Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል አስራ ሰባት




ምሥጢረ ሥጋዌ
ሥጋዌ ማለት ቃሉ የግእዝ ሲሆን‹‹ተሠገወ›› /ሰው ሆነ/ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሰው መሆን ማለት ነው፡፡ ምስጢረ ሥጋዌ ማለት ሰው የመሆን ምሥጢር ማለት ነው፡፡ ይህም ሰው የመሆን ምሥጢር ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው መሆኑን የምንማርበት ነው፡፡
ምሥጢረ ሥሥላሴ የሃይማኖታችን መሠረት ሲሆን ምሥጢረ ሥጋዌ ደግሞ የሃይማኖታችን ጉልላት ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ በመካከላችን ያልተደረገ ታላቅ ምሥጢር ስለሆነ ይረቅብናል ምሥጢረ ሥጋዌ ግን ምንም እንኳን በሰው መካከል ቢደረግ አስደናቂና ከሕሊና በላይ ነው፡፡ አባ ጊዩርጊስም ‹‹ለቀዳማዊ ልደት አመሥጠሮ ወለካልዑ ልደት አመንከሮ ቀዳማዊ ልደቱን አረቀቀው ድኀራዊ ልደቱን አስደነቀው›› ያለው
ምሥጢረ ሥጋዌ
*        በልበ አምላክ የተመከረ ምሥጢር ነው
*        እግዚአብሔር ራሱን ለፍጥረታቱ የገለጠበት መንገድ ነው
*        በአዳም ንስሐ ምክንያት የተደረገ ነው
*        በነቢያት ሲነገር የነበረ ምሥጢር ነው

የነቢያት ደጅ ጥናት
ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሮቹ ለነቢያት ካለገለጠ በስተቀር ምንም አያደርግም (አሞ 3÷7) ነቢይ ይህንን ሲል ባለቤቱ እግዚአብሔርም በውኑ እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን (ዘፍ 18÷14) ቅድመ ዓለም በልበ እግዚአብሐየር የታሰበውን በጸጋ ለአገልጋዮቹ እንደሚገልጥላቸው ያሳያል፡፡ በነቢያት በኩል እግዚአብሔር ሊያደርግ ያለውን ይገልጣል ነቢያቱም ይህንን ምሥጢር እንዲገልጥላቸው ደጅ ሲጠኑና ሲማጸኑ ነበር፡፡
ነቢያት በሦስት መንገድ ደጅ ይጠኑት ነበር
1. በትንቢት

ትንቢት ከአንድ ኩነት የሚቀድም ነው የአምላክን ሰው መሆን መላእክት ተገልጦላቸው ለነቢያት ነግረዋቸዋል ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያሉ ሕዝቡ ይዘጋጅ ዘንድ ይናገሩ ነበር፡፡ ትንቢታቸውም ሁለት ዓይነት ነው አንደኛው ደረቅ(ግልጥ) ሲሆን ሁለተኛው ስውርና ትርጉም የሚያሳ ነበር፡፡
ከደረቅ ትንቢት መካከል ለአብነት ልዑለ ቃል ኢሳይያስ መካከል ናሁ ድንግል ትጸንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ አማኑኤል ያለው ነሥአ ደዌነ ወጾረ(ኢሳ 7÷14 ኢሳ 53÷1) ያለው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ወተንሥአ እግዚአብሔር(መዝ 77÷65) ያለው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ስውር የምንለው ትርጓሜ የሚያሻው መካከል በሆሴዕ አማካኝነት ከተገለጸው ትንቢትለአብነት እንውሰድ ከሁለት ቀን በኋላ ይምራል ከሦስት ቀን በኋላ ያስነሳል በፊቱም በሕይወት እንኖራለን (ሆሴ 6÷2) ሁለት ቀን ያናል ምንማለት ነው ከሦስት ቀን ይፈውሳልስ ማለት ብሎ ካልጠየቁና ካልተረጎሙ ግልጽ አይደለምንና ሰዎች በቀላሉ አይረዱትምና ስውር አልነው፡፡
ሌላው ስውር ያልነው በምሳሌ የተገለጠውን ትንቢት ነው፡፡ ለአብነት ዳንኤል ያየው ራዕይ ለዚህ ማስረጃ ነው የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ሲጋጩ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕር ሲወጡ የመጀመርያው አውሬ የንሥር ክንፍ የነበራትና ክንፎቿ እስኪነቀሉ ትበር የነበረች አንበሳ ሁለተኛው በአንድ ወገን ቆማ ሦስት የጎድን አጥንት የምትበላ ድብ የምትመስል አውሬ ሦስተኛይቱም አራት ራሶች የነበራትና በጀርባዋ ላይ አራት የወፍ ክንፍ የኘበራት ነብር የምትመስል ሌላ አውሬ አራተኛይቱም ከእርሷ በፊት በነበሩት ሁሉ የተለየች አስፈሪ ትቢተኛ አውሬ ነበረች የሚለውን መጥቀስ ይቻላል(ዳን 7÷15-22)
ሥውር ምሳሌዎች
*        መርከብ(ዘፍ 6÷9 2ኛ ጴጥ 2÷5) ሐመርነ ዘኢይቀርቦ ሞገድ
*        ሙሴ(ዘጸ 3÷10 ሐዋ 7÷33)
*        የፍሲካው በግ(ዘጸ 12÷1-14 1ኛ ጴጥ 1÷19 1ኛቆሮ 5÷7 )
*        የኮሬቡ ዓለት(ዘጸ 17÷6 1ኛ ቆሮ 1÷4)
*        በበረሃ የወረደው መና(ዘጸ 16÷4 ዮሐ 6÷33)
*        የናሱ እባብ(ዘኁ 21÷8 ዘኁ 21÷49 ዮሐ 3÷14-15)
2. መሥዋዕታቸው

ከተነገረው ትንቢት ጋር አብረው የክርስቶስን መምጣት ከሩቅ ያሳዩ የነበሩ አራት የመሥዋዕት ዓይነቶች በአባቶቻችን ዘመን ነበሩ
*         መሥዋዕተ ኖኅ መሥዋዕቱ ከነ አቤል ከነ ሔኖክ መሥዋዕት የሚለየው ኖኅ በዚህ መሥዋዕት ምክንያት ዓለም እንደማጠፍ ቃል ተገብቶለታል
*         መሥዋዕተ መልከጼዴቅ
*        መሥዋዕተ አብርሃም
*        መሥዋዕተ ኦሪት
አምላክ ለምን ሰው ሆነ?
*        ፍጹም ካሳ ለመክፈል
በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም ኀጢያት ወደ ዓለም ገብቶ ትውልዱን ሁሉ ተቆጣጥሮ ስለነበር የሚጸለየው ጸሎት የሚሠዋው መሥዋዕት የሚያድን አልነበረም፡፡ (ኢሳ 64፥6) ብዙዎች የብሉይ ኪዳን አበው ደማቸውን አፍሰዋል፡፡ መራራ ሞትን ታግሰዋል ነገርግን የበደል ካሳ መሆን ግን አልቻሉም ምክንያቱም የበደሉ ዘር ስለነበረባቸውና የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደላቸው፡፡ ስለዚህም ፍፁም አምላክ የሆነ አምላካዊ ቃል በምድር ላይ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ ተገለጠ፡፡
የዓለምን ኀጢያት ተሸከመ (ኢሳ 53፥4) ቅድስት ሕይወቱንም መሥዋዕት አድርጎ ካሳ ከፈለልን (ኢሳ 53፥5) ቅዱስ ጳውሎስ “በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኀጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧልና” ብሎ እንደተናገረው (ዕብ 9፥26) በተጨማሪም (ዮሐ 10፥15-18) ተመልከት
*        አርአያ ለመሆን

የሰው ልጅ የሰይጣን ቃል በመስማት ሥነ ምግባር ብልሹነትን ወደ ዓለም አስገባ፡፡ በዚህም ምክንያት ስለሌላው ራሱን አሳልፎ መስጠት ሲገባው ራሱን ከተጠያቂነት ለማውጣት ሌላውን አሳልፎ መስጠት ጀመረ (ዘፍ 3፥12) ምቀኝነት ክፋት መግደል ወደ ሰው ልብ ገቡ (ዘፍ 4፥8፤13፥3፣ መዝ 61፥4) በመሆኑም ወልደ እግዚአብሔር ከምድር የጠፋውን የበጎ ምግባር ሕይወት አርአያ ሆኖ ለመመለስ ሰው ሆነ፡፡ ለአርአያነት መምጣቱንም “ከእኔ ተማሩ” በማለት ገለጸ፡፡ (ማቴ 1129) “እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት የፍቅርን ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ (ዮሐ 15፥17) ቅዱስ ጴጥሮስም “ክርስቶስም ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ መከራን ተቀብሎአል” ሲል እንደተናገረ ጌታችን አርአያ ለመሆን ሰው ሆነ፡፡ (2ኛ ጴጥ 2፥21)
*        ፍቅሩን ለመግለጥ

እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረው ያለምክንያት ስለወደደን ነው፡፡ (ሆሴ 14፥4) ይህም ከሁሉ ፍጥረት ሰውን አልቆና አክብሮ በመፍጠሩ ታውቋል፡፡ የሰው ልጅ በዲያብሎስ ፈተና ተጠልፎ የራሱን ፈቃድ ተጠቅሞ ሞት ቢፈረድበትም እራሱ ወርዶ እንደሚያድን ቃል ገባ ፈጸመውም፡፡ “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና” እያለ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እኛ አምላካችንን እንድንወደው በፍቅር ሕግ ከመታወጁ በፊት እርሱ እንደወደደን ይገልፃል፡፡ (ዮሐ 3፥16) “እግዚአብሔር አንድያ ልጁ እስኪሰጥ ድረስ አለምን ሁሉ እንዲሁ ወዱዋልና” ብሎ ጽፎልናል፡፡ በተጨማሪም (1ኛ ዮሐ 4፥19፣ ሮሜ 5፥8፣ ኤፌ 2፥4) ተመልከት
ከላይ ከጠቀስናቸው ምክንያቶችም በተጨማሪ
*         ለአዳም የገባለትን ቃል ኪዳን ለመፈጸም
*        የሰይጣንን ጥበብ ለመሻር
*        ምድር ለመልካም ተፈጥራ ሳለ በኀጢያት ረክሳ ነበርና በቅዱሳን እግሮቹ ተመላልሶ ሊባርካት (ኢሳ 45፥18፣ 3፥17)
*        ከእኛ በላይ ማንም የለም ለሚሉ ከሁሉ በላይ የሆነ አምላክ መኖሩን ለመግለጽ
*        አምላክ አካላዊ አይደለም ይሉ ነበርና አካላዊነቱን ለመግለጽ
*        እውነተኛ ሰላምና ዕርቅን ለመስጠት

ወደ ዓለም የመጣው ማነው?
ወደ ዓለም የመጣው ከሦስቱ አካላት አንዱ ወለድ ነው፡፡
ከመላእክት ወገን ቢልክስ ወይም ሌላ አዲስ ፍጥረት ፈጥሮ መላክ ሲችል አንደኛ ልጁን ወልድ ለምን ላከው ቢሉ አስቀድሞ የገባለትን ቃል ሊፈጽም ነው አስቀድሞ የገባለት ቃል ምንድር ነው ቢሉ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚለው ነው በዘፍጥረት መጽሐፍም አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ሆነ (ዘፍ3÷23) ብሎ መለኮታዊ ባሕርዩን እንደሚካፍል ተገልጦል፡፡ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ይህንን በተመለከተ ሲናገር‹‹ አሐዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ ርእዮ ትሕትናነ አጽነነ ሰማየ ሰማያት መጽዐ ወኀደረ ውስተ ከርሠ ድንግል ወኮነ ሰብእ ከማነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ ወተወልደ›› ብሏል(ውዳሴ ማር ዘሐሙስ)
አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ያልሆኑት ለምንድን ነው
አንደኛ ወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ጥንተ ግብሩ መወለድ ስለሆነ
ቤተክርስቲያን ለወለድ ሁለት ልደታት እንዳሉት ታምናለች፡፡ ይህንንም በተመለከተ አበው ‹‹ ነአምን ክልኤተ ልደታተ››(ሃይ አበው 34÷6 84÷25) ይኸውም ቀዳማዊ ልደት እና ደኀራዊ ልደት ናቸው፡፡ “ለእግዚአብሔር ልጅ ሁለት ልደታት እንዳሉት ልናምን ይገባል፡፡ መጀመሪያ ከዘመን ሁሉ በፊት ከእግዚአብሔር አብ መወለዱ ነው፡፡ ዳግመኛም በኋላ ዘመን ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው መወለዱ ነው” ሲል ሊቁ ባስሊዮስ ዘቂሳርያ አስረድቷል፡፡ አንዱ በመንፈስ አንዱ በሥጋ የተከወነ ሲሆን ቀዳማዊ ልደቱ በድኀራዊ ልደቱ እንደተገለጠ አበው ያስተምራሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በድኀራዊ ልደት›› እንዳለ፡፡
የወልደ እግዚአብሔር ሁለት ልደታት
*        ቀዳማዊ ልደት

ቀዳማዊ ልደት የሚባለው ዘመን ከመቆጠሩ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ ከሰው አእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢር የተወለደው ልደት ነው፡፡ ከዓለም በፊት ወልድ ከአብ መወለዱን መጽሕፍት ያስረዳሉ፡፡“አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድኩህ ….” (መዝ 2፥7) “ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድ ወለድሁ” (መዝ 109፥3) “ተራሮች ገና ሳይመሰረቱ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ” (ምሳ 8፥25)
*        ደኀራዊ ልደት

ይህ ልደት ጌታችን ዓለም ከተፈጠረ አዳም ከበደለ ከአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው፡፡ “ጊዜው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከው ከሴትም ተወለደ” እንደተባለ (ገላ 4፥4) ይህንንም ልደት ጌታ አስቀድሞ በነቢያት ሲናገር ነበር፡፡ “ስለዚህም ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣቸኋል፡፡ ድንግል ትጸንሳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ 7፥14) “ሕጻን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡፡ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ 9፥6) በተጨማሪም(ዘፍ 3፥15 ፤ 18፥13 ፤ 12፥8 ፣ መዝ 106፥20) ተመልከት
ቅድመ ዓለም ከባሕርይ አባቱ ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስና ስጋን ነስቶ ያለ አባት የተወለደውን የጌታችንን ልደት ሐዋርያው ጳውሎስ “ታላቅ ምሥጢር” ይለዋል (1ኛ ጢሞ 3÷16) ምክንያቱም ሊመረመር የማይችል ፍጹም ምሥጢር ነውና፡፡
ሁለተኛ የከዊን ግብሩን ለመግለጥ ነው
የአብ ከዊን ልብነት የመንፈስ ቅዱስ ከዊን እስትንፋስ እንደሆነ ሁሉ የወልድም ከዊን ስሙ ቃል ነው፡፡ከልብ ተገኝቶ ከአንደበት ወጥቶ ሩቅ ሄዶ ሥራ የሚሰራ ቃል እንጂ እስትንፋስና ልብ አይደሉም፡፡ ወልድም ረድኤተ እግዚአብሔር ሩቅ ወደ ነበረች ዓለም መጥቶ ዓለምን አድኖ መልሶ አርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ቃል ይህንን ሲሰራ ከልብ ወጥቶ ተለይቶ ከእስትንፋስ ተለይቶ አይደለም ከልብ ይነቃል በእስትንፋስ ሠረገላነት ወደ ውጭ ይወጣል ከልብ አይታጣም ከእስትንፈስ አይለይም ማለት ነው፡፡ወልድም ሰው የሆነው ባለመለየት ነው፡፡ ለእመቤታችን መልአኩ ሲያበስራት መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ብሏታል የአብን ሱታፌ ቅዱስ ኤፍሬም ሲናገር ፈነወ ለነ መዝራእቶ ልዑለ ብሏል(ውዳ ማር ዘሰኑይ) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ሰው መሆኑን አበው ከአባቱ ዕሪና ሳይለይ በማኅጸነ ድንግል ተወሰነ ከእርሷም ተወለደ ብለዋል(ሃይ አበ ም48÷2)
ሦስተኛ በልበ እግዚአብሔር የተሰወረውን ነገር ለሰው እንዲገለጥ ነው
ረቂቁ ነገር ከልብ ተለይቶ በልብ ሕልው ሆኖ ልግለጥ ባለ ጊዜ የሚገልጠው በቃል አማካኝነት ነው የሥላሴ ረቂቅ የሆነውን አንድነት ሦስትነት ምሥጢር በእግዚአብሔር ባሕርይ ተሰውሮ ሲኖር የተገለጠው በአካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ስለዚህም የተሰወረውን ይገልጥ ዘንድ በከዊን ግብሩ ስሙ ቃል የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፡፡ እንዘ ሥውር እምኔነ ይእዜሰ ክሡተ ኮነ እንዲል ቅዱስ ያሬድ እስመ በፍቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኀነነ እንዲል ውዳሴ ማርያም የአብ ፍቃድ ከወለድ ፍቃድ ከመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ የወልድ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ የመንፈስቅዱስ ከአብ ከወልድ አንድ ነው፡፡ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፍቃድን ለያይተው የተነሱ መናፍቃን ነበሩ፡፡ እነርሱም አስቀድሞ ዲያቢሎስ ቢስት ወልድ አዳምን እንፍጠር አለ አብና መንፈስ ቅዱስ ይቅርብን አስቀድመን የፈጠርነው እንደካደ አዳም ቢክድስ አሉ፡፡ ወለድም ይፈጠር እኔ ዋስ እሆናለሁ አለ አዳም ቢስት ወልድ ዋስ ሆኖ የእሱን ሥጋ ለብሶ አዳነው ይላሉ፡፡ እንደዚህ እንዳንል ቅዱስ ኤፍሬም በአብ ፍቃድ በወልድ በራሱ ፍቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፍቃድ መጥቶ አዳነን ብሎ አስተማረን፡፡
ሰው የሆነው መንገድ
በብስራተ መላክ
ጌታ ሥጋዌውን ድንገት አላደረገውም ድንገትስ አድርጎት ቢሆን እመቤታችን የመጽነስን የመውለድን ነገር አታውቅምና ምን አገኘኝ ብላ በተጨነቀች ነበር ስለዚህም ጊዜው ሲደርስ ቅዱስ ገብርኤልን ላከ፡፡ ለምን ገብርኤልን ላከው ሌሎች መላእክት አልነበሩምን ቢሉ ቅዱስ ሚካኤል መጋቤ ብሉይ ነውና ቅዱስ ገብርኤልን መጋቤ ሐዲስ አድርጌ ሾምኩህ ሲለው ነው፡፡ አንድም ቅዱስ ገብርኤል ባለውለታው ነው አስቀድሞ በዓለመ መላእክት ከይሲ ዲያቢሎስ ስክድ መላእክትን በያለንበት ጸንተን እንቆይ አምላካችንን እስኪገለጥ ድረስ ብሎ መላእክቱን አረጋግቶልና ከዚህያ ጊዜ ጀምሮ መላከ ብስራት ሆኖል(መጽሐፈ አክስማሮስ) አንድም ጥንቱን አብሳሬ ጽነስ ነው የማኑሄን ሚስት ያበሰራት ካህኑ ዘካርያስን ያበሰረው እርሱ ነውና
ያበሰራትም በዕለተ እሑድ ሦስት ሰዓት ቦታውም በቤተ ዮሴፍ ነው፡፡ ቤተ ዮሴፍ ነገሩን ሰምታ ይህስ መላከ ብስራት ሳይሆን አዳምና ሔዋንን ያሳተ ቢሆንስ ብላ ቸል አለችው ዳግመኛ ውሃ ስትቀዳ አበሰራት ይህስ ተደገመ እንሆ መላከ ብስራት ከሆነ በቤተ መቅደስ ተገኝተው ሊሰሙት ይገባል ብላ ወደ ቤተ መቅደስ ገባች በዛም መልአኩ ተገልጦ አበሰራት፡፡በሥውር
ይህ የተዋሕዶ ምሥጢር በሥውር የሆነ ነው፡፡ አስቀድሞ ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ በሥውር በእባብ ገላ ገብቶ አዳምና ሔዋንነን እንዳሳተ እንዲሁ ጌታ በሥውር ገብቶ ያሳተን ዲያቢሎስን ድል ለመንሳት በሥውር በአዳም ገላ ተገልጦ ድል አድርጎታል፡፡
በሥውር ያደረገበት ምክንያት
1. ጽንሱን ከአጋንንት ለመሠወር
2. ድል መንሳቱ እንዲደነቅ(በደካማ ባሕርይ ተገልጦ ዲያቢሎስን ድል ለማድረግ)

ይቆየን ይቀጥላል
                                                                                                                                      ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment