ተሠግዎተ ቃል
ነገረ ልደቱ ማቴዎስ እንደጻፈው
ማቴ 2÷1-2 ‹‹ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እንሆ ሰብአ ሰገል ‹የተወለደው የአይሁድ
ንጉስ ወዴት ነው? ኮከቡን በምስራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናል› እያሉ ከምስራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ››
የይሁዳ ቤተልሔም ማናት? (ለምን ቤተልሔምን አነሣት?) ቢሉ
ከታች (በቁጥር 5፡6 ላይ) ‹‹ወአንቲኒ ቤተልሔም›› ‹‹አንቺ ቤተልሔም…›› ብሎ የሚያመጣት ስለሆነ ከዚህ ላይ አንሥቷታል፡፡
አንድም፡- የጌታችን የትውልድ ቦታ የይሁዳ ቤተልሔም ናት ሌላ ቤተልሔም አለችና ከዚያ ሲለይ የይሁዳ ቤተልሔም ብሎ ጠቅሷታል፡፡
ሌላዋ ቤተልሔም የዛብሎን ቤተልሔም ተብላ የምትጠራ ነች፡፡ ይህችም ለዛብሎንና ለወገኖቹ ርስትነት የተሰጠች ነበረች (ኢያ
9÷15) የይሁዳ ቤተልሔም ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ የምትገኝ ከተማ ከተማ ናት
አንድም፡- ትንቢቱን ምሳሌውን ይፈጽም ዘንድ
ትንቢቱ ምንድን ነው? ቢሉ (ሚክ5÷2) ፣(ማቴ 2÷5)
ምሳሌውስ እንደምነው ቢሉ፡-
ታሪክ፡- ካሌብ ምድረ ርስትን ሰልሎ ሲመለስ (ከዚህ ቀደም ኢያሪኮን እንደሰለሉ) ‹‹ኬብሮንን›› ዓይቶ ለኢያሱ ‹‹ኬብሮንን
ስጠኝ ቀድሞ ሙሴ አሰጥሃለሁ ብሎኝ ነበር፡፡ ከ12 ነገድ አንዱ እኔ ነበርኩ፤ ያን ጊዜ 40 ዘመን ሆኖኝ ነበር ዛሬም 80 ዘመን
ይሆነኛል ከአንተ ጋር መውጣት መውረድ ይቻለኛል ጉልበት አለኝና ስጠኝ›› አለው፡፡ ኢያሱም በእስራኤል ምስክር ፊት ኬብሮንን ለካሌብ
ሰጠው፡፡ ካሌብም ኬብሮንን እጅ አድርጎ ‹‹አዙባ›. የምትባል ሚስት አገባ፡፡ አዙባ ከጠላቶቹ ወገን ነበረችና ኬብሮንን በእርሷ
ስም አላስጠራትም፡፡ ቀጥሎም ‹‹ከብታ›› የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ስም ‹‹ከብታ›› ተብላለች፤ ከብታ ማለት ቤተ ስብሐት
(ቤት የእመቤታችን፣ስብሐት የጌታ ምሳሌ) ማለት ነው፡፡ ከዚያም ‹‹ኤፍራታ›› የምትባል ሴት ሲያገባ በኤፍራታ ‹‹ኤፍራታ›› ተብላለች፤ኤፍራታ
ማለት ደግሞ ፀዋሪተ ፍሬ (ፀዋሪት የእመቤታችን፣ፍሬ የጌታ ምሳሌ) ማለት ነው፡፡ ከብታ ከኤፍራታ ወንድ ልጅ ወለደ፡፡ በዚያን ወራት
እጅግ ጥጋብ ሆኖ ስለነበር የልጁን ስም ‹‹ልሔም›› ብሎ ሰየመው ልሔም ማለት ኅብስት ማለት ነው፡፡ በልሔም ቤተ ልሔም ተባለች፡፡
(ቤት የእመቤታችን ልሔም የጌታ ምሳሌ) ኬብሮን 3 ስሞች አሏት ማለት ነው፡፡
ሄሮድስን ለምን አነሣው ቢሉ
ከታች (በቁጥር 17-18) ‹‹ሕጻናቱን ይገድሉ ዘንድ አዘዘ›› ብሎ ያመጣዋልና ነው
አንድም፡- ዘመን የሚቆጠር በንጉሥ ነውና
አንድም፡- ሄሮድስ የነገሠው በተንኮል ነበርና በሄሮድስ ላይ ሰማያዊ ንጉሥ መወለዱን ለማጠየቅ
ታሪክ፡- እስክንድር የሚባል ንጉሥ እስክንድርያ የምትባል ሴት አግብቶ አትሮብሎስን ሕርቃሎስን ማርያን
ይወልዳል፡፡ ንጉሡ በሚሞትበት ጊዜ ለሚስቱ ‹‹ታናሹን አንግሠሽ ታላቁን ካህን አድርገሽ ኑሪ›› ይላታል አድልቶ አይደለም ታናሽየው
ሕርቃሎስ ብልህና ሰው ማስተዳደር የሚያውቅ ስለነበር እንጂ፡፡ እንደነገራት አድርጋ ስትኖር ‹‹ሄሮድስ ወልደ ሐንደፌር›› የሚባል
ንጉሥ የእስራኤልን መንግሥት በጣም ይመኘው ነበርና ለታላቅየው ለአትሮብሎስ መልዕክት ይልክበታል፡፡ ‹‹ታላቅ ሳለህ ታናሽ አዋቂ
ሳለህ አላዋቂአድርገውህ በአንተ ላይ ታናሽህን ያነገሡብህ ለምድን ነው?›› ጦር አንሶህ እደሆን ከእኔ ወስደህ
ገድለህ ንገሥ ይለዋል አትሮብሎስም እውነት መስሎት ወንድሙን ገድሎ ነገሠ፡፡
ሟች ሕርቃሎስ አርሰጥአሎስ የሚባል ልጅ ነበረውና ለበቀል የአጎቱን የአትሮብሎስን ጆሮ ቆረጠው፡፡ እስራኤል አካሉ የጎደለ
አያነግሡም ነበርና አርስጥአሎስን ሳያነግሡት ቀሩ መንግሥትም በመካከል ቀረች፡፡ ይሄኔ ሄሮድስ እህታቸው ማርያን አግብቶ ነገሠ፡፡
እርሱ በተንኮል በጥበብ የነገሥኩ ቢመስለው ‹‹መንግስት ከቤተ ይሁዳ አይወጣም›› የተባለው ይፈጸም ዘንድ በንጉሥ ሄሮድስ ላይ ሰማያዊ
ንጉሥ ክርስቶስ ተወለደ ለማለት ሄሮድስን አነሣው፡፡
ሰብአሠገል እነማን ናቸው?
ሰብአሠገል፡- ማለት የጥበብ ሰዎች ማለት ነው
‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?››
ምነው ኮከቡ ይመራቸው አልነበረምን? መጠየቅ ለምን አስፈለጋቸው ቢሉ፡-
ከሰው ሲደርሱ ይሰውራቸው ነበርና
ስለምን ‹‹ንጉሥ›› አሉ ከፍ ብለው ‹‹አምላክ›› ዝቅ ብለው ‹‹ሕጻን›› ለምን አላሉም ቢሉ፡-
‹‹ንጉሥ›› የሚለው ስም ማዕከላዊ ነውና እሱን ገለጸላቸው
ስም ላዕላዊ - አምላክ ማለት ነው
ስም ማዕከላዊ - ንጉሥ ማለት ነው
ስም ታህታዊ - ሕጻን ማለት ነው
‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ›› ከማለት ‹‹የአይሁድ አምላክ፤ የአይሁድ ፈጣሪ›› ብለው ጠይቀው ቢሆን ‹‹እኒህ ሞኞች፣ተላሎች
ሰማይና ምድር የማይችሉትን ማን ችሎ ተወለደ? ባሏቸው ነበርና፡፡
ስሞ ታህታዊ ተገልጾላቸው ‹‹የተወለደው የአይሁድ ሕጻን›› ብለው ጠይቀው ቢሆን ‹‹እኔህ ሞኞች ተላሎች በእስራኤል ከተማ
እልፍ ተወልዶ፤ እልፍ ሞቶ ያድራል ስንቱን እናውቅላቸዋለን›› ባሏቸው ነበር፡፡
ሰብአሰገል እጅ መንሻ ይዘው ከምስራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡አመጣጣቸውስ እንደምን ነው? ቢሉ፡-
ታሪክ፡- መላእክት ሦስቱን ንዋያት (ወርቅ፣ እጣን፣ከርቤ) ለአዳም ሰጡት፡፡ አዳም ለሔዋን እያለ ከትውልድ ወደ ትውልድ
እየተላለፈ ከሰብአ ሰገል አባት ከዠረደሼት ደረሰ፡፡ ዝርደሸት ፈላስፋ ነበር ከውኃ ምንጭ አጠገብ ሆኖ ሲፈላሰፍ ድንግል በሰሌዳ
ኮከብ ተሰላ ሕጻን ታቅፋ አየና ፈጥሮ በሰሌዳ ብርት ቀርጾ አስቀመጠው፡፡ ዠረደሸት የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ልጆች (ሰብአ ሰገልን)
ጠርቶ ‹‹ እንዲህ ያለ (የሚመሰል) ኮከብ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ስጡት ብሎቸው ነበርና ያን የመሰለ ኮከብ
ስላዩ መጥተዋል፡፡
‹‹ኮከቡን››ሲል
በተፈጥሮ ገንዘቡ የሚሆን ሲል ነው አንድም፡- አምሳያው የሚሆነው ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናል ሲሉ ነው፡፡
ሰብአሰገልን ሲመራቸው የነበረው በቁሙ ኮከብ ነውን ወይስ መልአክ?
ሁለት ትርጓሜ አለው
መልአክ ነበር ይህ በምን ይታወቃል ቢሉ?
ኮከብ በሌሊት እንጂ በቀን (በመዓልት) አይታይም
አንድም፡- ኮከብ መጥቶ ይሄዳል እንጂ ቆሞ (ዘቅዝቆ) በቆመ ብእሲ አይሄድምና፡፡
አንድም፡- ኮከብ ነው፡፡ በሌሊት የሚታየውን በቀን (በመዓልት) እንዲታይ ወደ ቁልቁል የሚሄደውን (የሚወርደውን) ወደ ላይ
እንዲወጣ መጥቶ የሚሄደውን በሰው ቁመት እንዲሄድ የሚያደርግ እርሱ ነውና በቁሙ ኮከብ ነው፡፡
ለምን በኮከብ መራቸው? ቢሉኮከብ ያመልኩ ነበርና በሚያውቁት ለመሳብ (በለመዱት
ለመሳብ)
ለሰብአ ሰገል እንዲገለጽላቸው ያደረገው ለምንድን ነው ቢሉ?
አባታቸው ነግሯቸው ነበርና ይሹት፤ ለፍቅሩም ይሳሱ ነበርና
አንድም፡- ክህደት ጸንቶባቸው ነበርና ጌታ ክህደት ወደ ጸናበት ቦታ መሄድ ልማዱ ነውና፤በመዋዕለ ስደቱ ክህደት ወደ ጸናችባቸው
ወደ ግብጽ እንደሄደ
አንድም፡- በእስራኤል ዘለፋ ለአህዛብ ተስፋ ለመሆን
‹‹እኛ እንኳን አውቀን ስንመጣ እስከ አሁን ሳያውቁት›› እንዲሉ
አንድም፡- ነገሥተ ፋርስ ለጸብ እንጂ ለፍቅር አይመጡም ነበርና በጌታ ልደት ፍቅር እንደተጀመረ ለማጠየቅ
አንድም፡- የራሱን (የአባቱን) ገንዘብ ለመቀበል
ማቴ 2÷3 ‹‹ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ ኢየሩሳሌምም ከእርሱ ጋር››
ሄሮድስና ሕዝቡ (ኢየሩሳሌም) መደንገጣቸው ስለምን ነው?
ሄሮድስ፡- የተወለደው ንጉሥ ከሆነ እኔን ሳይገድል ይነግሣልን? ብሎ ነው
ሕዝቡ (ኢየሩሳሌም)፡- ሕዝቡ የደነገጡት ደግሞ ጦርነት ጸንቶባቸው ነበርና ነው
አንድም፡-ሰብአ ሰገል 3ቱ ነገሥታት ናቸው ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ነገሥታት
(ስማቸውም፡- ማንቲሱሁር፣ በዲዳስፋና ሜልኩ ይባላሉ) እልፍ
ሠራዊት አስከትለው መጥተው ነበርና በዚህ ምክንያት ሄሮድስና
ሕዝቡ ደነገጡ፡፡
ተአምረ ኢየሱስ 3 ናቸው፡ሲል ትርጓሜ ወንጌል 12 ይላል አይጣላምን? ቢሉ አይጣላም፡- ከሀገራቸው 12 ሆነው ተነሥተው
ፈለገ ኤፍራጥስ ሲደርሱ 9ኙ ተመልሰዋል፡፡
በምን ምክንያት ተመለሱ? ቢባል
ወደ ኋላ ጦር ተነሣባቸሁብለዋቸው ‹‹ፍርሻቡር›› በሚባል አዛዥ ተመልሰዋል
አንድም፡- ስንቅ አልቆባቸው
አንድም፡- ኢየሩሳሌም ጠባብ ናት ለሰፈር አትበቃም ብለዋቸው
ምስጢሩ ግን፡- ከበረከቱ ልደቱ እንዳላሳተፋቸው ያጠይቃል፡፡
ማቴ 2÷4፡- ‹‹የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንደሚወለድ ጠየቃቸው››
ሊቀ ካህናቱ አንድ አይደለምን? ለምን የካህናት አለቆች አለ ቢሉ?28
አንዱ ሹም ሌሎቹም የሹም ሽር ሆነው ተሹመው ነበርና
ጸሕፍት የሚላቸው እነማንን ነው? ቢሉ
ከ12ቱ ነገደ እስራኤል ተውጣጥተው ‹‹ርስት ከርስት፤ነገድ ከነገድ፤ ትውልድ ከትውልድ እንዳይፋለስ የሚጽፉ፤ በተለይም
‹‹ክህነት ከቤተ ሌዊ፣ መንግሥት ከቤተ ይሁዳ እንዳይወጣ የሚጽፉ ናቸው፡፡
ስለዚህ ሄሮድስ ከሹም ሽር ሊቃነ ካህናት ከጻሐፍት ወግ አይታጣም ብሎ ሰበሰባቸው፡፡
ማቴ 2÷5-6 ‹‹እነርሱም ‹አንቺ ቤተልሔም የይሁዳ ምድር ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም ሕዝቤን
እስራኤል የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና› ተብሎ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት፡፡››ትንቢቱን የተናገረው
ሚኪያስ ነው (ሚኪ 5÷2)
ታሪክ፡- ነቢዩ ሚኪያስ ሌላውን ሲያስተምር ውሎ ወደ ማታ በቤተ ልሔም በኩል ሲያልፍ ቤተ ልሔም ተፈታ፤ ምድረ በዳ ሆና፤
ቋያ በቅሎባት አየ፡፡ ‹‹እንዲህ ሆነሽ አትቀሪም ንጉሥ ይነግሥብሻል፤ የነጋሪት ድምጽ ይሰማብሻል፤ድንኳን ይተከልብሻል፤እስራኤል
ደጅ ይጠኑብሻል፤አሕዛብ ይገብሩብሻል›› ብሎ ትንቢት ተናግሯል፡፡
ነቢዩ የተናገረው ያልቀረም፡- ዘሩባቤል ነግሦባታል፤ እስራኤል ደጅ ጠንተውበታል፤ የነጋሪት ድምጽ ተሰምቶባታል፤ አሕዛብ
ገብረውባታል፤ ድንኳን ተተክሎባታል ፡፡
አንድም፡- ወገኖቼ እስራኤል ዘነፍስን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ
ይወለዳልና
ዘሩባቤል እንደነገሠ - ጌታ ተወልዶባታልና
ድንኳን እንደተተከለ - የብርሃን ድንኳን ተተክሎባታል
ነጋሪት እንደተሰማባት - ቅዳሴ መላእክት ተሰምቶባታል
እስራኤል ደጅ እንደጠኑባት - 99 ነገደ መላዕክት ደጅ ጠንተውባታል
አሕዛብ እንደገበሩባት - ሰብአ ሰገል ገብረውባታልና
አንድም፡- አንቺ የኤፍራታ ልጅ እመቤታችን በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት
ብትበልጭ እንጂ አታንሺም፤ ወገኖቼ እስራኤል ዘነፍስን
የሚጠብቃቸው ንጉሥ ክርስቶስ ባንቺ ባህርይ ከአንቺ ይወለዳል፡፡
ማቴ 2÷7፡-‹‹ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ጠይቆ ተረዳ››
ለምን በስውር ጠራቸው ቢሉ
ካህናት ‹‹አሁን ከእኛ ጠይቆ ይነግራቸዋልን? እንዳይሉት
አንድም፡- ውዳሴ ከንቱ ሽቶ ‹‹ሰብአሰገል እኛ እንኳን አውቀን ስንመጣ እሱ ከዚህ ሆኖ እስከ ዛሬ ሳይሰማ ኖሯል?›› ይሉኛል
ብሎ
ጠይቆ ተረዳ ያለው ምኑን ነው? ቢሉ
‹‹ይህን ኮከብ ካያችሁ ምን ያህል ዘመን ሆኗል? አላቸው ‹‹ሁለት ዓመት ሆኖታል›› አሉት፡፡ እሱም ‹‹ለካ ያም ብላቴና
ሁለት ዓመት ሆኖታል›› ብሎ ተረዳ ፡፡
ማቴ 2÷8፡- ‹‹ወደ ቤተልሔምም እነርሱን ሰደደ ፤ ‹ሂዱ ስለ ሕጻኑ በጥንቃቄ መርምሩ ባገኛችሁት ጊዜም
እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ› አላቸው››
‹‹መጥቼ እንድሰግድለት›› ማለቱ
የምጸት አነጋገር ነው
አንድም ፡-እሰግድለት ዘንድ አለ እገድለው ዘንድ ማለቱ ነው
አንድም፡- ‹‹እኛ ብቻ መስሎን ለካ የሀገሩም ሰዎች የሀገሩም ነገሥታት ያምኑበታል›› ብለው ሰብአ
ሰገል እምነታቸው እንዲጸናላቸው መንፈስ ቅዱስ አፉን ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ ሲያናግረው ነው፡፡ሄሮድስ ከሰብአ
ሰገል ጋር ሄዶ አይገድለውምን ሰብአ ሰገልን ለምን ላካቸው ቢሉ?፡-
ካህናቱ ዘመዶቹ ናቸውና ቀድመው ልከው ያሸሹብኛል ብሎ ነው፡፡
አንድም፡- ሰብአ ሰገል ይገላግሉኛል ብሎ አይሆንም ያልኳቸው እንደሆነ እልፍ
አእላፍ ሠራዊት አስከትለው መጥተዋልና ይጣሉኛል ብሎ ፈርቶ
ማቴ 2÷9፡- ‹‹እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፡፡ እነሆም በምስራቅ ያዩት ኮከብ ሕጻኑ ካለበት ቦታ ላይ እስኪቆም ድረስ
ይመራቸው ነበር››
ኮከቡ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት በሰው ቁመት ተዘቅዝቆ ቆመ፡፡
ማቴ 2÷10፡- ‹‹ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው››
ከሰው ሲደርሱ ይሰውራቸው፡ ከሰው ሲለዩ ይመራቸው ነበርና አሁን በከተማው በሰው መካከል ቢገለጽላቸው ፈጽሞ ደስ አላቸው፡፡
አንድም፡- አንኳን 2 ዓመታት የሄዱለት ነገር 2 ሰዓት የሄዱበት ነገር ሲፈጸም
ደስ ያሰኛልና ደስ አላቸው፡፡
አንድም፡- እንዲሁ መርቶ ከምን ያደርሰን ይሆን? ከባህር ይጥለን፣ከገደል
ይጥለን? ብለው ነበርና ካሰቡት ቢያደርሳቸው ፈጽሞ ደስ አላቸው፡፡
ማቴ 2÷11፡- ‹‹ወደ ቤትም ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፡ወድቀውም ሰገዱለት፡፡ ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው
እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት››
‹‹ወደ ቤትም ገብተው››
ማቴዎስ፡- ቤት፣ በዓት ይላል፡ ሉቃስ ጎል (ግርግም) ይላል አይጣላምን? ቢሉ አይጣላም፡-
ቤት፡- ቢል ዮሴፍ እንደ ዳስ አድርጎ ጥሎ ነበርና
በዓት፡- ቢል ኢዮሲያስ በጨው ግንብ አሰርቶ ነበርና፤ ጨውን ሲልሱ እንስሳት እየጋጡ አጎድጉደውት ነበርና
ጎል፡- ያለ እንደሆነ የተመቸ ነው የእንስሳት ማደርያ ሆኖ ነበርና፡፡
‹‹ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት››
ኮከቡን አይተው አምሳያው ሆኖ አገኙት ደስም አላቸው፡፡
‹‹ወድቀውም ሰገዱለት››
ከፈረስ ከሰረገላ ወርደው ሰገዱለት
አንድም፡- መልሰው መላልሰው ሰገዱለት
ሐተታ፡-እንደ ጥንት ነገሥታት ወግ፡- ንጉሥ ጋር ሲደርስ ይሰግዳል፡ የታዘዘ ብላቴና መጥቶ ተነሥ ብለውሃል ይለዋል፡፡ ዳግም
እልፍ ብሎ ይሰግዳል፡፡ አሁንም ተነሥ ብለውሃል ይለዋል፡፡ እንዲህ እያለ ከንጉሥ ሲደርስ እጅ ነሥቶ በቀኝ አብሮ ይቀመጥ ነበርና
በዚያ ልማድ ‹‹ወድቀው ሰገዱለት›› አለ
‹‹ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት››‹‹ወርቅ አመጡለት››
ይህን የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ
ሲሉ
‹‹ዕጣን አመጡለት››
ይህን የምናጥናቸው ጣኦታት ቀድም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ
‹‹ከርቤ አመጡለት››
ምንም ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ብትሆንም በመስቀል ጊዜ በሰውነትህ መራራ ሞትን መቀበል አለብህ (ትቀበላለህ)
ሲሉ
አንድም፡- ወርቅ ጽሩይ ነው፡- ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ፣ ዕጣን ምዑዝ ነው፡- ምዑዘ ባሕርይ ነህ ሲሉ፣ ከርቤ የተሰበረውን
ይጠግናል፡ የተለያየውን አንድ ያደርጋል፡- አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለያየ አዳምን አንድ ታደርገዋህ፡፡ ጽንዓ ነፍስን ሰጥተህ
ታጸናዋለህ ሲሉ
አንድም፡- ወርቅ ጽሩይ ነው፡- ባንተ ያመኑ ምእመናን ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ፣ ዕጣን ምዑዝ ነው ፡- ባንተ
ያመኑ ምእመናን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ፣ ከርቤ በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና
አንድም፡- ወርቅ፡- የሰማዕታት ምሳሌ ነው ‹‹ከመ ወርቅ ፈተኖሙ ለሰማዕት›› እንዲል በእሳት ይፈተናሉና ዕጣን፡-የባሕታውያን፡
‹‹ዕጣን ከሩቅ እንደሚሸት ባሕታውያንም በተስፋ ይኖራሉና›› ከርቤ፡- የምእመናን ‹‹ምእመናን በፍቅር አንድ ይሆናሉና››
አንድም፡- ወርቅ፡- የሃይማኖት ምሳሌ ነው፡፡ ወርቅ ጽሩይነቱም ግብዝነቱም የሚታወቅ በእሳት ሲፈተን ነው፡ የሃይማኖትም
ጥንካሬና ድክመቱ የሚታወቀው መከራ ሲቀበሉበት ነው፡፡ዕጣን፡- የተስፋ ምሳሌ ነው ዕጣን ከሩቅ እንዲሸት ተስፋም ያልያዙትን እንደያዙት
ያላዩትን እንዲያዩት ታደርጋለችና፡፡ ከርቤ፡-የፍቅር ምሳሌ ነው፡፡ ከርቤ የተሰበረውን እንደሚጠግን የተለያየውን አንድ እንደሚያደርግ
ፍቅርም አንድ ታደርጋለች ሃይማኖት፡ ፍቅር ፡ ተስፋ ያንተ ገንዘብ ናቸው፡ ሲሉ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ገብሩለት፡፡
ማቴ 2÷12 ‹‹ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ››
‹‹በሌላ መንገድ ወደ ሃገራቸው መሄዳቸው ስለምንድን ነበር ቢሉ››
ሄሮድስ ከነገ ከሠለስት ይመጣሉ ሲል እመቤታችን መንገድ እንድትገፋ
አንድም፡- ሃይማኖት እንዲሰፋ ነው፡፡ በመጡበት የተመለሱ እንደሆነ ሃይማኖት ይጸናል እንጂ አይሰፋም ባልመጡበት ቢመለሱ
ግን ያልሰማው እየሰማ ሃይማኖት ይሰፋል፡፡
አንድም፡- መንገድ እንዲቀርባቸው ፡፡ በሌላ መንገድ ሁለት ዓመት የመጡትን በ40 ቀናት ገብተዋልና
አንድም፡- በሌላ መንገድ(ጎዳና) ማለቱ በሌላ ኃይለ ቃል ሲል ነው፡፡ ‹‹አይቴ ሃሎ››፡‹‹ወደየት አለ?›› እያሉ መጥተው
ነበርና ‹ረከብናሁ አገኘነው›› እያሉ ተመልሰዋና
አንድም፡- በሌላ ሃይማኖት ሲል ነው ‹‹ንጉሥ›› እያሉ መጥተው ‹‹አምላክ›› እያሉ ተመልሰዋልና
ማቴ 2÷13፤- ‹‹እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሄሮድስ ሕጻኑን ሊገድው ይፈልገዋልና
ተነሳ፣ ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፣ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው››
መልአኩ ለዮሴፍ ሰብአ ሰገል ከሄዱ በኋላ የነገረው፤ እያሉ ያልነገራቸው ለምንድን ነው? ቢሉሰብአሰገል
ሳሉ ነግሮት ቢሆን ሲሰደድ አይተው አምክነቱን በተጠራጠሩ ነበርና፡፡
አንድም፡- መሰደዱስ ካልቀረ ይዘነው እንሂድ ባሉ ነበርና ይዘውትም እንዳይሄዱ የጌታ ስደት ወደ ግብጽ እንጂ ወደ ሌላ
(ባቢሎን) አይደለምና፡፡
‹‹ሕጻኑንና እናቱን ይዘህ ….››
‹‹ሕጻኑን›› ብሎ ‹‹እናቱን›› ቢተው ህጻኑን አለኝ እንጂ እናቱን አለኝን? ባለ ነበር
‹‹እናቱን›› ብሎ ‹‹ሕጻኑን›› ባይል እናቱን አለኝ እንጂ ብላቴናውን አለኝን? ባለ ነበርና
‹‹ሕጻኑን እና እናቱን›› አለው
አንድም፡- መልአክ መሆኑን ለማጠየቅ
ሰይጣን ቢሆን አመላክቶ ይተዋል ለመልአክ ግን አካቶ መናገር ልማድ ነውና መልአክ መሆኑን ለማጠየቅ ‹‹ህጻኑንና እናቱን››
አለ፡፡
ማቴ 2÷14-15፡- ‹‹እርሱም ተነሥቶ ሕጻኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ ልጄን ከግብጽ ጠራሁት የተባው
እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስም እስኪሞት በዚያ ኖረ፡፡››
ኮብላይ ለልማዱ መንገዱ ሌሊት ነውና በሌሊት ሄደ ሲል ነው፡፡ መልአኩ እንደነገረው ወዲያውኑ ሳይውል ሳያድር በሌሊት ሄደ
ሲል ነው፡፡
‹‹ከጌታ ዘንድ በነቢይ›› ማለቱ
እግዚአብሔር በነቢይ አድሮ ሲል ነው
አንድም፡- ነቢይ ከእግዚአብሔር ተገልጾለት
በነቢዩ ቃል ‹‹እስራኤል ህጻን በነበረ ጊዜ ወደድሁት ልጅንም ከግብጽ ጠራሁት›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ
(ሆሴ 11÷1)
ትንቢቱማ ከግብጽ መውጣቱን እንጂ መውረዱን (መሰደዱን) አያመለክትም ቢሉ፡- ካልወረዱ መውጣት የለምና እንዲህ አለ
ስደቱን ወደ ግብጽ ያደረገው ስለምንድን ነው? ቢሉ ትንቢቱን ምሳሌውን ሊፈጽም
ትንቢት፡- ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ወስተ ምድረ ግብጽ እንዘ ይጼዓን ዲበ ደመና ቀሊል›› ‹‹እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና
እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል›› ኢሳ 19÷1 ይህማ የተነገረው ለያዕቆብ አይደለምን ቢሉ? ለጊዜው ለያዕቆብ ቢሆንም ፍጻሜው ግን
ለጌታ ነው፡፡
አንድም፡- ዘፍ 15÷13 ‹‹…ዘርህ ለእነርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ፡፡ ባርዎችም አድርገው
400 ዓመታት ያስጨንቋቸዋል፡፡›› ብሎ ለአብርሃም ነግሮት ነበርና ጌታም የአብርሃም ዘር ነውና ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡
ፍጻሜው እንደምን ነው ቢሉ? ግብጽ ታቀርበዋችና ፡ ይሹታልና ለፍቅሩ ይሳሳሉና
አንድም፡- በግብጽ ክህደት ጸንቶ ነበርና ወደ ጸናበት መሄድ ልማድ ነውና
ከስር በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ደዌ ወደ ጸናባቸው ወደ ጌርጌሴኖን ሄደ›› ብሎ እንደሚያመጣው
አንድም፡- ገዳማተ ግብጽን ለመባረክ
በግብጽ እነ ገዳመ ሲሐት፣ እነ ገዳመ አስቄጥስ፣ አሉና እኒህን ለመባረክ
አንድም፡- ኪዳነ መልከጼዴቅን ለመፈጸም ‹‹ዘመዶቼን ማርልኝ›› ቢለው
‹‹ልጄን በሥጋ ሰድጄ እምርልሃለው›› ብሎት ነበርና
አንድም፡- ሃይማኖት ከሁሉ ሲጠፋ በግብጽ አይጠፋምና እስከምጽአት ድረስ ወልድ ዋሕድ ስትል ትኖራለችና
መሰደዱ ስለምን ነው ቢሉ?
እንዳይሞት
ጊዜው አልደረሰምና
ከቤተልሔም ሆኖ ድኖ ቢሆን ኖሮ ‹‹ይህማ ምትሐት ነው ባሉ ነበርና››
አንድም፡- አዳምን እንደካሰ ለማጠየቅ
አዳም ከዚህ ዓለም አፍአ ከምትሆን ከገነት ተሰዶ ነበርና ለዚያ እንደ ካሰ ለማስረዳት
አንድም፡- ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ
ሰማዕትነት በእሳት፣ በስለት ብቻ አይደለም እንደነ ገ/ክርስቶስ አገር ጥሎ መሰደድም ሰማዕትነት ነውና
አንድም፡- አጋንንትን ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለመስደድ
ከዚህ ሲደርሱ የጌታን ስደት መተረክ ይገባል (ራዕ 12÷1-17) ፣ ቅዳሴ ማርያም ገጽ 235፡- ‹‹አዝክሪ ድንግል ንግደቶ
ዘምስሌኪ እንዘ ትጎይዪ ምስሌሁ እምሀገር ለሃገር በመዋእለ ሄሮድስ ርጉም›› እንዳለ
ማቴ 2÷16፡- ‹‹ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአሰገል እንደተሳለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልክ ከሰብአ ሰገል እንደተረዳው
ዘመን በቤተልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕጻናትን ሁሉ አስገደለ››
ይቆየን ይቀጥላል
ስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment