የሰኞ ሥነ ፍጥረታት
ወይቤ እግዚአብሔር ለይኩን ጠፈር ማዕከለ ማይ
እሑድ ማታ ለሰኞ አጥቢያ እግዚአብሔር በውሃ መካካል ጠፈር ይፈጠር አለ በውቂያኖስና በሐኖስ መካከል ድንበር ይለይ ዘንድ
እንዳለውም ሆነ ፡፡ ጠፈር ማለት ኃያል ጽንዕ ማለት ነው ለሐኖስ ኃይል ጽንዕ ነውና አንድም ቤት ማለት ነው ለሰው ለአራዊት ለፍጥታት
ሁሉ መኖርያ ነውና፡፡ ሥዕለ ማይ ማለት ነው፡፡ሰማይ ያለውን ሰባቱ ሰማያት ይላቸዋል
ጠፈርንም በሰማያዊ ቀለም አምሳል ፈጥሮታል እጅግም ቢበራ ዓይን ይበዘብዝ ነበርና እጅግም ጨለማ ቢሆን ለዓይን ይከብድ ነበርና
በሰማያዊ ቀለም አምሳል ፈጥሮታል፡፡ ዕለተ ሰኞ ቀን በመጀመሪያ ሰዓተ ሌሊት ውሃ ከምድር ጀምሮ እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ ሞልቶ
አድሮ ነበርና ያንን ለሦስት ከፈለው፡፡
አንዱን እጅ(ሢሶውን) አርግቶ ጠፈር አድርጎታል ከላይ የቀሩ
አንዱን እጅ(ሢሶውን) ከጠፈር በላይ ያለው ብጽብጽ ውሃ (ሐኖስ)
አንዱን እጅ (ሢሶውን) ውቂያኖስ አድርጎታል-----------------------በምድር ያለ ነው
ምሳሌነታቸው፡- ከላይ የቀሩት ሁለቱ እጅ(ጠፈርና ሐኖስ) የአብና የመንፈስ ቅዱስ በዚህ ዓለም የሰፈረው አንዱ እጅ የወልድ
ምሳሌ ነው፡፡
ጠፈር ለምን ተፈጠረ?
ጠፈርን እግዚአብሔር የፈጠረበት ምክንያተት በዕለተ ረቡዕ ለሚፈጥራቸው ፍጥረታት ማደሪያ መመላለሻ ይሆን ዘንድ ነው፡፡
እመቤታችንና ዕለተ ሰኞ
በሰኞ ዕለት የብርሃን ማኅደር የኾነው ጠፈር ተገኝቷል /ዘፍ.1፡6-7/፡፡ ከእመቤታችንም ብርሃን ክርስቶስ ተገኝቷልና እመቤታችን
በዕለተ ሰኞም ትመሰላለች /ዮሐ.1፡5-9፣ ውዳሴ ማርያም ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው፣ ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ 15-17/፡፡
የማክሰኞ ሥነ ፍጥረታት20
“….እግዚአብሔርም ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደወገኑ ዘር ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል
አለ እንዲሁም ሆነ…..ሦስተኛ ቀን” (ዘፍ 1፥9-13)
በዚህ እለት በነቢብ ሦስት ፍጥረታት ተፈጥረዋል፡፡ በዕለተ ሠሉስ በ1ኛው ሰዓተ ሌሊት ሢሶው ውሃ ተከፍሎ በዚህ ዓለም ቀርቶ
ነበርና ይህንን ከሦስት ከፈለው
አንዱን እጅ ከምድር
በታች ሰደደው
አንዱን እጅ የሚያርፍበትን
ቦታ ጠርጎ ወደ ዳር አውጥቶ ውቅያኖስ አደረገው
አንዱን በዚህ ዓለም ተወው ዛሬ አብርሕት፣ቀላያት፣አፍላጋት የምንላቸው ከዚህ የቀሩ ናቸው፡፡
አንድም ፡- ለሁለት ከፈለው
አንዱን እጅ ከምድር
በታች አሰፈረው
አንዱን ውቅያኖስ አደረገው ዛሬ በዚህ ዓለም ያለው ውሃ ወጭትን አጥብበው ባፈሰሱት ጊዜ ጥቂት ልቅላቂ እንዳይታጣ እንደዚህ
ሆኖ የከረ ነው፡፡
እንደዚህ አድርጎ ካደላደለ በኋላ “……ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድር ላይ እንደወገኑ ዘር ያለበት ፍሬን የሚያፈራ
ዛፍን ታብቅል” ባለ ጊዜ ፡-
በመጥረቢያ(በጥፍር)
የሚቆረጡ ዕጸዋትን
በማጭድ የሚታጨዱ አዝዕርትን
በእጅ የሚለቀሙ አትክልትን ፈጠረ
ዕጸወ ገነትን
ዕጸወ ገነትን ለምን ለያቸው በጥፍር የሚቆረጡ በመጭድ የሚጻጨዱ በእጅ የሚለቀሙ አይደለምን ቢሉ በምድር ያሉ አዝርዕት ዕጸዋት
አትክልት ከአራቱ ባሕርት ነውና በዚህ ይለያሉ፡፡ በነፍስ ያፈራሉ ያብባሉ ቢወጓቸው ውሃ ይወጣቸዋል ቢሰቡቋቸው እሳት ይገኝባቸዋል
(እንደአስታ ዶግ ያሉ) ቢቆርጧቸው አፈር ሆነው ይበሰብሳሉና ከዕጽወ ገነት ይለያሉ፡፡
ሰው ወዳጁ እግዚአብሔር በዚህ ዕለት ከላይ ከጠቀስናቸው ፍጥረታት በተጨማሪ ብሩህ ብሩሁን መሬት በምሥራቅ በኩል በናጌብ
(በምድር ዳር) ጠቅልሎ አኑሮት ነበርና በምሥራቅ ኤደን ገነትን ተክሏል፡፡ ስለ ገነት ምንነት ስለ ሃያው ዓለማት
ስንነጋገር የምንመለስበት ሲኾን ለጊዜው ግን በገነት ውስጥ ስለ በቀሉት ዕፅዋት እንማማር፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በገነት ውስጥ (ለአዳም) ሦስት ዓይነት ዕፅዋትን ፈጥሮለታል፡፡ አንዱ የሚጠብቀው - ዕፀ በለስ፣ አንዱ የሚመገበው፣
ሦስተኛው ደግሞ የሚታደስበት - ዕፀ ሕይወት፡፡ እስኪ በጥቂቱም ቢኾን ስለ እነዚህ ዕፅዋት እንመልከት፡-
እንዲመገባቸው የተሰጡት ዕፅዋት
ሰው ወዳጁ እግዚአብሔር በገነት ውስጥ ታላላቅና ታናናሽ ዕፅዋትን ያበቀለ ሲኾን ታናናሹ ብቻ ቅጠላቸው ዐሥራ ኹለት ዐሥራ
ኹለት ክንድ ያክላል፡፡ እንደ ኮከብም ያበራል፡፡ ፍሬአቸውም ክብ ነው፡፡ ዛሬ እነዚህን ዕፅዋት የሚመገቡት በብሔር ብጹዓን ያሉ
ጻድቃን ቅዱሳንና በገነት ያሉ አዕዋፍ ናቸው፡፡ የሚያመጣላቸውም ነፋስ ነው፤ ነፋሱ እንደ ዝናብ ያዘንብላቸዋል፡፡ ያን ተመግበውም
ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ይኖራሉ /ገድለ ዞሲማስ/፡፡
ዕፀ ሕይወት
አበው እንደሚነግሩን ዕፀ ሕይወት ጫፏ ከሰማይ ይደርሳል፡፡ ፍሬዋ እንደ ሮማን ፍሬ ተነባብሮ ከእግር እስከ ራሷ ምሉ ነው፡፡
