ቅዱስ ቁርባን በሐዲስ ኪዳን
የምሥጢረ ቁርባን አመሠራረት
ምሥጢረ ቁርባን የመሠረተው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህንን ምሥጢር በሁለት መንገድ መሥርቶታል፡፡
1. በትምህርት(ዮሐ 6÷54) ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ብሎ በማስተማር
2. በተግባር (ማቴ 26÷26'1ኛ ቆሮ 11÷23-26) በዕለተ ኃሙስ ማታ በአልዓዛር ቤት መጋቢት 26 ቀን ሕብስቱንና ወይኑን አክብሮ ለውጦ ሕብስቱን ሥጋ መለኮት ወይኑን ደመ መለኮት አድርጎ ለቅዱሳን ሐዋርያት በመስጠት ምሥጢረ ቁርባንን በተግባር መሥርቶታል፡፡ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራ አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ኃጢአት የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡ (ማር 26÷26)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ምሥጢረ ቁርባንን በተግባር በአልዓዛር ቤት የመሰረተው የፋካውን እራት ከበሉ በኋላ ነው፡፡ የፋሲካውን እራት በልተው ከዚያ ሥጋ ወደሙን መቀበላቸው በልተው ቆረቡ አያሰኝምን; አያሰኝም፡፡ ምክንያቱም፡-
ከዚያ በፊት ሥርዓት አልተሠራምና
ሐዋርያት ሕፃናተ አእምሮ ናቸውና፡፡ ሕፃናት ሲበሉና ሲጠጡ አድረው ይጠመቃሉ ይቆርባሉ ሥርዓት አፋለሱ አይባልም
በተአምራቱ ከሆዳቸው ያለውን አጥፍቶላቸዋልና
ጌታ ለምን አብሯቸው ተቀበለ;
ሥርዓትን ለሐዋርያት ለማሳየት ነው
በኋላ ዘመን የሚነሡ ካህናት ተቀብለው ማቀበል እንደሚገባቸው ሥርዓት ሲሰራ
ሐዋርያት ይህንን ሲያዩ የመጀመሪያቸው ስለሆነ ከአእምሮአቸው በላይ ሆኖ እንዳይከብዳቸው እንዳይጨንቃቸው ለማደፋፈር እንጂ ኃጢአት ኖሮበት ሥርየት ለማግኘት የተቀበለ አይደለም፡፡
ምሥጢረ ቁርባን በመብልና በመጠጥ ለምን ሆነ
ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ቁርባንን በወርቅ በብር ወይም በሚለበስ ወይም ደግሞ በሌላ ነገር ሳይሆን በመብልና በመጠጥ ብቻ ያደረገበት ምክንያት አለው ይኸውም
ዲያብሎስ በእባብ ሥጋ አድሮ በመብል የሰውን ልጅ እንዳሳሳተ ሁሉ ጌታም የአዳም ልጆች የሚድኑበት ቁርባን በሚበላ እና በሚጠጣ አደረገው
መብል መጠጥ ከመላው ሰውነታችን እንደሚዋሐድ ሥጋዬን ደሜን ብትቀበሉ ከሰውነታችሁ ተዋሕጄ አብሬያችሁ እኖራለሁ ሲል ነው፡፡
በሕይወት ለመኖር ዕለት ዕለት ምግብ መጠጥ እንደሚያስፈልግ ሁሉ እኛም ለነፍስ መብል መጠጥ ሆኖ የተሰጠንን የጌታን ሥጋና ደም በየጊዜው መቀበል እንደሚገባ ለማስገንዘብ
መብል መጠጥ ያፋቅራል እናንተም ሥጋዬን ደሜን ብትቀበሉ ፍቅርን ታገኛላችሁ ሲል ምስጢረ ቁርባን ጌታ በመብል እና በመጠጥ መሠረተው
ስንዴ እና ወይን ለምን ተመረጡ
የተነገረ ትንቢት የተመሰለ ምሳሌ ስላለ
U ትንቢቱ፡- (መዝ 4÷6) ‹‹አቤቱ የፊትህን ብርሃን በላያችን ታወቀ በልቤ ደስታን ጨመርህ በስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይት ይልቅ በዛ›› (መዝ 103÷14) ‹‹ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል ዘይትም ፊትን ያበራል እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል›› ተብሎ ተነግሯልና፡፡
U ስንዴ ባለሙያ ሴት ያዘጋጀው እንደሆነ ስብን ወይን ደግሞ ደምን ይመስላል በሚመስል ነገር ለመስጠት
U ጌታ እና እመቤታችን በዚህ ምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ ይመገቡት የነበረው ስንዴ ይጠጡት የነበረው ወይን ነበርና
U ስንዴ በሽተኛ የበላው እንደሆነ በሽታው ይቀሰቀስበታል ለጤናማው ሰው ግን ኃይል ይሆናል እንደዚሁ ሁሉ ተዘጋጅተው ለሚቀበሉት መድኃኒተ ሥጋ ወነፍስ ይሆናል በድፍረት በኃጢአት ሳሉ የሚቀበሉትን ግን መቅሰፍት ዕዳ በደል ይሆንባቸዋልና፡፡
U ስንዴ እና ወይን የጌታ ምሳሌ ናቸውና (ዮሐ 12÷24' ዮሐ 15÷1)
U ጥቂት ወይን ለሆድ ሕመምተኞች ፈውስ ይሆናልና(1ኛ ጢሞ 5÷23) ፈውስም በሥጋና ደሙ ነውና፡፡
ምሳሌው፡- አብርሃም ወደ መልከጼዴቅ በሄደ ጊዜ መልከጼዴቅ ሕብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከት ይዞ ተቀብሎታልና (ዘፍ 14÷17) ስለዚህ ምሳሌው በተመሰለበት ነገር ይሰጠን ዘንድ ሥጋውን በስንዴ ደሙን በወይን አደረገው፡፡
ሊቆርብ የሚገባው ማን ነው
በክርስቶስ የባሕሪይ አምላክነት ያመነ ዕድሜ ሳይወስነው ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተማረ ምግባር ከሃይማኖት ያጣመረ ማንኛውም ክርስቲያን የጌታን ሥጋና ደም መቀበል እንደሚገባው ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡
ከቅዱስ ቁርባን የሚገኙ ፀጋዎች
ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ይሰጠናል፡፡ (ዮሐ 6÷57) ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ››
የኃጢአት ሥርየት ይሰጣል (ማር 26-28) ‹‹ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢያት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው››
የጋብቻን አንድነት ያረጋግጣል፡፡ ‹‹እንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየውም›› (ማቴ 19÷4)
የዘላለም ሕይወት ይሰጣል፡፡ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው ›› (ዮሐ 6÷1)
የክርስቲያኖች ሕብረት ይሰጣል፡፡ (1ኛ ቆሮ 10÷14) ‹‹የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ጋር ሕብረት ያለው አይደለምን; የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን; አንድ እንጀራ ስለሆነ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና›› እንዲል ለዚህ ነው በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ ‹‹አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር በይቅርታ አንድ ያደርገን ዘንድ ሰላምን እንማልዳለን›› እያለ የሚጸልየው፡፡
ምስጢረ ቁርባን የሚያሰጠው ተጨማሪ ፀጋዎች
ፍሬ ማፍራት ይሰጣል
መከራ መስቀሉን እንድናስተውል ያደርጋል
የእግዚአብሔር ፍቅርን እንድናስተውል ያደርጋል
መንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት ይሰጣል
ድል አድራጊነት እናገኛለን
አእምሮን ያነፃል ምሥጢርን ይገልጣል
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment