Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሦስት




ዶግማ(መሠረተ እምነት)

ዶከይን ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲኾን በጥሬው አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ አዋጅ ማለት ቢኾንም በምሥጢራዊ ማለትም በቤተ ክርስቲያናዊ ትርጓሜው ግን ሃይማኖት (የእምነት መሠረት) ማለት ነው፡፡ በመኾኑም ዶግማ የተደነገገ ሳይኾን የተገለጠ ነው፡፡ መገኛውም እግዚአብሔር ነው፡፡ ከሰው ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠ እውነት ነው፡፡ በማኝኛውም አካል (በሲኖዶስም ጭምር)፣ በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ኹኔታ (በሞትም በሕይወትም) የማይለወጥ ማንነት አለው፡፡
ዶግማ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት ነው ብለናል፡፡ ስለ ቅድስት ሥላሴ፣ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ (ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መኾኑን፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና እንደተወለደ፣ እንደ ተሰቀለ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ፣ ዳግመኛ በክበበ ትስብእት እንደሚመጣ)፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ስለ ምሥጢረ ቁርባን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያንና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ክብረ ድንግል ማርያምና ክብረ ቅዱሳን የምንማው እንጂ ማናችንም ልናሻሽለው አንችልም፡፡ እንኳንስ አንድ ግለሰብ ይቅርና ሲኖዶስም ቢኾን አለመለወጡን፣ አለመፋለሱን ይመረምራል እንጂ መጨመር ወይም መቀነስ አይችልም፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ነገር ግን (ሐሳባችንን ቀይረን) እኛ ብንኾን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችኁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን የሚሰብክላችኁ የተረገመ ይኹን” ያለውም ስለዚኹ ነው /ገላ.1፡8/፡፡
፡ ስለኾነም ስለ እግዚአብሔር የምንማረው ኹሉ በጥቂት ቃላት ብቻ ታጥሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡
ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት(ዶግማ) ስንል ቤተ ክርስትያን ስለነገረ እግዚአብሔር ስለነገረ መላእክት ስለነገረ ቅዱሳን ስለሕይወት ስለሰው ያላት አስትምህሮ(ትምህርት) ብቻ አይደለም የምንኖርበት ጭምር እንጂ፡፡ በሌላ አገላለጽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ( መሠረተ እምነት) ስንል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት መግለጫ ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህም የእኛንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት በጉልህ የሚያስረዳ ነው፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) ምንጮች
† የእግዚአብሔር መገለጥ
መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት‹‹ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው በእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ በሚያስተነትኑበት በደስታ በዓል አደረጉ›› ይላል (መዝ 117÷26-27) የክርስትና መሠረትም በመዝሙሩ ላይ እንደተገለጠው የጌታ እግዚአብሔር መገለጥ ነው፡፡
እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር ግብሩን በፍጥረቱ ማወቅ ቢቻልም ግን ባሕርዩን ጠቅልለን መራዳት አይቻልም፡፡እግዚአብሔር ፈጣሪ ዓለማት ሆኖ በፈጠረው ሰው ይመረመር ዘንድ እንዴት ይቻላለዋል? ነገር ግን እግዚአብሔር በየዘመናቱ ራሱን ለሰው ልጆች ገልጦል፡፡ እግዚአብሔር በግብሩ (በሥራው) ለሁሉ ይገለጣል ከዚህ በተጨማሪ ለቅዱሳኑ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ እገዚአብሔርን 570 ጊዜ ያህል ተገልጦ አናግሮታል(ዘኁ 12÷5) ለቅዱሳኑም ለሄኖክ መዓዛ ባለው እንጨት ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል ለኖኅ በቀስተ ደመና ለያዕቆብ በመሰላል ከፍታ ላይ ለኢሳይያስ በዙፋኑ ተቀምጦ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ለዳንኤል በሽበታም ሰው አምሳል ተገልጦል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ይህንን በተመለከተ ሲናገር ‹‹ እርሱ እንደመረዳታችን መጠን ተገለጠ(አስተማረን) ስንል እርሱ ራሱ እንደኛ ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እርሱ በእኛ አምሳል ተገለጠ አልተገለጠ እርሱ ራሱ ነው አይለወጥም፡፡ ሲፈልግ እኛን ለማስተማር አንዱ ለጠባያችን ተገልጦ ይታያል ሌላ ጊዜ ደግሞ አስቀድሞ የለበሰውን እንደልብስ አውልቆ ሌላ ልብስ ለብሶ ይገለጣል እርሱ ለእኛ በመንገሩ እርሱ እንዲህ ነው ማለት አይደለም ነገር ግን ባሕርይው የማይመረመር ነውና በምንረዳው በእኛ ምሳሌ ተገልጦ ፍቃዱን ገለጠልን›› ብሏል
በኋላም በሐዲስ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተገልጦ በብሉይ በከፊል ሲገለጥ እንደነበር ሙሉ በሙሉ(በሰው አካል) ራሱን ገለጠልን፡፡ ክርስቶስ ከላይ የጠቀስነውን የቅዱስ ዳዊትን የትንቢት ቃል ፈጸመ፡፡ ለዚህም ነው ሁል ጊዜ በቅዳሴ አገልግሎታችን ቡሩክ ስሙ ለእግዚአብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር እያልን እግዚአብሔርን የምናመሰግነው መገለጡንም የምናደንቀው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሲመላለስ ሰዎች ረቡኒ ብለው ይጠሩት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረኛል ፡፡ ረቡኒ ማለት መምህር ማለት ነው፡፡ ተከታዮቹም ደቀ መዛሙርት ተሰኝተዋል ከሄደበት እየሄዱ ካደረበት እያደሩ ትምህርቱን ሲያደምጡ ስለነበር ክርስቶስ ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር እንደሆነ በመግለጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ፍቃድ በማስተማር እግዚአብሔርን መንግስት ለዓለም ገለጠ፡፡ (ዮሐ 1÷18) የክርስቶስ እንደመምህርም መገለጥ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት መሲሕ እርሱ መሆኑን ያመለክታል መሲሕ መምህር ማለት ነውና፡፡(ኢሳ 54÷13 ዮሐ 6÷45)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰው ራሱን የገለጠው መለኮታዊ መምህር ሆኖ ነው፡፡ የእርሱ ቃል የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ገልጦ አስተምሯል፡፡ ሲያስተምርም ለአይሁድ የማስተማርም ለመገሰጽም ባለስልጣን እንደሆነ ይገልጥላቸው ነበር፡፡ ‹‹እንደጸሐፍቶቻቸው ሳይሆን እንደባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበር›› (ማቴ 7÷29)
ዮሐ 12÷44-50
‹‹በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም እኔን ያየ የላከኝን አየ፡፡ በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣው፡፡ ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም እኔ ዓለምን ላላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁምና፡፡የሚክደኝን ቃሌን የማይጠብቀውን ግን የሚፈርድበት አለ እኔ የተናገርኩት ቃል እርሱ በመጨረሻይቱ ቀን ይፈርድበታል፡፡ የተናገርኩት ቃል ከእኔ አይደለምና ነገር ግን የላከኝ አብ አንድናገር እንዲም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ››
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ብቻ አላስተማርም በተግባር እያሳየ ጭምር እንጂ፡፡ እርሱንም ለሰው ልጅ በእውነት ገለጠ(ዮሐ 14÷6) እውነትና ብርሃን መሆኑን አስተማረ(ዮሐ 8÷12) ሕግንም እየፈጸመ በጥቂቱ አደገ፡፡
ዮሐ 1÷1-5
‹‹በመጀመርያ ቃል ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህም በመጀመርያ እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለእርሱ ምንም የሆነ የለም፡፡ ሕይወት በእርሱ ነበረ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ ብርሃንም በጨለማ ያበራል ጨለማም አላገኘውም፡፡››
ዮሐ 1÷14-18
‹‹ያም ቃል ሥጋ ሆነ በእኛ አደረ ለአባቱም አንድ እንደሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩንአየነ ጸጋና እውነትን የተመላ ነው፡፡››
አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውልጅን በቃል ትምህርተና በተግባሩ አርአያ ሆነው፡፡ ይህን እርሱ ያስተማረውን ወንጌል እንለዋለን የምስራች ለዓለም ሁሉ የሚሆን የእግዚአብሔር መንግስት የምስራች ነው፡፡ሐዋርያትንም የክርስቶስን የምስራች ቃል ለዓለም ሰበኩ(ማቴ 28÷19) ዓለምን ይሰብኩ ያስተምሩ ዘንድ በዓለም ይፈርዱ ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ልኮ አሰማራቸው፡፡(ዮሐ 15÷6)
በኦርቶዶክዊት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ትምህርት ጸንተን የምንኖር ናት ሐዋርያዊት መባሏም ለዚህ ነው፡፡(ሐዋ 2÷42) ይህም የሐዋርያት ትምህርት ለቅድስት ቤተ ክርስትያን ዶግማ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ መመሪያ ወይም ትምህርት ነው፡፡ ይህም የሐዋርያት ትምህርት የጌታችን የመድኃኒተችን የኢየሱስ ክርስቶሰ ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት(ዶግማ) ዓለም ሁሉ የሚድንበት ዓለም የእግዚአብሔርን መንግስት የሚወርስበት እውነተኛ ቃል ነው፡፡
ስለእግዚአብሔር መገለጥ ስናወራ በብሉይ እግዚአብሔር ሕዝቤ ብሎ የሚጠላቸው እስራኤል ዘሥጋ ራሱን ይገልጥ እንደነበር ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ በብሉይ እንደምናየው የነበረው መገለጥ በነቢያቱ ላይ እያደረ በኅድረት ተዋሕዶ በትንቢት በራዕይ በሕልም እየተገለጠ ሕዝቡን ያስተምር ነበር፡፡ ይህ የነቢያቱ ትንቢትና ምሳሌ ፍጻሜው የመሲሑ መምጣት ነው፡፡
ይህም የእግዚአብሔር መገለጥ የቅድስት ቤተ ክርሰትያን ዶግማ(መሠረተ እምነት) መሠረት ነው፡፡


† መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን መገለጥ በጽሑፍ የምናገኝበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በተለያየ ጊዜ በተነሱ ቅዱሳን አበው የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ በሁለት ኪዳኖችም የተከፈለ ነው በብሉይና በሐዲስ፡፡ ኪዳን ማለት ውል ስምምነት ማለት ነው ይህም የእውነት መጽሐፍ የሕግ የትንቢት የታሪክ የመዝሙር የጸሎት የመልእክት ክፍል ያለው ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በአምስት ክፍሎች የተከፈሉ ናቸው፡፡ የሕግ(የኦሪት) ክፍል መጻሕፍት የታሪክ ክፍል መጻሕፍት የትምህርት ክፍል መጻሕፍት የመዝሙርና የጥበብ ክፍል መጻሕፍት የትንቢት ክፍል መጻሕፍት የሐዲስም መጽሐፍት እንዲሁ የወንጌል ክፍል የታሪክ ክፍል የሥርዓት ክፍል የመልዕክት ክፍል የትንቢት ክፍል በማለት እንከፍላቸዋለን፡፡ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርቷ የሚቀዳው ከዚህ መጽሐፍ እውነት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተመሩት አበው የጻፉትም ስለሆነ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራው ቤተ ክርስቲያን ይህንን መጽሐፍ መሠረት በማድረግ ታስተምራለች፡፡ ሁላችንም ልናውቅና ልንረዳው የሚገባው እውነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚቃረን ትምህርት ጋር የሚቃረን ትምህርት አታስተምርም፡፡ የዘወትር ዝማሬዋ ቅዳሴዋ ውዳሴዋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

† ሥርዓተ አምልኮ

ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ዓይነት ሰዋስዋዊና ዘይቤአዊ ትርጕም አለው /አባ ጐርጐርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ገጽ 12-17/፡፡ የመዠመሪያው የተወሰነ ቦታን ያመለክታል፡፡ ይኸውም የክርስቲያኖች ቤት፣ መኖሪያ ማለት ነው /1ኛ ቆሮ.11፡18/፡፡ “ቤተ ክርስቲያን እንሒድ” /መዝ.121፡1/ ሲባልም ይኽን ፍቺ የያዘ ነው፡፡ በመጻሕፍትም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቤት ተብላለች /ዘፍ.18፡27፣ መዝ.5፡7፣ መዝ.26፡4፣ መዝ.83፡4፣ መዝ.92፡5፣ ሉቃ.2፡49፣ 1ኛ ጢሞ.3፡15፣ ዕብ.10፡21/፡፡ኹለተኛው ደግሞ ክርስቲያኖች ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ /1ኛ ቆሮ.3፡16፣ 1ኛ ቆሮ.6፡19/፡፡ ይኸውም በመንፈሳዊና በምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ፥ ርሱ አድሮባቸው የሚኖሩ፥ ከቅዱሱ ቅባት /1ኛ ዮሐ.2፡20/ እና ከሥጋ ወደሙ የተካፈሉ ምእመናንን ለማመልከት ነው፡፡ሦስተኛው ትርጕሙ ደግሞ የክርስቲያኖችን ኅብረት (ጉባኤን) የሚያመለክት ነው /1ኛ ጴጥ.5፡13/፡፡ እኛም በዚኹ ክፍል ት\ኵረት የምናደርገው በዚኹ በሦስተኛው ትርጓሜ ላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች በኅብረት እግዚአብሔርን ያመልካሉ ይህም ሥርዓተ አምልኮ ቤተ ክርስቲያን በሠራችው ሥርዓት የሚካሄድ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች በኅብረት የሚያከናውኖቸው ሥርዓተ አምኮዎች ቢኖሩም በዋንኝነት ቅዳሴ ቀዳሚ ነው፡፡
በብሉይ የሚከወነው ሥርዓተ አምልኮ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በመሰብሰብ የሚከወን ነው፡፡ ሥርዓተ አምልኮ በብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮው ጾም ጸሎቱ በሙሴ ሕግ መሠረት የሚከወን ነበር ይህም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወይም በተለያዩ ቦታዎች በተሠሩ ምኩራቦች ይደረግ ነበር፡፡ ምኩራቦቹ በተለያየ ቦታ የሚሰሩ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ግን አንድ እርሱም በኢየሩሳሌም የሚገኝ ነው፡፡ በሙኩራባቸው እስራኤላዊያን ለጸሎት ይሰባሰባሉ መጽሐፍትን ያጠናሉ ይሰብካሉ፡፡
በሓዲስ ኪዳን የሚካሄደው ሥርዓተ አምልኮ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ነው ስለዚህም በብሉይ የነበረው ሥርዓተ አምልኮ በጌታችን በኢየሴስ ክርስቶስ አማናዊ ሥርዓተ አምልኮ ተተክቷል፡፡ በብሉይ የሚነበቡ መጻሕፍት የሚዜሙ መዝሙራት ክርስቶስን የሚሰብኩ ነበሩ በሐዲስ ደግሞ በጉልህ የሚሰብኩ ሆነዋል፡፡ እንዲሁም የነበረው መሥዋዕት በክርስቶስ አማናዊ ሥጋና ደም ተለውጧል፡፡
የአይሁድም የጾም ሥርዓት እንዲሁ አዲስ ትርጉም አግኝቶል፡፡ የፍሲካ ጾም የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የምናስብበት የምንዘክርበትና የምናከብርበት ሆኖል፡፡ የአይሁድ ጰንጠቆስጤ በዓልም የመንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መውረድ የምንዘክርበት በዓል ሆኖል፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትና ሥርዓተ አምልኮ ቀዳሚው የክርስትና መሠረተ እምነት መሠረት ነወ፡፡ ሥርዓተ አምልኮው መጽሐፍ ቅዱስና ቅዱስ ትውፊት የተረሱ ሳይሆኑ በክርስትና የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የምናገኛቸው ያለፉ ሳይሆኑ አሁንም ያሉ የምንገለገልባቸው ናቸው፡፡ በጸሎትና በቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት አማካኝነት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር መማር ይችላል ጌታችን እንዳለ ‹‹ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ይሆናሉ››ዮሐ 6÷45 ከዚህም በተጨማሪ ሥርዓተ አምልኮን ቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎትን ምሥጢራቷን የሚያጠና ሰው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት ማወቅ ይችላል፡፡
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment