Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አስራ አምስት



                                     

የእግዚአብሔር አንድነት
እግዚአብሔር አንድ ነው ስንል አንዳንዶች ሦስትነት የሌለው እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ነገር ግን በመጻሕፍት እንደተገለጠው እግዚአብሔር አምላክ አንድ ነው ማለት ሦስትነት የለበትም ለማለት እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነው ማለታችን ተገዳዳሪ ተወዳዳሪ የሌለው ከእርሱ ሌላ ፍጹም ምድርን ፈጥሮ የሚገዛ የለም ማለታችን ነው፡፡ይህም ከምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ አለመሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ሥላሴ በባሕርይ፣ በሕልውና፣ ፣ በመፍጠር፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በመንግሥት፣ በመለኮት፣ በአምላክነት፣ እግዚአብሔር በመባል ይህንና ይህን በመሳሰሉት ነገሮች አንድ ናቸው፡፡
በእግዚአብሔርነት አንድ ናቸው
ሥላሴ በእግዚአብሔርነት አንድ ናቸው ማለታችን እንዴት ነው እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንል የለምን ቢሉ አዎን እንላለን እንዲህ ግን ስላልን አንድ እግዚአብሔር እንጂ ሦስት እግዚአብሔር አንልም፡፡ለዚህም ምሳሌ ያስረዳናል ፀሐይ ሲወጣ ክበብ ብርሃን ሙቀት ይወጣል ብርሃኑ ሲወጣ ፀሐይ ወጣ እንላለን ክበቡን ስናይ ፀሐይ ወጣ እንዲሁም ሙቀቱ ሲሞቀን ፀሐይ ወጣ እንድንል ሁሉን ፀሐይ እንላለን ነገር ግን አንድ ፀሐይ እንጂ ሦስት ፀሐይ አንልም እንዲሁ ወልድ ከአብ ቢወለድም መንፈስ ቅዱስ ከአብ ቢሰርጽም አንድ እግዚብሔር እንጂ ሦስት እግዚአብሔር አይባልም፡፡
*        ጌታ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው(ሐዋ 16፥31)
*        አባት የተባለ አብ ነው ወልድን ወልዷልና (2ኛ ጴጥ 1፥17)
*        ቸር የተባለ መንፈስ ቅዱስ ነው ለሰው ልጆች ጸጋን ይሰጣልና (1ኛ ቆሮ 12፥4)

የአንጾኪያው ሊቀጳጳስ እዱስ ባስልዮስ “እኔስ እግዚአብሔር ስል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለቴ ነው” እንዳለ፡፡
በአምላክነት አንድ ናቸው
ሥላሴ በአምላክነት አንድ ናቸው፡፡ አብ አምላክ ወልድ አምላክ መንፈስ ቅዱስ አምላክ እንል የለምን ቢሉ አዎ እንላለን እንዲህም ስላልን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አንልም፡፡ ለዚህም ምሳሌ አስረጅ ነው ከላም የተወለደውን ላም ከሰው የተወለደውን ሰው እንድንል እንዲሁ ከአምላክ የተወለደውን አምላክ እንላለን፡፡ ከአምላክ የተገኘ አምላክ እንዲል አንቀጸ ሃይማኖት(ሃይማኖተ አበው ዘአትናትዎስ 4 ቁ 4)
በመፍጠር
ስማዕ እስራኤል አሐዱ ውእቱ አምላክከ (ዘዳ.6÷4) እንዳለች ኦሪት ሥላሴ በፈጣሪነት አንድ ናቸው፡፡ አብ ፈጣሪ ወልድ ፈጣሪ መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ አንልምን ቢሉ እንላለን እንዲህ ማለታችን አንድ ፈጣሪ ስንል እንጂ ሦስት ፈጣሪ ስንል አይደለም፡፡ለዚህም ምሳሌ አለን ከንጉሥ የጠወለደ ንጉሥ ከመኮንን የተወለደ መኮንን እንዲባል እንዲሁ ከፈጣሪ የተወለደ ፈጣሪ ከፈጣሪ የሠረጸ ፈጣሪ ሊባል ይገባዋል (ዮሐ አፈወርቅ ድር. 2)
ሥላሴ የሚታየውን እና የማይታየውን ግዙፉኑንና ረቂቁን ሁሉን በመፍጠር አንድ ናቸው፡፡ (መዝ 101፥25፣ ዘፍ 1፥1)
አባቶች በአንቀጸ ሃይማኖት አንድ አምላክ በሚሆን በእግዚአብሔር አብ እናምናለን ሰማይና ምድርን የፈጠረ የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ አንድ የአብ ልጅ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ብለውናል ይህም በመፍጠር አብ ከወልድ ከአብ አንድ መሆኑን አመልካች ነው፡፡
በመለኮት
ሥላሴ በመለኮትንት አንድ ናቸው አብ መለኮት ወልድ መለኮት መንፈስ ቅዱስ መለኮት ልንል እይደለምን ቢሉ አዎን እንላለን እንዲህ ማለታችን አንድ መለኮት ማለታችን እንጂ ሦስት መለኮት ማለታችን አይደለም፡፡ ከእሳት ፍሕም ዋዕይ ነበልባል ይወጣል ዋዕዩም ነበልባሉም ፍሕሙም እሳት እንዲባል ከመሎት የወጣወውም የሰረጸውም መለኮት ሊባል ይገባዋል፡፡
በሕልውና አንድ ስለመሆኑ
ሕልውና ማለት አኗኗር ማለት ነው፡፡ ይኸውም አብ ልብ፣ ወልድ ቃል፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ናቸው፡፡ አብ ለራሱ ለወልድና መንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፣ ወልድ ለራሱ ለአብና መንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፣ መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ለአብና ወልድ እስትንፋሳቸው ነው፡፡ ሥላሴ በአብ ልብነት ያስባሉ በወልድ ቃልነት ይናገራሉ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ሕያው ሆነው ይኖራሉ፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንዱ በአንዱ ሕልዋን ሆነው ይኖራሉ (ዮሐ 1፥48-11) ይህም መገናዘብ ይባላል እንጂ የአንዱ አካል ከአንዱ ውስጥ ተከፍሎ የሚጨመር አይደለም፡፡
ባሕርይ
የሥላሴ /የእግዚአብሔር/ ባሕርይ ረቂቅ፣ በሁሉ ቦታ የሚገኝ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ነው፡፡ ሥላሴ በእነዚህ ሁሉ አንድ ናቸው (ዘጸ 3፥14፣ ዮሐ 4፥24) ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ሰው ሲወለድ ከእናት ከአባት ባሕርይ አካል ከፍሎ ይወለዳል የወለድ ልደት ግን ተከፍሎ የለበትም፡፡ ወለድ አካሉ ከአብ አካል ሳይከፈል እንበለ ዘር ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምኣካል ከአብ ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምኣካል ሠረጸ እንላለን እንጂ በሕገ ተፈጥሮ እንዳለው አይደልም፡፡አብ ወልድን ወለደው ማለት ከአካሉ ከባሕርይው አስገኘው ማለት ነው፡፡ ወልድ ከአብ ተወለደ ማለት አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡ አብ መንፈስ ቅዱስን አሠረጸው ማለት ከአካሉ ከባሕርይው አስገኘው ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ሠረጸ ማለት አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በባሕርይ አንድ ናቸው አብ ከወልድ አብ ከመንፈስ ቅዱስ ወልድ ከአብ ወልድ ከመንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ከአብ መንፈስ ቅዱስ ከወልድ የተለየ ባሕርይ የላቸውም በባሕርይ አንድ ናቸው እንጂ
በሥልጣን
ሥላሴ በስልጣን አንድ ናቸው፡፡ አይበላለጡም አብ ሥሉጥ ወልድ ሥሉጥ መንፈስ ቅዱስ ሥሉጥ እንል የለምን ቢሉ አዎን እንላለን እንዲህ ስላልን ሦስት ሥልጣን አንልም አንድ እንላለን እንጂ (ዮሐ 10፥30 ሃይ. አበው ዘመቃርዩስ 1 ቁ 3)
በመመስገን
ሥላሴ በመለኮትንት አንድ ናቸው ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ እንል እይደለምን ቢሉ አዎን እንላለን እንዲህ ማለታችን አንድ ምስጋና ለማቅረብ እንጂ ሦስት ምስጋና ማቅረባችን አይደለም፡፡
ኅብረ መልክዕ
ሥላሴ በኅብረ መልክ አንድ ናቸው ማለት እንዴት ነው ቢሉ የአብ መልክ የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን መልክ ይመስላል የወልድም መልክ የአብና የመንፈስቅዱስን ይመስላል የመንፈስ ቅዱስም መልክ የአብና የወለድን መልክ ይመስላል፡፡ አካላት እለ ዕሩያን በአርአያ ወበመልክዕ እንዲል (ሃይ አበው ኪራኮ ክ1 1ቁ 3)
በፈቃድ
እስመ በፍቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኀነነ እንዲል ውዳሴ ማርያም የአብ ፍቃድ ከወለድ ፍቃድ ከመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ የወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ የመንፈስቅዱስ ከአብ ከወልድ አንድ ነው፡፡ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፍቃድን ለያይተው የተነሱ መናፍቃን ነበሩ፡፡ እነርሱም አስቀድሞ ዲያቢሎስ ቢስት ወልድ አዳምን እንፍጠር አለ አብና መንፈስ ቅዱስ ይቅርብን አስቀድመን የፈጠርነው እንደካደ አዳም ቢክድስ አሉ፡፡ ወለድም ይፈጠር እኔ ዋስ እሆናለሁ አለ አዳም ቢስት ወልድ ዋስ ሆኖ የእሱን ሥጋ ለብሶ አዳነው ይላሉ፡፡ እንደዚህ እንዳንል ቅዱስ ኤፍሬም በአብ ፍቃድ በወልድ በራሱ ፍቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ መጥቶ አዳነን ብሎ አስተማረን፡፡
በኃይል በምሕረት በማንሳት በማዳን በብርሃን በሕይወት አንድ ናቸው
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment