በዲ/ን ያሬድ መለሰ
መነሻ
በወጣትነት ሕይወት ውስጥ በብዙ ወጣቶች ዘንድ እንደ ጥያቄ የሚቀርበው ጉዳይ ነው የመተጫጨት ሕይወት ፡፡ በክርስትና የሕይወት መስመር ውስጥ አንድ ክርስቲያን ሁለት ምርጫዎች አሉት፡፡ የመጀመርያው የምንኩስና ሕይወት ሲሆን ሁለተኛው የትዳር ሕይወት ነው፡፡ ከመጽሕፍት ትምህርት እንደምንረዳው ሁለቱም ሕይወት እግዚአብሔር የባረካቸው ናቸው፡፡(ማቴ 19:1-6) (ዕብ 13፡4) (1ቆሮ 7፡1-7) ብዙ ቅዱሳን አባቶችም የሄዱበት የሕይወት መስመር ነው፡፡ይህን አስደሳች የሕይወት መስመር ጣፋጭ ለማድረግ ታድያ እግዚአብሔርን አስቀድሞ መለመን ወደ እርሱም መመለስ ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ያልታከለበት ምርጫ የመተጫጨት ሕይወት ፍጻሜው ያማረ አይሆንም፡፡ ስለዚህም በሕይወት ምርጫችን እግዚአብሔርን ማስቀደም ይሆንብናል፡፡ የዚህ ጽሑፍ በመተጫጫት ሕይወት ውስጥ መንፈሳዊ ወጣቶች ሊያደርጉት የሚገባውንና ማድረግ የሌለባቸውን የሚዳስስ ነው፡፡ ዓላማውም ስለመተጫጨት ሕይወት ማስተማር ነው፡፡ስለመተጫጨት ሕይወት ከማየታችን በፊት ስለትዳር አንዳንድ ነጥቦችን መዳሰስ አስፈላጊ ነው፡፡
የጋብቻ አጀማመር
ጋብቻ የተጀመረው በመጀመሪያው የሰው ዘር አባትና እናት በሆኑት በአዳምና በሔዋን ነው፡፡መሥራቹም ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ በመሥራቹም የጋብቻ ክቡርነትና ፀጋነት ታወቀ፡፡በዚህም ምክንያት የቤተሰብን የኅብረተሰብን ምንጭ መሠረተ (ዘፍ 2፡18-23) (ኩፋ 4፡6) በአዳምና በሔዋን መካከል ያለው ጋብቻ መወሰን ያለበት ነው፡፡ ምክንያቱም ለአዳም ብዙ ሴቶች አለመፈጠራቸው ለአንድ ወንድ አንዲት ሴት እንጂ አያሌ ሴቶች ያልተፈቀዱለት መሆኑን እንረዳለን፡፡ይህንም በብሉይ ዘመን ከነበሩ ደጋግ አባቶች ዘንድ ብንመለከት የጸና ነው፡፡ ለምሳሌ የኖኅ ጋብቻ የተባረከ ሕጋዊ ጋብቻ ነበር፡፡ የአብርሃምም እደዚሁ፣ የይስሐቅና የርብቃ፣ የዮሴፍና የአስናት ጋብቻም የተባረከና ቅዱስ ነበር፡፡ጋብቻ በሕገ ልቡና እንደነበሩ አባቶች በኦሪትም የነበሩ ቅዱሳን አባቶች አክብረውታል፡፡ ስለዚህም የቤዛዊተ ዓለም የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተሰቦች በቅዱስ ጋብቻ የተገኙ ናቸውና፡፡ እዲሁም የዘካሪያስና የኤልሳቤጥም ጋብቻ መለኮትን ያጠመቀ ዓለም የሰበከ ቅዱስና ነብይ ወሰማዕት መጥምቁ ዮሐንስን አስገኝቷል፡፡
በብሉይ ኪዳን የነበሩት የአባቶቻችን የተባረከና ቅዱስ ጋብቻ እንደነበረ የአብርሃምና የሣራ ጋብቻ የይስሐቅና የርብቃ ጋብቻ መመልከት ይቻላል፡፡በዚህ ዘመን የዘመድ ጋብቻ ሲመረጥ ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም በምድር ላይ ሰው ዘር ባለመብዛቱ ነው፡፡ (ዘፍ 24፡1-) (ዘፍ 23፡1-5) (ዘፍ 28፡29) (1 ኛሳሙ 18፡22-29) ኦሪት ከተተካ በኋላ ግን ይህ የሥጋዊ ዝምድና ጋብቻ ቀርቷል፡፡ ዘመድም ከዘመዱ እንዳይጋባ ትዕዛዝ ወጥቷል፡፡ (ዘፍ 18፡6-18) (ዘፍ 20፡17)
የሐዲስ ኪዳንን የጋብቻ ክቡርነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ገልጦልናል፡፡ (ዮሐ 2:1-11)ጌታም ስለ ጋብቻ ሲያስተምር፡-ጋብቻ ሰው በዘፈቀደ ሊፈታው የማይገባ ጽኑዕ የውሕደት ማሰሪያ እግዚአብሔር አምላክም የሚገኝበትና የሚያዝበት ትልቅ ምሥጢር እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ (ማቴ 19:1-6) (ዕብ 13፡4)
የጋብቻ ለምን
የጋብቻ መሰረታዊ ዓላማዎች ሦስት ናቸው፡፡ እነዚህም፡-1. በኑሮ ለመረዳዳትና ሕይወትን በጋራ ለመምራት ነው
‹‹ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት›› (ዘፍ 2፡18) በዚህ ቅዱስ ቃል መሠረት የምንረዳው ጋብቻ ሲመሠረት ዓላማው መረዳዳት መሆኑን ነው፡፡ መረዳዳት ሲባልም በፍቅርና በመተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር የሴቷ ብቸኛ ግዴታ ሳይሆን የወንዱም ኃላፊነት ነው፡፡ 1ጴጥ 3፡1-7
2. ለመባዛትና ዘር ለመተካት ነው፡፡
• ወላጆች አምሳያቸውን ልጅ በመውለድ ሲተኩ የሰው ዘር ከገጸ ምድር እንዳይጠፋ ይረዳል፡፡
• ጋብቻን ያጠናክራል ያጸናል፡፡
• የተጋቢዎችንም ቤት በደስታና በፍቅር ይሞላል፡፡
ይህ ዘር የመተካቱ ነገር ግን እግዚአብሔር በፈቀደ የሚደረግ ነው፡፡ ተጋቡ ማለት ዘር ይተካሉ ማለት አይደለም፡፡ ቀዳሚውና ዋናው በነፍስ በሥጋ በሃይማኖት መተሳሰብ መረዳዳትና መተጋገዝ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
3. ከዝሙት ኃጢአት ለመጠበቅ ነው፡፡
የጋብቻ አስፈላጊነት ሰው ለፈቀደሰው ሥጋውን ዝርው አድርጎ በነፍስም በሥጋም እንዳይጎዳ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ዝሙት ጠንቅ በተናገረበት ወቅት በባልና በሚስት መካከል ሚስት በገዛሥጋዋ ላይ ሥልጣን እንደሌላት ባልም በገዛ ሥጋው ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደሌለው ይገልጽልናል፡፡
‹‹በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላል›› ጋብቻ ከፈቃደ ሥጋ ለሚመጣ ማንኛውም ፈተና ፍቱን መድኃኒት ነውና፡፡ (1ቆሮ 7፡1-7) (ዕብ 13፡3)
ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት
የጋብቻ መቅድሙ መተጫጨት ነው፡፡ ቅዱስ ጋብቻን ለመመሥረት (ይህም ከእጮኝነት ዘመን የሚጀምር ነው) የሚያስብ ሰው አስቀድሞ ከግምት ውስጥ ሊያስገባቸው የሚገቡ ጉዳዎችን አሉት፡፡
1. በሃይማኖት አንድ መሆን፡- ሃይማኖት የሁሉ ነገር መሠረት ነው በጋብቻ ሕይወት በአንድ ላይ ለመኖር የተጫጩ እጮኛሞች አንድ ሃይማት ሊኖራቸው ይገባል (2ኛ ቆሮ 6፡14)
2. ድንግልናቸውን መጠበቅ፡- የተክሊልን ብርሃን ለማግኘት ድንግልና አስፈላጊና ዋናው ነገር ነው ድንግል ማለትም ወንድ ያላወቃት ሴት ወይም ከሴት ያልደረሰ ወንድ ማለት ነው፡፡
3. የሁለቱም ፈቃደኝነት፡- መተጫጨታቸው በቤተሰብ በኩል ከሆነ የታጩት ሰዎች ፈቃደኛ መሆን አለባቸው፡፡ያለ ተጋቢዎቹ ፈቃድ የሚደረግ መተጫጨት ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡ ከወላጆቻቸው ፈቃድና መስማማት በኋላ በቅድሚያ ለመምህረ ንስሐ በመንገር ወደ ጋብቻው ቃል ኪዳን ያመራሉ፡፡
4. በጸሎት ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ፡- ሁለቱም ተጋቢዎች የሕይወትን ክብር የሆነውን የጋብቻን ሕይወት ለማግኘት ጉጉት ከመጀመራቸው ከማስተዋል ጋር በተሰበረ ልብ ሆነው በፍጹም አሳብ የልዑል እግዚአብሔርን እርዳታ በጸሎት ማማከር አለባቸው
5. የዕድሜ ገደብ፡- ወጣቶች በሚጋቡበት ጊዜ በተፈጥሮ ሕግ በሃይማኖት በሥርዓትና በማኅበረሰባዊ የጋብቻ ድንጋጌ መሠረት በእድሜ የማይቀራረቡ ከሆነ በጋብቻው ላይ ችግር እንደሚያስከትል ከወዲሁ መታወቅ ሊኖርበት ይገባል፡፡ ዕድሜን በተመለከተ ወንዶች ከ 20 በላይ ሴቶች ከ 15 ዓመት በላይ ሲሆናቸው መተጫጨትና መጋባት የሚፈቀድላቸው መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና ተመልክቶአል (ፍት.መን. 24 ም.3 ክፍል 2)
6. ሁለገብ መመጣጠን፡- ሁለገብ መመጣጠን ሲባል በዕድሜ፣ በጠባይ፣ በመንፈስና በአእምሮ ተመጣጣኝ ደረጃ እንዲኖራቸው በቂ ጊዜ መውሰድና ትልቅ ጥናት ማድረግ ይህም ለወደፊትና ለቀጣዩ ሕይወታቸው ሰላማዊነት ይረዳል፡፡
7. መንፈሳዊ እውቀት፡- የሚተጫጩ የፍቅር አጋሮች ስለ ሃይማኖታቸው፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሊማሩና ሊያውቁ ይገባል፡፡
8. የዝምድና ሁኔታ፡- ትልቁን ሊጠነቀቁለት የሚያስፈልገው ጉዳይ በተጋቢዎች መካከል ያለው የዝምድና ሁኔታ ነው፡፡ ይህንንም በ 3 መንገድ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በትዳር አብራኝ የምትኖረውን የሕይወት አጋሬን እንዴት መምረጥ እችላለሁ?፣ የተሳሳተ የእጮኝነት ሕይወት፣ መተጫጨት ለምን፣ የመሳሰሉትን ርዕሰ ጉዳዮች በሚቀጥለው ክፍል ይከታተሉ፡፡
No comments:
Post a Comment