ከዕፀ ሕይወት ፍሬ አንዲቱን ቆርጦ በአፉ ጎርሶ አላምጦ ሳይውጣት እንደ ቀድሞው ፍሬ ተክታ ትገኛለች /ሕዝ.47፡12-13፣ ራእ.22፡2-3/፡፡
ከዕፀ ሕይወት አንዲቱን ፍሬ በበሏት ጊዜ ጣዕሙ ከአፍ፣ መዓዛው ከአፍንጫ ሳይለይ እስከ ሰባት ቀን ይቀመጣል /ኄኖ.7፡6-16/፡፡
ከዚህች ዕፅ የቀመሱ ሰዎች “እንዲህ ያለውስ ምግብ ያለ እግዚአብሔር ቸርነት ለፍጡር አይገባውም ነበር” እያሉ ያደንቃሉ፡፡ ቅጠሏ፣
አበባዋ፣ ፍሬዋ ያለ ደዌ ያለ ሕማም ነፍስን ከሥጋ ይለያል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ዕፀ ሕይወትን ብላም አትብላም አላለውም፡፡ ይህ ለምን እንደ ኾነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲመልስልን
እንዲህ ይለናል፡- “አዳም ቢፈልግ ኖሮ፥ ይህን ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን ዛፍ ከሌሎች ዛፎች ጋር አብሮ መብላት ይችል ነበር፤
በመኾኑም ስለ ዕፀ ሕይወት ብላም አትብላም አላለውም፡፡” በኋላ ላይ ይበልጥ እያብራራነው እንድምንሔድና ከዚህ መረዳት እንደምንችለው፥
የሰው ልጅ (አዳም) የራሱ የኾነ ነጻ ፈቃድ አለው፡፡ ይህ ነጻ ፈቃዱ እንኳንስ ዲያብሎስ እግዚአብሔርም ቢኾን ጣልቃ የሚገባበት
አይደለም፤ ሰው ራሱ እንደ ውዴታው የሚያዘው እንጂ፡፡ በመኾኑም በዚህ ነጻ ፈቃዱ፥ ከፈለገ ይህን ዕፀ ሕይወት በልቶ ለዘለዓለም
መኖር ይችል ነበር፡፡ ውሳኔው ለራሱ ለአዳም የተተወውም ስለዚሁ ነው፡፡
መረዳት ያለብን ግን ዕፀ ሕይወት ሲባል ዕፁ በራሱ ሕይወትን የሚሰጥ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ዕፁ የመታዘዝ ምልክት ነው፤
እግዚአብሔርን ቢታዘዝና እንደ ሕጉ ቢኖር ይህቺን ዕፅ በልቶ ይታደስ ነበር፡፡ ይታደስ ነበር ሲባል የሰው ልጅ በመዋቲነትና በኢመዋቲነት
መካከል ኾኖ ተፈጥሮ ስለ ነበር ወደ ኢመዋቲነት ይሸጋገር ነበር ማለት ነው፡፡ በበደለ ጊዜ ይህቺን ዕፀ ሕይወት እንዳይበላ መከልከሉም
ስለዚሁ ነው፡፡ ምክንያቱም ከበደሉ ሳይነጻ ይህቺን ዕፅ ቢበላ ኖሮ ለዘለዓለም እየበደለ ነበር የሚኖረው፡፡ በበደሉ ምክንያት የመጣበት
ጉስቁልና ለዘለዓለም አብሮት ነበር የሚኖረው፡፡ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔር ግን መጀመሪያ ሞቱንና ጉስቁልናዉን አስወግዶ ወደ ቀድሞ
ቦታው ወደ ገነት ወደ ቀድሞ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ከገነት እንዲወጣና ከዚህች ዕፅ እንዳይበላ አደረገው፡፡ ዛሬ ይህ
ዕፀ ሕይወት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ኾኖ ተሰጥቶናል /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/፡፡
ዕፀ በለስ
ይህቺ ዕፅ እግዚአብሔር በገነት በምዕራብ በኩል የተከላት ሲኾን አዳምና ሔዋን እንዳይበሏት የከለከላቸው ብቸኛይቱ ዕፅ ነች፡፡
እንዳይበሏት ሲከለከሉ እንኳን ሔዋን ራሷ እንደ ተናገረችው ነፍጓቸው ወይም ተመቅኝቶዋቸው ሳይኾን፡- አንደኛ) ስለ ፍቅሩ ለፈጠረው
ለእግዚአብሔር በፍቅር በመታዘዝ እንዲመልስ፤ ኹለተኛ) ፍጡርነቱን እንዲያውቅባት፤ ሦስተኛ) ነጻ ፈቃዱ እንዲገልጥባት የተሰጠችው
ናት፡፡ ቸሩ እግዚአብሔር “ትሞታለህ” ሲለው እንኳን እግዚአብሔር ስለ ጥልቅ ፍቅሩ አዳምን የመከረው እንጂ ጠበኛ አምላክ ኾኖ የተናገረው
አይደለም፤ እገድልሃለሁ አላለውምና፡፡
እዚህ ጋር መረዳት ያለብን ዕፀ በለስ በራሷ መልካም መኾኗን ነው፡፡ ፍሬዎቿም እንደዚሁ መልካም ናቸው፡፡ በውስጧ ሞትን
የተሸከመች፣ ወይም መርዝነት ያላት አይደለችም፡፡ ስለዚህ ዕፀ በለስ ልክ በዕፀ ሕይወት ላይ እንደተነጋገርነው የሕግ ምልክት ናት፡፡
በመኾኑም አዳም የሞት ሞትን የሞተው የሕግ ምልክት ኾና የተሰጠችውን ዕፅ ባለመታዘዙ ስለ በላት እንጂ ዕፀ በለስ የምትገድል ኾና
አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ አዳምን የጣለው አለመታዘዙ ነው፤ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ ግድ የለሽነቱ ነው፡፡ ይህን
ሐሳብ ስለ ሰው ልጅ ውድቀት ስንነጋገር በስፋት እንመለስበታለን፡፡
በዕፀ በለስ ውስጥ ከዕውቀት በቀር ምንም የለም፡፡ ዕውቀት ሲባል ራሱ አዳምና ሔዋን ከክብር መዋረዳቸውን
ማወቅን ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ዕፀ በለስ በጎ ዕውቀትን የምታሳውቅ ዛፍ ብትኾን ኖሮ ኃጢአት
“ኃጢአት” ሳይኾን “የዕውቀት አስተማሪ” በተባለ ነበር፤ እባብ በእርሱ አንጻርም ዲያብሎስ ባልተወቀሰ፣ “የሐሰት”
ሳይኾን “የጥበብ አማካሪም” በተባለ ነበር፡፡ ነገር ግን አይደለም፤ አዳምና ሔዋን መልካም የተባለው መታዘዝ፣ ክፉ የተባለውንም
አለመታዘዝ ከመውደቃቸው በፊት ያውቁ ነበር፡፡
ዛሬ በዕፀ በለስ ምክንያት የመጣው ሞት በዕፀ መስቀል ምክንያት ተወግዶልናል፡፡
ዕፅዋት ዕለተ ማክሰኞ ላይ የመፈጠራቸው ምክንያቱ ምንድነው?
እያንዳንዱ ፍጥረት የተፈጠረበት ቀንና ቅደም ተከተል የራሱ የኾነ ጥልቅ ምክንያት አለው፡፡ በዚህ ዕለት ማለትም ማክሰኞ
ላይ የተፈጠሩት ፍጥረታትም በዚሁ ዕለት መፈጠራቸው የራሱ የኾነ ምክንያት አላቸው፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያህልም፡-
ü ዕፅዋት የሚበቅሉት በፀሐይ ምክንያት
ብቻ ነው ብለን እንዳንደመድም ፀሐይ ከመፈጠሯ በፊት ፈጠራቸው፡፡ ይህን በማስመልከት አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አንቀጽ
ሲተረጉምልን እንዲህ ይለናል፡- “ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ቃል በተናገረ ጊዜ፥ በምድር ላይ የበቀሉ ፍጥረታት እንደምን ካለ
መኖር ወደ መኖር እንደመጡ ታስተውሉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ እነዚህ አዝርእቶች የበቀሉት ገበሬ ስለ ጣረ፣ ወይም ስላረሰ፣ ወይም
በሬዎች ስለ ተጠመዱ፣ ወይም ሌላ ፍጥረት ደክሞባቸው የበቀሉ አይደሉም - እንዲሁ ኹሉም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አዳመጡ፤ እነርሱም
ከምድሪቱ በቅለው ወደ መታየት መጡ፡፡ ዛሬም፥ የአዝርእት ምርትን የምናገኘው፥ በገበሬዎች ጥረት ወይም በሌሎች ሠራተኞች ድካም ሳይኾን፥
ከእነዚህ በፊት እግዚአብሔር ጥንቱን እንዳደረገው፥ አሁንም በቃሉ ትእዛዝ የምናገኝ እንደኾነ ከዚህ እንማራለን፡፡ ሰዎች በስንፍናቸው
ምክንያት፥ በኋላ ዘመን የሚያመጡትን ስሕተት ያቀና ዘንድ፥ ከልቡናቸው አንቅተው የሚናገሩትንና “የምድር ዘሮች የሚበቅሉት በፀሐይ
አማካኝነት ነው” ብለው ለሚነሡ ኹሉ ምክንያት ያሳጣቸው ዘንድ፥ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ስለ እያንዳንዱ ሥነ ፍጥረት አፈጣጠር በዝርዝር
ነገረን” /ትርጓሜ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ክፍለ ትምህርት 5 ቍ.12/፡፡ ሊቁ ይህንን የሚለን ፀሐይ ድርሻ የላትም ለማለት ሳይኾን የእነዚህ
ፍጥረታት መገኘት ከፀሐይ መኖር ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ብለን እንዳናስብ ነው፡፡
ü እነዚህ ዕፅዋት ለሰው ብቻ ሳይኾን ሐሙስና ዓርብ ለሚፈጠሩ ለእንስሳትም ምግብ ናቸውና ከእንስሳቱ በፊት አስቀድመው ተዘጋጁ፡፡
በዚህም የእግዚአብሔር አስደናቂ ፍቅሩ ለሰው ብቻ ሳይኾን ለእንስሳቱም ጭምር እንደ ኾነ እንማራለን፡፡ ይኸውም በኋላ ላይ፡- “የሚበቅለው
ሐመልማል ኹሉ መብል ይኹንላቸው” ባለው ይታወቃል /ዘፍ.1፥30/፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ! ርስት መንግሥተ ሰማያት ለማይወርሱ ለእንስሳቱ
እንኳን እንዲህ የሚያስብላቸው አምላክ፥ ለእኛ ደግሞ እንዴት እንደሚያስብልንና እንደሚያፈቅረን እንኳንስ በመናገር በማሰብም አንደርስበትም፡፡
እመቤታችንና ዕለተ ማክሰኞ
በዕለተ ሠሉስ ምድር ገበሬ ሳይጥርባት፣ ሳይደክምባት፣ ዘር ሳይወድቅባት በቃሉ ብቻ በእጅ የሚለቀሙ አትክልት፣ በማጭድ የሚታጨዱ
አዝርእት፣ በምሳር የሚቆረጡ ዕፅዋት ለሥጋውያን ምግብ የሚኾኑ ተገኝተዋል፡፡ ከእመቤታችንም የወንድ ዘር ሳይወድቅባት ዕፀ ሕይወት፣
ፍሬ ሕይወት (የመንፈሳዊያን ምግብ) የሚኾን ጌታ ተገኝቷልና በዕለተ ሠሉስ ትመሰላለች ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ‹‹አንቲ ውእቱ ገራህት
ዘኢተዘርአ ውስቴታ ዘርእ ወጽአ እምኔኪ ፍሬ ሕይወት›› እንዲል /ውዳሴ ማርያም ቅዱስ ኤፍሬም የደረሰው፣ ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ
15-17/፡፡
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment