Saturday, 15 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ስምንት





የእግዚአብሔር ባሕርያት

የምዕራብያኑ ካቶሊካዊያን እግዚአብሔርን ለመመርመርና በጥልቀት ለማወቅ ምንም ወሰን የለውም የሚለውን ትምህርት በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እግዚአብሔር ራሱን እስከሚያውቀው መጠን ድረስ ማወቅ እንችላለን በሚል ትምህርት የተጀመረ ነው፡፡ ይህ የምሥራቃዊያን አባቶች(ኦርቶዶክሳዊያን) አጥብቀው የሚቃወሙት ነው፡፡ እንዲህም እያሉ ያስተምራሉ እግዚአብሔርን ከግብሩ(ከሥራው) የተነሳ እናውቀዋለን እንጂ ባሕርይውን መረዳት አንችልም፡፡ እግዚአብሔር እራሱን በገለጠው መጠን ብንረዳም ባሕርያቱን ግን ጠቅልለን አንረዳም፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ቸር ነው እንላለን ይህም ከግብሩ አንጻር ሰዎች የተረዱት ሐቅ ነው ግን የቸርነቱን መጠን መስፈር(ጠቅልሎ መረዳት) የሚቻላቸው እናዳልሆነ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡
ምዕራባዊያኑ ቶማስ አኩናስ እንደሚለው እግዚአብሔርን ጠቅልለን መረዳት እንችላለን ይላሉ፡፡ ይህ የምዕራባዊያን ሊቅ መንፈሳዊነት(ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት) ካለን እግዚአብሔርን ማወቅ እንችላለን የሚለውን የአባቶቻችንን ትምህርት አይቀበለም ይልቁንም ሳይንሳዊ ሎጆኮችን ልፍፎችን በመጠቀም የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መኖር ይረዳል ብሎ ያስተምራል፡፡(ለምሳሌ የማያምን ሰው የእግዚአብሔርን መኖር እንዴት እንደሚረዳ አምስት ማረጋገጫዎችን አስቀምጦ ነበር)
እንደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የምንናገረው ከገለጠልን ውስጥ ጥቂቱን ነው፡፡ ይህ የሚሆነንበት የእኛ ሕሊና መሸከም የማይችለው ባሕርይ ስላለው ብቻ ሳይሆን ሰው መረዳት የቻለውን እንኳን የሚገልጽበት ቋንቋ ስለሌለው ነው፡፡ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ ወዳጆች ሆይ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም፡፡ ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለን ገና አልተገለጠም፡፡ ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን›› (1ኛ ዮሐ 3÷2) በማለት እንኳንስ የእግዚአብሔር ባሕርይ ይቅርና ለሰው የተዘጋጀው ክብርም ከዕለተ ምጽአት በፊት ከገናንነቱ የተነሳ የተገለጠ እንዳይደለ ገልጦልናል፡፡
የምሥራቅ ኦርቶዶክሳዊያን አባቶቻችን ስለእግዚአብሔር መርምረን መድረስ እንደማንችል ያስተምራሉ፡፡ ፍጡር ፈጣሪውን ይመረምር ዘንድ አቅም ስለዚህም ስለእግዚአብሔር ለመረዳት መጀመርያ እግዚአብሔርን መምሰል ይገባል ከእርሱም ጋር በሕይወት መኖር ሕብረት መፍጠር ያሸል ይላሉ፡፡ ስለእግዚአብሔር መርምረን ስለማንጨርስ ትርፉ ልፋት ነው ነገር ግን እርሱን ከመሰልን ራሱ ምሥጢር ይገልጣል ይላሉ ልቡናን ንጹሕ በማድረግ ነቢያት እግዚአብሔርን አይተውታል ፊት ለፊትም ተያይተዋልና እንዲል
እንደምሳሌ ብንጠቅስ ቅዳሴ ማርያምን ማንሳት ይቻላል፡፡ ቅዱስ ሕርያቆስ በዚህ ቅዳሴ ላይ እንዳስቀመጠው ጠለቅ ያለ ነገረ መለኮታዊ ጥያቄዎች ከጠየቀ በኋላ በአንዲት ዓረፍተ ነገር ይዘጋዋል ‹‹አቅቶት ወደ ቀደመ አኗኗሩ ይመለሳል›› ስለዚህም መጨረሻው ድምዳሜው እግዚአብሔርን መመርመር ማቆም ይደርሳል ብለው አስተምረዋል፡፡ሦስቱ አባቶች በተለይ(ባስልዮስ ዘቂሳርያ ጎርጎርዩስ ዘኑሲስና ጎርጎርዩስ ዘእንዚናዙ) በተለይ እግዚአብሔርን የሚመረመር የሚታወቅ የሚነገርለት በግብሩ የማይታወቅ የማይደረስበት የማይመረመር የማይነገርለት መሆኑን በሚገባ አስቀምጠውታል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በፈቀደ መጠን በቅዱሳን አባቶቻችን በኩል እንዲሁም በመጽሐፍት ከገለጡልን የእግዚአብሔር ባሕርይ ምን እንደሆነ እንገልጻለን፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ነው (ዮሐ4፥24)

መንፈስ ነው ስንል ሊታይ ሊዳሰስ ሊለካ ሊወሰን አይችልም ማለታችን ነው፡፡ ነፋስ እንኳ ወጀብና ማዕበል ሲያስነሳ ዛፍ ሲያንቀሳቅስ እንዳለ እናውቃለን እንጂ አናየውም (ዮሐ 3፥8) ነፋሳትን የፈጠረ አምላክ ምን ያክል ረቂቅ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ከነፋስ ነፍስ ትረቃለች፣ ከነፍስ መላእክት ይረቃሉ፣ ከመላእክት እግዚአብሔር ይረቃል፡፡
ሁለት ዓይነት መንፈስ አለ አንደኛው ዝርው መንፈስ የምንለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አካላዊ መንፈስ ነው፡፡ እግዚአብሔር አካላዊ መንፈስ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ ሰማያት የእጅህ ሥራ ናቸው፡፡(መዝ 101÷25) ወደ ማደሪዎችህ እንገባለን እግርህ በቆመበትም እንሰግዳለን(መዝ 131÷7) በሌላም የመጽሐፍ ክፍል ‹‹ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር›› (ዘፍ 1÷26) በማለቱ አካልና መልክ ያለው መሆኑን ገልጾል፡፡መጽሐፍ እንደሚነግረን እግዚአብሔር አካላዊ መንፈስ ነው አካላዊ መንፈስ ነው ማለታችን ግን እንደኛ ቁስ አካላዊ መልክ አለው ማለታችን አይደለም ፡፡ ዝርው መንፈስ (አካል የሌለው) እንዳልሆነ ግን ልናስተውል ይገባል፡፡(ኢሳ 40÷18)
አፍርንጅ የተባለ መናፍቅ ለሥላሴ መልክ የለውም (እግዚአብሔር ዝርው መንፈስ ነው አካል የለውም) ብሎ ተነስቶ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃኑ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ነው የሚለውን ጠቀሱበት ይህስ ስላዩ ዓይኖች አላቸው የሥላሴን መልክ አያስረዳም አለ ንግበር ሰብአ ብሎ ሰውን በመልኩና በአርአያው መልክ መፍጠሩን ታምናለህን አሉት አዎን አምናለሁ አላቸው ታዲያስ መልኩን ከወዴት አመጣው ትላለህ አሉት በዚህም እረተውታል፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ነው ስንል
*      ምልዓቱ
*      ርቀቱ
*      የማይመረመር ስውር መሆኑ
*      ራሱን የሚገልጥ ክሱት መሆኑ
*      በአካላት መደበላለቅ በመለኮት መለያየት የሌለበት መሆኑ
*      እንደ እግዚአብሔርነቱ ሊገለጥ የማይችል መሆኑ(እንደአቅማችን በቋንቋችን ልክ እንጂ)
ቅዱስ ነው (ዘፀ 15፥11፣ ዘሌ11፥44፣ ሉቃ 1፥48-49፣ ራዕ 4፥8)

ቅዱስ ልዩ ማለት ሲሆን ለእግዚአብሔር ሲቀጸል ፍጹም ልዩ የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ፍጹም ቅዱስ ነው ማለታችን ስለሁለት ነገር ነው አንድ እግዚአብሔር ከሕጸጽ የነጻ በመሆኑና ከክፍትና ከርኩሰት የተለየ መሆኑ ሁለተኛው ሌሎችን ጭምር የሚቀድሳቸው እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህም ነው አቤቱ በቅድስና የከበረ እንደአንተ ያለ ማነው? ተብሎ የማይነጻጸር ቅድስናው የተመሰከረለት፡፡
እግዚአብሔር በባሕርይው ቅዱስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቅድስና ግን በጸጋ እግዚአብሔር የተገገኘ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የሆነ የለም እርሱ ቅዱስ ሆኖ ሌሎችም ቅዱስ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ (ዘፀ 15፥11፣ ዘሌ11፥44፣ ሉቃ 1፥48-49፣ ራዕ 4፥8)
ዘለዓለማዊ ነው

እግዚአብሔር በዚህ ዘመን አለ በዚህ ዘመን የለም አይባልም፡፡ የነበረ ያለና የሚኖር ነው፡፡ ለባሕርይው ሞት ለመንግስቱ ሽረት የሌለበት ዘላለማዊ ነው፡፡(መዝ 912፣ መዝ 14013፣ ራዕ 18)
ሁሉን ቻይ ነው

ሁሉን ማድረግ የሚቻለው፣ የሚሳነው ነገር የሌለ፣ ለሚሰራው ሥራ ሁሉ እረዳት የማያስፈልገው ነው፡፡ (ዘፍ 18፥14፣ መዝ 134፥6፣ ኤር 32፥17) ሁሉን ቻይነቱ በመጻሕፍት ተገልጦ እናነባለን ለአብነትም
አብርሃምና ሣራ በእርጅና መውለዳቸው (ዘፍ. 17÷)
የዘካርያስና የኤልሳቤጥ (ሉቃ 1÷8-)
የማኑሄና የሚስቱ በእርጅና መውለዳቸው(መሳ13)
ድንቁ የተዋሕዶ ምሥጢር ያለወንድ ዘር በድንግልና መወለዱ
እስራኤል በተአምራት ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ እስራኤለን አሻግሮ ፈርኦንን ማስጠሙ
በሁሉ ቦታ ያለ ነው
አምላካችን በሁሉ ቦታ የሚገገኝ ነው፡፡ እርሱ የሌለበት ቦታ የለም፡፡ ወደሰማይም ብንወጣ ወደ ምድርም ብንወርድ እርሱ የሌለበት ቦታ የለም፡፡(ዮና 1-2፣ ኤር 23፥23)
ቸር ደግ ነው

እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ መልካም ነግርን ያደርጋል ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ የሰውፊት ሳያይ ሳያዳላ ኅጥእ ጻድቅ ሳይል ለሁሉም በቸርነት ይሠራል፡፡ ኅጢአትን ስንሰራ ይታገሰናል፡፡ (መዝ 1447-9፣ ማቴ 540-45 መዝ 325፣ መዝ 3019፣ ጢሞ24)
ሁሉን አዋቂ ነው

የእግዚአብሔር ጥበብ ይህን ያክላል ይህን ይመስላል የሚባል ነው፡፡ ከእርሱ የተሰወረ የለም ያለውንም የሚመጣውንም የሚያውቅ ጥበበኛ ነው፡፡( ዳን 220-21፣ ሮሜ 11332ኛቆሮ 26፣ ኢሳ 4610)
በመለኮትቱ ጠባቂ ነው

እግዚአብሔር ይህን ዓለም በመለኮታዊ ስልጣኑ እየመገበ እያስተዳደረና እየታደገ የዘላለም ጥባቆቱን ይገልፃል፡፡ በእርሱ ፈቃድ ካልሆነ በቀር የሚደርስ አንዳች ነገር የለም፡፡(ማቴ 10፥30፣ ሐዋ 10፥11፣ መዝ 22፥1-2)
ፍቅር ነው

እግዚአብሔር ሁሉን ያለ አድሎ የሚወድ አምላክ ነው፡፡ ስለወደደን ፈጠረን ስለወደደን ሞተልን፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ወደንና ፈቅደን እንድንገዛለት ይፈልጋል እንጂ አስጨንቆ አይገዛም፡፡ (1ኛዮሐ4፥16፣ ኤፌ 2፥4-5፣ ሮሜ2፥4)
እውነተኛ ፈራጅ ነው

እግዚአብሔር ፍርድ የማያዛባ አምላክ ነው፡፡ ጻድቁን በጽድቅ ሲያድን ኅጥኡን በኅጢያቱ ያጠፋዋል፡፡ በዕለተ ምጽአት ለሁላችን እንደ ስራችን የሚከፍል እውነተኛ ፈራጅ ነው፡፡ (መዝ 36፥28፣ 1ኛጴጥ 2፥4፣ ዮሐ 8፥16)

ጻድቅ ነው (1ኛ ሳሙ 2÷2 2ኛ ጢሞ 4÷8 ራዕ 16÷7)
ሁሉን አዋቂ ነው (መዝ 24÷10 ኤፌ 4÷6 ኤር 17÷10 ኤር 23÷24 ዕብ 4÷13)
ጥበበኛ ነው (መዝ 103÷24 ሮሜ 11÷33 ኤር 17÷10 ምሳ 2÷6 ዳን 2÷21)
ቸር መሐርይ ይቅር ባይ (መዝ 102÷8 ሮሜ 2÷4 ዮና 4÷2 ሰቆ ኤር 2÷22)
ፈታሒ በጽድቅ ኰናኔ በርትዕ (ኢሳ 9÷1-5 ኢሳ 60÷10)
እውነት ነው (ዮሐ 3÷33 መዝ 25÷10 ዘፍ 23÷19)
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment