይም ዝርዝር ሕጎች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡
የስምምነቱ ሕግ ጊዜያዊም ለረዥም ጊዜ የሚቈይም ሊኾን ይችላል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር በምሕረት ዓይን እንዲያየንና በቤተ ክርስቲያን እንዲኹም በዓለም ላይ የተጋረጡትን ችግሮች እንዲያርቅ ቅዱስ ሲኖዶስ ለኹለት ሳምንት ጾምና ጸሎት ቢያውጅ ጊዜአዊ ሕግ (ቀኖና) ይባላል፡፡ በዓመት ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መኖራቸው ግን በሕይወት እስካለን ድረስ የሚገዛን ቀኖና ነው፡፡
የስምምነት ሕግ የተጻፈም ያልተጻፈም ሊኾን ይችላል፡፡ ያልተጻፈ መኾኑ ግን ሕግ ከመኾን አይከለክለውም፡፡ ካልተጻፈ ተብሎ አይጣስም፡፡ እያንዳንዳችን የአንዳችንን ፍላጐት ለመጠበቅ ተፈጥረናልና /ዘፍ.4/፡፡

ቀኖና ቤተ ክርስቲያን

ቀኖና የሚለው ቃል እንደ አኹኑ ለቤተ ክርስቲያን ከማገልገሉ በፊት ሕዝቡ በማንኛውም የዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚዳኝበት ሕግን ያካተተ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያናዊ (ክርስቶሳዊ ሕግ) እና ሕዝባዊ (ቄሳራዊ) ሕግ ተብሎ የተለየው በኋላ ነው /The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 277/፡፡ ቤተ ክርስቲያንም መዠመሪያ አከባቢ ላይ ቀኖና የሚለውን ቃል ስትጠቀም የመጻሕፍቶቿን ዝርዝር፣ የሥርዓተ አምልኮቷን አፈጻጸም፣ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን አፈጻጸም፣ የአንድ ክርስቲያን ሥነ ምግባር ምን መምሰል እንዳለበት ለመግለጥ ነበር፡፡ ይኽ ቀኖና እንዲኖራት ምክንያት የኾናትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይከሰቱ የነበሩት አለመግባባቶች ናቸው፡፡ በተለይ አንዳንድ ከእምነትም ከምግባርም የሚወጡ ሰዎች ሲገኙ ምእመናን ግራ እንዳይጋቡ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይወጣ ነበር፡፡ እንደ ችግሩ መጠንም የሚወጣው ሕግ (ቀኖናው) ዳርቻው አጥቢያዊ፣ ወይም ሀገረ ስብከታዊ፣ ወይም ሀገራዊ፣ ወይም ዓለማቀፋዊ ይዘት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ትንሽ ቆየት ብለን እንደምንመለስበት በጉባኤ ኒቅያ የተደነገጉት ቀኖናት ዓለማቀፋዊ ይዘት ያላቸው ቀኖናት ናቸው /Ibid/፡፡
ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊት ካልኾነች እውነተኛ አይደለችም፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ ማወቅ ብቻውን ትርጕም የለውም፤ አጋንንትም ያውቁታልና፡፡ ትርጕም የሚኖረው ስናምንና ስንጠመቅ ነው፡፡ ይቅርታ ሰላምን እንደሚሰጥ ይታወቃል፤ ይቅር ካላልን ግን ትርጕም የለውም፡፡ በሌላ አገላለጽ እምነታችንን የምናከናውንበት ዝርዝር ቀኖና ከሌለ እምነታችን ትርጕም አልባ ነው፤ ምክንያቱም ቀኖናእምነታችንን እንዴት እንፈጽም?” ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ዝርዝር አፈጻጸም ነውና፡፡
የቤተ ክርስቲያን ቀኖናት የተሰጡት በሐዋርያት ነው፡፡ ለሕዝቡ ያስተማሩትም እነርሱ ናቸው፡፡ በእነርሱ ወንበር የተቀመጡት ሊቃነ ጳጳሳትም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ጊዜውን የዋጀ ቀኖና ይሠራሉ፡፡
ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከሌለ የሚሠለጥነው ዲያብሎሳዊ ሕግ ነው፡፡ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዋና ዓላማም ሰዎችን ሥርዓት አስይዞ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖራቸው ማድርግ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ብንጠቅስ አርዮስን ለመገሰፅ ቤተ ክርስቲያን 25 ዓመት ፈጅቶባታል፡፡ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደብረ ሐይቅ (የግራኝ መሐመድ ወንድም የታሰረበት) ደብረ ዳሞ፣ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ክብራን ገብርኤል፣ ግሸን ደብረ ከርቤ እና ሌሎች ታላላቅ ገዳማት ነበሩ፡፡ ይኽ የኾነበት ዋና ምክንያትም የቀኖና ዓላማ ሰዎች እንዲታረሙ ማድረግ እንጂ ሰውን መቅጣት ስላልኾነ ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አንድን ሌባ ያገኛሉ፡፡ ይዘዉም እጁን ይቈርጡታል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ታላቁ ሊቅ አለቃ አካለ ወልድም በቅኔ አድርገው አጼ ቴዎድሮስን ወረፏቸው፡፡ አለቃ አካለ ወልድ ይኽን ያደረጉበት ዋና ምክንያትምሰውዬው እጁ ስለተቈረጠ ከዚያ በኋላ መሥራት አይችልም፤ የሰው ጥገኛ ነው የሚኾነው፡፡ ቀኖና ሊሰጠው ይገባ ነበርሲሉ ነው፤ እንደተናገርን የቀኖና ዓላማ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መጉዳት ወይም ጫና መፍጠር አይደለምና፡፡
ሕግ ከጽዮን ይወጣል” /ኢሳ.23/ እንደተባለ የሕግ ምንጭ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ሕግ አውጪ ብቻ ሳትኾን ሕግ ተርጓሚዋና ሕግ አስፈጻሚዋም ርሷ ራሷ ናት፡፡ ሕጓም ዓለምአቀፋዊ ዳርቻ አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ኹሉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንም አለ፡፡ አትስረቅ፣ አትግደል፣የሚሉት የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ናቸው፡፡ በመኾኑም እነዚኽ ሕጎች በማንኛውም ቄሣራዊ ሥርዓት፣ በማንኛውም ዓይነት ቋንቋ፣ በማንኛውም ዓይነት ማኅበረ ሰብእ ውስጥ አሉ፡፡ የሥላሴ አጥር ዳር ድንበር የለውምና የቤተ ክርስቲያን ሕግም ዳር ድንበር የለውም፡፡ ጾም የቤተ ክርስቲያን ሕግ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ግን እንደየቦታውና እንደየሰዉ ኹናቴ ሊለያይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በዓፋር የሚኖር ክርስቲያን እስከ ዘጠኝ ሰዓት ካልጾምክ ካልነው በውኃ ጥም እንገድሏለን፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚኖረው ክርስቲያን ዓፋር ላይ እንደሚኖረው ክርስቲያን 400 ሰዓት ላይ ውኃ ልጠጣ ቢል ግን የተለየ ምክንያት ከሌለው በቀር ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲኽ ሲባል ግን እያንዳንዱ ሰው በራሱ ሕሊና ያለበትን ኹናቴ እያመዛዘነ በራሱ ውሳኔ የሚያደርገው ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እንዲኽ ዓይነት ለየት ያለ ቀኖና (Exceptional Canon) የሚያወጣው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ አካል ብቻ ነውናይኼ እኮ ቀኖና ነው፤ ባናደርገውም ምንም ችግር የለውምከሚለው ግላዊ አስተሳሰብ ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የራሱ የኾነ ልዩ ባሕርያት አሉት፡፡
ሥልጣን ባለው አካል የሚደነገግ፣ የሚተገበር፣ የሚሻሻል ነው፡፡ ሲደነገግም ሲሻሻልም በግለሰቦች የግል ፍላጐት ወይም ፈቃድ የሚደነገግ ወይም የሚሻሻል አይደለም፡፡
ሃይማኖታዊ ይዘት አለው፡፡ ምክንያቱም ዓላማው ሰውን ኹሉ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ማፍለስ ስለኾነ ቄሣራዊ ይዘት የለውም፡፡ ቢኖርም እንኳን አንድ ክርስቲያን በዚኽ ምድር የሚኖረው ቆይታ ከሰማያዊ ሕይወቱ ጋር ሳይጣረስበት እንዴት መኖር እንዳለበት የሚያስረዳ ነው፡፡
ሰው ልጅ ከሚችለው በላይ ሸክምን አይጭንም፤ሸክሜ ቀሊል ነውእንዲል /ማቴ.1129/፡፡
የሸላሚነትና የቀጪነት ሥልጣን አለው፡፡ ቄሣራዊ ሕግ የሸላሚነት ይዘት የለውም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ግን ለምሳሌ ተጋድሎአቸውን በድል ያጠናቀቁት ክርስቲያኖች ቀን ተለይቶላቸው፣ ታቦት ተቀርጾላቸው በምእመናን ዘንድ ክብርን እስከ ማግኘት ይደርሳሉ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ የዘለዓለም አክሊል ዘውድ አለው፡፡
የአምልኮ ይዘት አለው፡፡ በውስጡ ጾም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት እና የመሳሰሉትን ኹሉ ያካትታል፡፡
የመመዘን ጠባይ አለው፡፡ ለምሳሌ የቃየን መሥዋዕት ያልሰመረችው መሥዋዕት ስላላቀረበ ሳይኾን በሕጉ መሠረት አሰስ ገሰስ ኾኖ ስለተገኘ ነው /ዘፍ.4/፡፡
በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ የተደነገገ አይደለም፡፡
ሰዎችን ደስ ለማሰኘት አይወጣም፤ የሚወጣው እግዚአብሔር ደስ ለማሰኘት ብቻ ነው፡፡ለዓለም ከሚመች ከንቱ ልፍለፋ ራቅእንዲል ለዓለም የሚመች ቀኖና አይወጣም፡፡ ቀኖና የሚወጣው የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድግና ምእመናን በሚኖሩበት ማኅበረ ሰብእ ውስጥ አርአያ እንዲኾኑ ነው፡፡
አንጻራዊ ጽድቅ ስለሌለ አንጻራዊ ቀኖናም የለም፡፡ ጥቁሩን ጥቁር ነጩንም ነጭ የሚል እንጂ የተድበሰበሰ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አታወጣም፤ እንዲኽ ካልኾነ የውጫሌ ሕግ ነው፡፡ በዓለማዊ ሕግ የወንጀሉ መጠን ይታያል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕግ ግን ወንጀል ወንጀል ነው፡፡

ትውፊት


በሰዋስዋዊ ዘይቤው ሲፈታ፥ ትወፊት ማለት ስጦታ፣ ልማድ፣ ትምህርት፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ሥርዓት፣ ከጥንት ከአበው ሲያያዝ ሲወርድ፥ ቃል በቃል ሲነገር የመጣ ማለት ነው /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ፣ 397/፡፡ ጽርዓውያንምፓራዶሲስይሉታል፤ አንድን ነገር እጅ በእጅ ለሌላ ሰው ማስረከብን ወይም ማቀበልንም ያመለክታል፡፡ ዕብራውያን ደግሞማሳር - ማቀበልእናቂብል - መቀበልየሚሉ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያናዊ ትርጓሜው ስንመለከተው፥ ትውፊት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጠቅላላ በአበው፣ በነቢያት፣ በሐዋርያት፣ በጳጳሳት፣ በሊቃውንት፣ በካህናት በኵል የሚያስተላልፈው ሕያው (ሕይወትን የሚሰጥ) ቃል ማለት ነው፡፡ ይኽ ሕያው ቃል ቀደምት አበው ከእግዚአብሔር የተቀበሉትና ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት፥ ቤተ ክርስቲያንም በየጊዜው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የምትጠቀምበት ሕያው ትምህርት ነው፡፡

በቅዳሴያችን ጊዜ ቄሱነዋ ወንጌለ መንግሥት - መንግሥተ ሰማያትን የምትሰብክ አንድም ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታገባ ወንጌል ይኽቺ ናትብሎ ለንፍቀ ካህኑ መስጠቱ፥ ንፍቀ ካህኑምመንግሥቶ ወጽድቆ ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ - ጌትነቱንና ቸርነቱን የምትናገር የሰጠኝን ወንጌልን ሰጠኹኽብሎ ለዲያቆኑ መስጠቱ ሐዋርያት ከሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ተቀብለው ለማስተማራቸው አምሳል ነውና ትውፊት ቅብብል፣ ውርርስ መኾኑን በግልጽ ያሳያል /ሥርዓተ ቅደሴ 1053 አንድምታው/፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት(ዶግማ) ምንጮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስና ትዉፊት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ቅዱሳን መጽሕፍት በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ(ሥፍራ) አላቸው፡፡ አሥራው መጻሕፍት ሙሉዕ የሚያደርገው ትዉፊት እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ትዉፊት ስንል በቃል(በጽሑፍም) የሚተላለፈውን ትውፊት፣የቅዳሴ መጻሕፍት የአበው ጽሑፎች ቀኖናዎች በጉባኤያት የተወሰኑ ውሳኔዎች (የሃይማኖት መግለጫዎች) እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች(Practices in the church) የሚያጠቃልል ነው፡፡
እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፥ እግዚአብሔር ከፍጥረት መዠመሪያ አንሥቶ በጽሑፍም ያለ ጽሑፍም የገለጠውን እውነት የምናገኘው በቅዱስ ትውፊት ውስጥ ነው፡፡ በመኾኑም የተጻፈውና ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ለድኅነታችን የሚኾን የእግዚአብሔርን መገለጥ የያዘ ስለኾነ እኵል አስፈላጊ ነው፡፡
እንደ ምዕራቡ ቤተ ክርስቲያን (ካቶሊክ) ትርጕም ቅዱስ ትውፊት ማለት ያልተጻፈ ነገር እና በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍን ብቻ የያዘ ነው /J.N.D. Kelly, Early Christian Doctrines, pp 30-31/፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ግን ከላይ እንደገለጥነው ቅዱስ ትውፊት የተጻፈውም ያልተጻፈውም ኹሉ የሚያካትት ነው፡፡ በመኾኑም (ቅዱስ ትውፊት) በውስጡ መጽሐፍ ቅዱስን፣ የአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንና ቀኖናትን፣ የሦስቱን ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያትን (ጕባኤ ኒቅያ፣ ጕባኤ ቁስጥንጥንያ፣ ጕባኤ ኤፌሶን) እና ትእዛዛትን፣ መጻሕፍተ ቅዳሴያትን፣ ገድለ ቅዱሳንን፣ ቅዱሳት ሥዕላትን፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርና የሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸምን፣ ክርስቲያናዊ የአለባበስ፥ የአነጋገር እንዲኹም የአመጋገብ ሥርዓትን ሌላውንም ኹሉ ያካተተ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ብዙ ቁም ነገሮችን የያዙ ናቸው፡፡ ሁሉም በመጽሐፍ ቅዱስ(አሥራው መጻሕፍት) ያለና የተገለጠ(የተጻፈ) ነው ለማለት ይቸግራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ምሉዕ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡(ዮሐ 2030 ዮሐ 2125) ትዉፊት ምንጊዜም የመጽሐፍትን ምሥጢር ነገረ ድኅነትን ነገረ ቅዱሳንን ነገረ ክርስቶስን ሌሎችን የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ጋር የሚጣጣም እንጂ የሚቃረን መሆን የለበትም፡፡
ትውፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ቀጥሎ ስለ ክርስትና የሚነግረን እና ከቅዱሳን ሐዋርያትና ከአባቶቻችን የተቀበልነው ትምህርት ነው፡፡

ትውፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፉ ነገር ግን ፈጽሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያልሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችን፣ ታሪኮችን የያዘ ነው፡፡ ትውፊት ቅዱሳት መጽሐፍትም ከመጻፋቸው በፊት የነበረ ነው፡፡ ይህም በቃልም ሆነ መጽሑፍ የሚወርሱት ነው፡፡

ለምሳሌ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እሑድን የክርስቲያን ሰንበት እንደሆነ ታስተምራለች በዚህ ወቅት ነው ክርስቲያኖች ሁሉ ተሰብስበው እግዚአብሔርን የሚያገለግሉት ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉት ይህ ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተጻፈም በትውፊት ያገኘነው ነው፡፡

ትዉፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ በፊት ነበረ

ትውፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀዳሚ ነው፡፡ ትውፊት ከአባታችን አዳም ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ እስራኤል በተጻፈ ሕግ ከመመራታቸው በፊት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ሲመራቸው የነበረ ትውፊት ነው፡፡
ለአብነትም
1. በኦሪት ዘፍጥረት አቤል ለእግዚአብሔር ንጹሕ መስዋዕት አቀረበ(ዘፍ. 44) ታዲያ አቤል መስዋዕት ማቅረብ እንዴት አወቀ? እምነቱንስ ከየት አገኘው ብለን ብንጠይቅ ያለጥርጥር ከአባታችን ከአዳም እንዳገኘው መናገር ይቻላል፡፡ ይህም የሆነው በትውፊት ነው አቤል ይህንን ያደረገው ሙሴ ስለመስዋዕት ከመጻፉ 1400 ዓመት በፊት ነው፡፡
2. አባታችን ኖኅ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ያቀረቡት የሚቃጠል መሥዋዕት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በተቀበሉት ትውፊት መሠረትም ስለመሥዋዕትና መሰዊያን ስለመሥራት ያውቁ ነበር (ዘፍ. 127)
3. ኖኅ በተመሳሳይ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ (ዘፍ 820-21)
4. አብርሃም ካህኑን መልከ ጸዴቅን ስያገኘው ያሳየው ክብር ለካህናት ስለሚገባው ክብር ከመጻፉ አስቀድመው የተገለጹ ናቸው (ዘፍ. 1520)
5. በክርስትናም የሐዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች በትውፊት ያገኙትን የብሉይ ኪዳን ታሪኮች ተርከዋል፡፡ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ሙሴን የተገዳደሩትን ስም በመጥቀስ ጽፎል ይህ ግን በሙሴ መጽሐፍ አልተጠቀሰም፡፡‹‹ኢያኔስና አያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት››(2 ጢሞ 38)
የትውፊት ጥቅም
ትውፊት ጥሬውን ብስል ደረቁን እርጥብ አድርጎ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምረናል፡፡ ትውፊት ሐዲስ ኪዳንን ከብሉይ ኪዳን፤ ብሉይ ኪዳንን ከሐዲስ ኪዳን የምንመሳከርበት ነው፡፡ ያለ ትውፊት መጽሐፍ ቅዱስን ምሉዕ ማድረግ አይቻልም፡፡
ሌላው የትውፊት ጥቅም የመጽሐፍትን ቃል ሳይከለስ ሳይለወጥ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላልፋል፡፡
የመጽሐፍትን ትርጉም ለማወቅ ያስረዳናል፡፡ ለምሳሌ (ዮሐ 2030) ላይኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገስለዚህ በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረገውን ለማወቅ ግድ ትውፊት ያስፈልገናል፡፡ (ዮሐ 2125) ላይምኢየሱስም ያደረገው ሌላ ብዙ ነገር ደግሞ አለ፡፡ ሁሉም እያናዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸው ይመስለኛል፡፡ሲል ወንጌላዊው ዮሐንስ ተናግሮዋል፡፡ ስለዚህ ጌታ ያደረገውን ለማወቅ የግድ ትውፊት ያስፈልገናል፡፡
በትውፊት የቤተ ክርስቲያን ንዋያትና የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ለእኛ ደርሰውናል፡፡
በትውፊት የቀና ሃይማኖት ደርሷል፡፡ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጓሜ እያንዳንዱ ሰው እንደሚረዳው ይተርጉም ተብሎ ቢተው ኖሮ አሁን ቤተ ክርስቲያን ላይ ካለው ይልቅ ብዙ መከፋፈል በተፈጠረ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ለእኛ የደረሰን በትውፊት ነው፡፡
ትውፊት በዙ ሥርዓቶችንና ትምህርቶችን ጠብቆ አቆይቶልናል፡፡ ለምሳሌ ሰንበትን ማክበር፥ ፍትሐት፥ ክህነት ደረጃና ተግባር ወዘተ . . .

ማጠቃለያ

ትውፊት ስንል በሰዎች የተሰሩ ባዶ ዋጋ ቢስ ልምዶችና ወጎች ማለታችን አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ ከመጽሐፍ ጋር የማይዛመዱትንና ረብ የለሽ መሆናቸውን የተናገረላቸውን ሰዋዊ ልማዶች ማለታችን አይደለም፡፡ ነገር ግን የቀናውንና በትውፊት የደረሰን የጌታችን ትምህርት የሐዋርያት ትምህርት የሆነና ከትውልድ ወደ ትውልድ አልፎ የደረሰንና ስለ ቤተክርስቲያን ሥርዓት እና ቀኖና በቅዱሳን አባቶች ጉባዔ የተወሰነውንና ከአባቶቻችን መምህራንና የቤተክርስቲያን የእምነት ሰማዕታት ከተቀበልነው ትምህርት ጋር የተስማማውን እንዲሁም እውነተገኛ ሐዋርያዊ ትውፊት ማለታችን ነው፡፡ ይህም ትውፊት የክርስትናችን መሠረት ነው፡፡ትምህርታችን ከዚሁ አባቶች ካስተማሩት ትምህርት የሚቀዳ እንጂ በየዘመኑ የተሻሻለ አዳዲስ ሐሳቦች የሚጨመሩበት አይደልም፡፡
ይቆየን ይቀጥላል

ስብሐትለእግዚአብሔር

1 comment:

  1. ዶግማንና ቀኖናን በተመለከተ ጥያቄዎች አሉኝ። ብጠይቅ መልስ አገኝ ይሆን፧

    ReplyDelete