Monday, 24 July 2017

ነገረ ሃይማኖት ክፍል ሃያ ሦስት


ጥምቀተ ክርስቲያን

በቤተ ክርስቲያናችን ሁለት የጥምቀት ዘመናት አሉ
  •   የሕጻናትጥምቀት
  •  የንዑሰ ክርስቲያን ጥምቀት

የሕጻናት ጥምቀት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለምሥጢረ ጥምቀት ብርቱ ጥንቃቄ ታደርጋለች፡፡ ሰው ሁሉ በጥምቀት የሚሰጠውን ጸጋ እንዲያገኙ ጥረት ታደርጋለች፡፡ ሰዎች ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ በማለት ሕፃናት እንዲጠመቁ ታስተምራለች ታጠምቃለችም፡፡ ሕፃናትን የምታጠምቀው በቅዱሳን አበው ትዉፊትና ሥርዓት በቅዱሳን መጽሐፍት ትምህርት መሠረት ነው፡፡ የሕፃናት ጥምቀት ክርስትና ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ነው፡፡
የፕሮቴስታንቱ ዓለም ክፍሎች በማርቆስ ወንጌል የሚገኘውን ክፍለ ንባብ በቁሙ በመተርጎም ‹‹ ያመነ የተጠቀ ይድናል›› የሚለውን ቃል በመጥቀስ ከመጠመቅ በፊት ማመን መቅደም አለበት በማለት ሕጻናት መጠመቅ የለባቸውም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ትምህርታቸውን ብንጠቀልለው ይህንን ይመስላል፡፡
U የሕጻናት ጥምቀት በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አልተቀመጠም
Uየእምነት ጥምቀት(ካመኑ በኋላ ማጥመቅ) ይገባል
U ከሌሎች እምነቶች የመጡና ዳግመኛ ‹‹እውነተኛ›› ጥምቀት የተጠመቁ የእምነቱ የተቀበሉ አዲስ ሰዎች ሆነዋል የሚል ነው
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሕጻናትን የምታጥቅበት ምክንያት ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡
1. መጀመርያው ነጥብ ማር.1616 ላይ የተገለጸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ምንን መሠረት አድርጎ የተነገረ ነው የሚለው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ከሕጻናት ጥምቀት ጋር ምንም አያገናኘውም፡፡ ጌታችን ይህንን የተናገረው ስያስተምር ለነበረው ሕዝብ ነው እነዚህ ደግሞ ጥምቀት ሳይፈጽሙ የሕጻንነት ዘመናቸው ያለፈባቸው ሰዎች እንደሆኑ ከመጽሐፉ ዓውደ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ይሀ ጥቅስ ከሕጻናት ጥምቀት ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡
2. ጌታችንም ‹‹ሕጻናትን ወደ እኔ እንዲመጡ ተዉ አትከልክሏቸው የእግዚአብሔር መንግስት እንደነዚህ ላሉት ናትና›› (ማር. 1014) የሕጻናት ጥምቀትን የሚደግፉ መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስረጂ ታደርጋለች፡፡
3. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስን ‹‹ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከመንፈስና ከውሃ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም››(ዮሐ 35) ይህ ማለት ማንኛውም ሰው በጥምቀት ዳግመኛ በመወለድ ወደ እግዚአብሔር ለመግባት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡
4. በበዓለ ኃምሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲሰብክ ይህንን ብሎ ነበር ‹‹የተስፋው ቃል ለእናንተና ልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ የሚጠራቸው በሩቅ ላሉሁሉ ነውና አላቸው›› ሐዋ 239) በዚህም ምዕራፍ ላይ በተመሳሳይ ልጆቻቸውም ጭምር ወደ መዳን እንዲቀርቡ ማጥመቅ እንዲገባ ያስተምራቸዋል፡፡ ለዚህም ምስክራችን ‹‹ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ››የሚለው የመጽሐፍ ቃል ነው(ሐዋ. 240)
5. የጥምቀት ምሳሌ የሆነው ግዝረት በእስራኤላዊያን ልማድ በልጅነት ስለሚደረግ ‹‹በስምንተኛው ቀን ልጅ አስገርዝ›› (ዘፍ.1712) ይህም ሥርዓት ከሕጻናት ጥምቀት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የእስራኤላዊያን ሥርዓት ነው፡፡ማንኛውም ወንድ ልጅ በተወለደ 8ተኛው ቀን እንዲገረዝ ታዟል፡፡ትልልቅ ሰዎችም በልጅነታቸው ካልተገረዙ ካደጉ በኋላ ይገረዙ ነበር፡፡ አብርሃም 99 ዓመቱ እስማኤል 13 ዓመቱ ይስሐቅ ደግሞ 8ተኛው ቀን ተገርዘዋል፡፡ (ዘፍ 17÷-9-27 ' ዘፍ 21÷1-5) በሐዲስ ኪዳን ግዝረት የጥምቀት ምሣሌ ነው፡፡ (ቆላ 2÷11-12) በኦሪቱ ሕፃናቱም አዋቂዎችም ተገርዘው ለአብርሃም የሰጠውን ተስፋ እንደወረሱ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትም አዋቂዎችንም በማጥመቅ እንደ ተስፋ ቃሉ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወረሱ ታደርጋለች፡፡
6. ኖኅና ቤተሰቡ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ ሆነው በመርከብ ውስጥ ገብተው ከጥፋት ውሃ ድነዋል፡፡ ኖኀ ከጥፋት የዳነባት መርከብ የጥምቀት ምሳሌ እንሆነች ተጽፏል (1 ጢሞ 3÷20-22) ኖኀ ከእነቤተሰቡ ወደ መርከብ ውስጥ እንደገባ ዛሬም በኖኅ አንጻር የሚገኙ ወላጆች ቤተሰባቸውን በሙሉ ሕፃናትንም ሳይቀር ማስጠመቅ እንዳለባቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ኖኀ ሦስቱ ልጆቹ ሕፃናት ቢሆኑ ኖሮ መርከብ እንዳይገቡ ያግዳቸው ነበርን; ልጆቹስ ሕፃናት ልጆች ቢኖራቸው ሕፃን ስለሆኑ በመርከብ ውጪ ይተውአቸው ነበርን; እግዚአብሔር በሃይማኖት ያላወቁና ያላመኑ ለድኅነት የተዘጋጀውን መርከብ ዓይተው ያልተረዱ በራሳቸው ፈቃድ መወሰን የማይችሉ ሕፃናት ቢኖሩ አድገው የፈጣሪን መኖር አውቀው ወደ መርከቡ በራሳቸው ፈቃድ ለመግባት እስኪወስኑ ከመርከብ ውጪ የሚተዋቸው ወላጅ ይኖርን; ለዚህ ነው እግዚአብሔር ኖኅን ከእነቤተሰቡ ወደ መርከብ ግባ ያለው፡፡ ማንም እንዳይጠፋ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ነውና በዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን እያጠመቀች ከጥፋት እንዲድኑ የዘላለም ሕይወት እንዲወርሱ ታደርጋለች፡፡
7. እግዚአብሔር ሕፃናትን ከፀጋው አያርቃቸው ከእናታቸውም ማኅፀን ሳሉ ይቀድሳቸው ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ያሳድርባቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡(ኤር 1÷4-5 ሉቃ 1÷42-45) ነቢዩ ኤርሚያስና መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
እግዚአብሄር ከማኅፀን ጀምሮ ነው የመረጣቸው፡፡ ታዲያ ጌታችን ከማኅፀን ጀም ጸጋውን የሚያሳድርባቸው ከሆነ ከተወለዱ በኋላ እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ማን ነው; እንዲሁም በወንጌል ላይ ጌታችን ሕፃናትን ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዳቀረባቸውና እንዳቀፋቸው እጁንም ጭኖ እንደባረካቸው ተጽፏል፡፡
8. (ማቴ 19÷13-15 ማር10÷13-16 ሉቃ 18÷15-17) እነዚህ ሕፃናት በወላጆቻቸው እምነት ነው የተባረኩት እንዲባረኩላቸው ወደ ጌታችን እንደ ኦሪቱ ልማድ ያመጧቸው ወላጆቻቸው ነበር፡፡ ታዲያ ባለቤቱ ሕፃናትን ከበረከቱ ካልነሣቸው ከበረከቱ ካላራቃቸው ተጠምቀው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዳይቀበሉ ምን ይልክላቸዋል;
9. የመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው በሐዋርያት ዘመን ክርስትናን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ከነቤተ ሰቦቻቸው እንደተጠመቁ አስረጅ የመጻሕፍት ታሪኮች ስላሉ
  • ልድያናቤተሰቧ (ሐዋ 1615)
  •  የወይኒ ቤት ጠባቂውና ቤተሰቡ(ሐዋ. 1633)
  • ቆርኔሌዎስናቤተሰቡ(ሐዋ 1048) 
  •  የምኩራቡ አለቃ ቀርስጶስና ቤተሰቡ (ሐዋ 188)
  •  የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች(1 ቆሮ 116)

ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን ለምን 40 እና 80 ቀናቸው ታጠምቃለች

ይህ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለምን ተሰራ ቢሉ የአበው ምክንያት

U አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ 40 እና 80 ቀናቸው በክብር ወደ ገነት እንደገቡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በመጀመሪያ በሠራው ሥርዓት መሠረት ወንዶችን 40 ሴቶችን 80 ቀን ታጠምቃለች ፡፡ ‹‹በተፈጠረባት ምድር ለአዳም 40 ቀን ከተፈጸመ በኋላ ይገዛትም ይጠብቃትም ዘንድ ወደ ገነት አስገባነው፡፡ ሚስቱንም 80 ቀን አስገባናት፡፡( ኩፋ 4÷-9)

Uበኦሪት (ዘሌ 12÷1-8) ላይ እስራኤላውያን የእግዚአብሔር በረከት እንዲያድርባቸው የእግዚአብሔር ሕዝብ /ወገን/መሆናቸው እንዲረጋገጥ ወንድ ልጅ በተወለደ 40 ቀን ሴት ልጅ በተወለደች 80 ቀኗ ወላጆቸው መሥዋዕት ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ይወስዷቸው ነበር፡፡ ካህናቱም መሥዋዕቱን ሠውተው ሕፃናቱን በእግዚአብሔር ስም ባርከው ስማቸውንም ከመዝገብ አስገብተው ይጽፏቸው ነበር፡፡ እንደዚሁም ቤተ ክርስቲያን ሕፃናቱን 40 እና 80 ቀን አጥምቃ የእግዚአብሔር ወገን ተደርጋለች፡፡ አሁን ክርስቲያኖች መስዋዕት ይዘው መሄድ አይጠብቃቸውም በመሥዋዕቱ ሕጻናቱን ለእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆኑ እናስረክባለን እንጂ ሕይወታቸውን ለእርሱ መሥዋዕት እንዲያደርጉ በእርሱ ፍቅር ትምህርት ሕይወት እንዲኖሩ በብሉይ መሥዋዕት በሐዲስ በዚህ ተክተነዋል፡፡

ስለዚህ ከላይ ባየናቸው ምክንያቶች ወንድ ልጅ 40 ሴት ልጅ 80 ቀናቸው ማጥመቅ እንዲገባ ታዟል፡፡ ነገር ግን ሕፃኑ ወይም ሕጻኗ ለሞት የሚያሰጋቸው ሕመም ካገኛቸው 40 እና 80 ቀናቸው በፊት በሞግዚት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተወስደው መጠመቅ ይችላሉ፡፡ ህጻኑ ሳይጠመቅ ቢሞት በካህን ጥፋት ከሆነ ከሥልጣን ክህነት እንዲሻር ጥፋቱ የወላጆች ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከምዕመናን እንዲለዩ ይደረጋል፡፡ (ፍት ነገ መንፈሳዊ አንቀጽ-3)

የንዑስ ክርስቲያኖች ጥምቀት

ንዑስ ማለት ትንሽ /ታናሽ/ ማለት ነው፡፡ ንዑስ ክርስቲያን የክርስቲያን ታናናሾች ማለት ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ስም የሚሰጣቸው ተጠምቆ የእግዚአብሔርን ልጅ ላልሆኑ ገና ለመጠመቅ በሂደት ላይ ላሉ ሰዎች ነው፡፡
ንዑሰ ክርስቲያን ዕድሜው ከፍ ያለ እና አስቀድሞ ክርስትናን ያልተቀበለ ስለሆነ ከመጠመቁ በፊት ትምህርተ ሃይማኖትን በሚገባ መማር አለበት፡፡ ይህን ሲጨርስ ሰይጣንን ክዶ ክርስቶስን አምኖ ሃይማኖቱን መስክሮ ጸሎተ ሃይማኖትን ደግሞ ይጠመቃል፡፡
ሐዋርያት በጥንተ ስብከት ከቤተ አይሁድና ከቤተ አሕዛብ ወደ ክርስትና የተመለሱትን ሰዎች ሲያጠምቁ አስቀድመው አስተምረዋቸው ነበር፡፡ ጌታም ያመነ የተጠመቀ ይድናል በማለት ተናግሯል፡፡ (ማር 16÷16)
ተጠማቂው ሃይማኖቱን ከተረዳና ካመነ በኋላ ንስሐ መግባት አለበት ፡፡ይህንንም ቅዱስ ጴጥሮስ (በሐዋ 2÷38) ላይ ገልጾታል፡፡ ተጠማቂው ሕጻን ከሆነ ግን የሃይማኖቱን ምስክርነት በሕጻኑ ምትክ የክርስትና እናትና አባት እንዲፈጽሙ ያደርጋል፡፡
ማጠቃለያ
  • ሥርዓተጥምቀትንመፈጸምየሚችለውሥልጣነክህነትያለውብቻነው(ማቴ28÷19)
  •  ምሥጢረ ጥምቀት የሚፈጸመው በስመ ሥላሴ ብቻ ነው(ማቴ 28÷19)
  •  የተጠመቀው ሰው ድኀነት ሥጋ ድኀነተ ነፍስ ያገኛል ያልተጠመቀ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያዩ አይችሉም (ማር 16÷-16' ዮሐ 3÷6)
ይቆየን ይቀጥላል

ስብሐትለእግዚአብሔር



1 comment: